“በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስርና ጥቃት በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል!” ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ በሲቪል ሰዎች ላይ እንግልትና እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት፣ ብሎም በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መከሰቱንና ሕይወት መጥፋቱን፣ እንዲሁም በታሳሪዎችና በምርኮኞች ላይ የሚደርስ ኢሰብአዊ አያያዝ፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ሕጻናትን ለውትድርና መጠቀም የሚያመላክቱ መረጃዎች እጅግ የሚያሳስበው መሆኑን ገለጸ።
ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ፣ ወረታ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ ሦስት የትግራይ ተወላጆች በድንገት በተሰባሰቡ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ መገደላቸው ለኮሚሽኑ የደረሱት ጥቆማዎች ያመለክታሉ።
ይህ ጥቃት የደረሰው ከእለቱ አንድ ቀን አስቀድሞ ፍየል ውሃ በሚባል ቦታ ሕወሃት/ትግራይ መከላከያ ኃይሎች በወሰዱት የጥቃት እርምጃ የፎገራ ወረዳ ነዋሪዎች የሆኑ የሚሊሽያ ቡድን አባላትና የወረዳው የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ መገደላቸው ከተነገረ በኋላ ነው። ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋዱን ጉመራ ወንዝ ተብሎ ከሚጠራና ከተገደሉት የወረዳው የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ ትውልድ ቦታ የኃላፊውን እሬሳ ለመቀበል የመጡ ነዋሪዎች ጥቃቱን እንዳደረሱ ይነገራል።
የፎገራ ወረዳና የአካባቢው የፀጥታና የአስተዳደር ኃላፊዎች በወሰዱት አፋጣኝ እርምጃ ሁኔታው የተረጋጋና ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም፣ የተከሰተው ሁኔታ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንዳይዛመት የሚያሰጋ ነው።
በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይና የሕወሃት/ትግራይ መከላከያ ኃይሎች ተቃዋሚ ናቸው በሚል በሲቪል ሰዎች ላይ እንደተወሰዱ የሚነገሩ የግድያና የአፈና እርምጃዎች የሚያሳስቡ ናቸው። ከአላማጣና አካባቢው በድጋሚ ያገረሸውን ግጭትና በመኾኒ እየተወሰዱ ስለመሆናቸውን የሚነገሩ የበቀል ጥቃቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰዎች መፈናቀል እያደረሰ ነው።
ቴሌኮሙኒኬሽንና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ስራውን አዳጋች ያደረገው ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ያለውን የተደራሽነት ሁኔታ በተመለከተ የሚያደርገውን ክትትል የሚቀጥልና በቆቦ፣ በወልዲያ እና በማርሳ ተጠልለው የሚገኙ ከአላማጣና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎችን የሚጎበኝ መሆኑን ይገልጻል።
ኢሰመኮ የግጭቱ መባባስና የግጭቱ ተጽእኖ በአፋርና በአማራ ክልል የሚገኙ ቦታዎችን ጨምሮ ወደ ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጭምር መስፋፋቱ እጅግ የሚያሳስበው ነው።
እንዲሁም ኮሚሽኑ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚደርሱትንና በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሱ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት እና የእንግልት መረጃዎችንም እየተከታተለ ይገኛል። የሚድያ ሰራተኞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ሌሎች ቦታዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ለኮሚሽኑ ጥቆማዎች ደርሰውታል።
ከሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተባብሶ የታየው ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ክስተትና እስር ሁኔታ ተገቢውን ትኩረትና መፍትሔ ከአለማግኘቱ በተጨማሪ፤ በስፋት የሚደመጡ የጥላቻና ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች ሁኔታው ሊያባብሱና ብሎም በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ትስስር ሊያላሉ የሚችሉ ናቸው። ስለሆነም፣ በየትኛውም አካባቢ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁና የፌዴራል መንግስትም ሆነ የክልል መስተዳድሮች በነዚህ ነዋሪዎች ላይ እንግልት ያደረሱና ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች የፈጸሙ የሕግ አስከባሪ አካላትን ሕግ ፊት ሊያቀርቡ ይገባል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በተለይም ይህን በመሰል ፈታኝና የውጥረት ወቅት መንግስት ለሲቪል ሰዎችና ተጋላጭ ለሆነው ማኅበረሰብ ክፍል ከፍተኛ ጥበቃ የማድረግ ተጨማሪ ኃላፊነት የሚጣልበት ጊዜ ነው። መሰረታዊ የሆኑ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና የሰብአዊ መብቶች መርሆች በግጭት ወቅት ጭምር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያዙና ሲቪል ሰዎችና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ላይ ከፍ ያለ ግዴታ የሚጥሉ ናቸው።
ስለሆነም ኮሚሽናችን በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታውን በተመለከተ የሚያደርገውን የክትትል ስራ የሚቀጥል ሲሆን፣ በግጭቱ ለሚሳተፉ ወገኖች በሙሉ እንዲሁም የሚድያ ተቋማትን ጨምሮ ለሀገራዊና ለዓለም አቀፍ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሙሉ ማንኛውንም የማኅበረሰብ ክፍል አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር፣ መግለጫዎችና ተግባራት እንዲቆጠቡ ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል” ብለዋል።
ፎቶ:- ዶ/ር ዳንኤል በቀለ