Connect with us

ከኦሮሚያ ክልል የተሰጠ መግለጫ

ከኦሮሚያ ክልል የተሰጠ መግለጫ
Photo: Social media

ዜና

ከኦሮሚያ ክልል የተሰጠ መግለጫ

ከኦሮሚያ ክልል የተሰጠ መግለጫ

የኦሮሚያ ክልል ሕዝብና መንግስት ኢትዮጵያን በመገንባት ዉስጥ የሚመጥነዉን አስተዋፅኦ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ የሀገርና የህዝብ ሉአላዊነትና ነፃነትን ለማስከበር በሚከፈለዉ መስዋዕትነት ላይ እራሱን ቆጥቦ አያውቅም፡፡

በውጪ ወረራና በታሪክ አጋጣሚ የባንዳነትን ተግባር ስፈጽሙ በነበሩት ኃይሎች ላይ በየ ታሪክ ምዕራፉ እራሱን ሰጥቶ ኢትዮጵያን የገጠሙዋትን ችግሮች ለማክሸፍ መስዋዕትነትን ከፍሏል፡፡ እንደ ሐገር ስናስመዘግብ በቆየናቸው ድሎች ውስጥ ተወራራሽ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡

ዛሬም እንደ ትናንቱ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ህዝብ በማቀናጀት በወንድሞቻችን አብሮነት በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣውን የውስጥና የውጪ ትንኮሳ ለማክሸፍ ዝግጁነቱን ይገልፃል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፌደራል መንግስቱ የወሰደዉን የአንድ ወገን ተኩስ የማቆም እርምጃ ለሕዝብ ጥሩ የጥሞና ዚዜ የፈጠረ መሆኑን አምኖ ስደግፍ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከአፈጣጠሩ የተጣመመው ሕወኃት/ጁንታ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ለተደረገው ጥሪ ቦታ እንደሌለው በግልፅ አሳይቷል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ በአሮጌ የፖለቲካ እይታ ተሞልቶ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል፡፡

የሕወሓት የፖለቲካ ፅንሰ ሐሳብ ህዝብን እንደ ጠላት በመፈረጅ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የግጭት መነሻ የአንድነት ፀርና ለሐገራዊ ብሔርተኝነት መውደቅ ምክንያት ሆኗል፡፡

የጁንታው ፀረ አንድነት ፈንጂ በየቀኑ እየፈነዳ ለዜጎች ሞትና ስቃይ ምክንያት በመሆን ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የድህነትና የኋላ ቀርነትን እሽክርክሪት ዘመን አራዝሞብናል፡፡

ለእድገታችንና የብልፅግና ጉዞ እንቅፋት በመሆን እንድንሸማቀቅ አርጎናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሃገርና ህዝብ በቀዳሚነት እየተጎዱ ነው፡፡

ሕወሓት/ጁንታ እታገልላቸዋለሁ ብሎ እሚናገረውና በስማቸው እየኖረ ያለዉን የትግራዋይ ሕዝብን ጨምሮ አስቦላቸዉ ወይም ተቆርቁሮላቸው አያውቅም፡፡ ይህ ቡድን ትናንት የሐውዜን ህዝብ በሚገበያይበት ቦታ ላይ ቦምብ በማዝነብ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈፅም ለፕሮፖጋንዳ ግብአትነት እንጂ ለሉአላዊነት ትግል አልነበረም፡፡ ሕዝብን በመጨፍጨፍ ህዝብን ነፃ ማውጣት በየትኛውም መስፈርት የሚታረቅ አስተሳሰብ አይደለም፡፡

ዛሬም ቢሆን በተባበሩት መንግስታት የወጣውን የሕፃናት መብት ድንጋጌ በመጣስ ጨቅላ ሕፃናትን ለጦርነት ከፊት አሰልፈው በመማገድ ላይ ይገኛል፡፡ አዛውንቶችን፣ እናቶችንና የሐይማኖት አባቶችን እንደ ጋሻ ከፊት በማሰለፍ በእልቂታቸው የጀግንነት አክሊል ለመድፋት ይሞክራል፡፡

አሁንም ቢሆን ሕወሓት/ጁንታ የፌደራል መንግስት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ካሳየው ፍላጎት በተቃራኒ በመሔድ ላይ ይገኛል፡፡ በፌደራል መንግስት የታወጀው የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት አርሶ አደሩ በክረምት ወቅት ተረጋግቶ እንዲያርስ፤ ለዜጎች እርዳታ እንዲደርስና ግጭት እንዳይባባስ ቢሆንም ጁንታው የተፈጠረበትን የጥፋት ስሜትና እጅ መቆጣጠር አልቻለም፡፡

የ1967ቱ የሕወሓት/ጁንታው ማኒፌስቶ ህዝብና ህዝብን በማጋጨት ሰላምና መረጋጋትን ለመንፈግ የተወጠነ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ግንባታ ቋሚና ማገር በመሆን ለዛሬ ያደረሳትን ህዝብ ለመበታተን ያለመ ነው፡፡

ሕወሓት/ጁንታ ላለፉት 27 ዓመታት ሀገር ሲመራ በነበረበት ወቅት በህዝብ ውስጥ ትቶት ያለፈው ሰቆቃ ሳያንስ ዛሬም በሐገር ላይ የጭካኔ ተግባራትን እየፈፀመ ነው፡፡

ሕወሓት/ጁንታ በማይካድራ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ተግባር በብሄር ላይ ያተኮረ የህዝብ ጠላትነት ላይ የተመሰረተ እኩይ ተግባር ነው፡፡ አሁንም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈፀም ሲቅበዘበዝ ይታያል፡፡

የሕወሓት/ጁንታ ኃይል የሕዝብና የሐገር ጥቅምን አሳልፎ ከመስጠት አይመለስም፡፡ እድገታችንንና ልማታችንን ለመግታት ከሚታገሉ የዉስጥና ውጪ ጠላቶች ጋር በማበር የጥፋትና የማፍረስ ሴራዎችን በዋና ተዋናይነት ሲፈፅም እንደነበረ በገሀድ ታይቷል፡፡ ሕወሓት/ጁንታ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከማስተጓጎል ጀምሮ ከነአካቴው እስከ ማደናቀፍ ድረስ የተላላኪነትና የባንዳነት ትወና ድርሻውን ተወጥቷል፡፡

የሕወሓት/ጁንታ ክህደት በህዝብ ንቀት ብቻ የተገታ አልነበረም፤ የሐገር ሉዓላዊነትን ጭምር ጥያቄ ውስጥ እስከሚገባ አስነዋሪ ተግባር ፈፅሟል፡፡ ኢትዮጵያ ብትፈርስም፣ በውጪ ወራሪ ብትወረርም ደንታ እንደሌለው እስከ መግለፅ ደርሷል፡፡

ስለሆነም ሕወሓት/ጁንታ ለአንዱ የሚያስብ፣ ሌላውን የሚነፍግ ሳይሆን በጅምላ የመጨፍጨፍና የማፈራረስ አቅጣጫን ይከተላል፡፡ ከእሱ ተወልዶ፤ ከእጁ በልቶ ላደገው ህዝብ የማይራራ፣ ሌላ ዘመድ ሊኖረውም ሆነ ሊያፈቅር አይችልም፡፡ “ጅግራ ዘመድ መስሎ ወፊቱን በላት: እንደሚባለው ሁሉ፤ ለአንዱ አዝኖ፤ ሌላውን አኩርፎ ሌሎችን ደግሞ የተፀየፈ መስሎ የሚቀርበውን ፕሮፖጋንዳ አምኖ መቀበል ሞኝነት ነው፡፡

የሕወሓት/ጁንታ ኃይል ተሸንፏል፤ በፖለቲካ ሜዳዉ አሸናፊ ሀሳብ ማቅረብ ተስኖት ለቆ ስደትን መርጧል፡፡ በማግስቱ የጦርነት ነጋሪትን መጎሰም ጀመረ ፡፡ ውሎ ሳያድር በዜጎቻ ላብ የተገዛውን የሀገር ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት መሳሪያ በመዝረፍ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ዛተ፡፡

በከሀዲዎችና የውጪ ሃይሎች ማበረታቻ የሰከረው ሕወሓት በመከላከያ ሰራዊቱ ለይ የጥቃት እርምጃ ወሰደ፡፡ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ከ20 ዓመታት በላይ የኖረውን የመከላከያ ሠራዊት በከባድ የጭነት መኪናዎች ከመጨፍለቅ ጀምሮ እጅግ አስነዋሪ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

የክልልና የሀገራችን ህዝብ በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መከላከያ ሰራዊቱን ለመደገፍ ሁሉ አቀፍ ድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ዛሬም ቢሆን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ሕዝብ የሀገር ሉዓላዊነት ጋሻ ከሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሆን ማናቸዉንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነዉ፡፡ መንግስትም የህዝብ ተሳትፎን በማቀናጀት ሁለንተናዊ ስኬት ለማስመዝገብ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡

ትናንት በችግር ውስጥ የመንግስትን ጥሪን በመስማት ሁለንተናዊ ድርሻችሁን የተወጣችሁና የአሸባሪዎች የጥፋት መርዝ እንዲደፋ ያደረጋችሁ የክልላችን የህብረተሰብ ክፍሎች ዛሬም እንደ ትናንቱ የጎላ ተሳትፏችሁን እንድታበረክቱ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በሕዝባችን የተባበረ ክንድ ዘላቂ ሉዓላዊነታችን ይረጋገጣል

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top