የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መገለጫ ሰጥተዋል
ዶ/ር ሊያ ታደሰ በመግለጫቸውም ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ በሀገራችን የወረርሽኙ ምጣኔ በአንፃራዊ ሁኔታ ከነበረበት የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም ወረርሽኙ አሁን ላይ በተለያዩ አፍሪካ አገራት ለሦስተኛ ዙር ወይም third wave እየተከሰተ ሲሆን ይህም ችግር በቀጣይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ላይ ከፍተኛ ስጋትን ስለፈጠረ ህብረተሰቡ የመከላከያ እርምጃዎችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን በሙሉ አቅም ከመተግበር እና ከማስተግበር ጎን ለጎን የኮቪድ-19 ክትባት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሰጠ እንደሆነና በዚህም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የመጀመርያ ዙር ክትባት እንዲያገኙ መደረጉንና የመጀመርያዉን ዙር ወስደው 3 ወር ለሞላቸዉም የሁለተኛ ዙር ክትባት በመስጠት ረገድም እስከአሁን ወደ 42 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ሁለተኛ ዶዝ ወስደዋል ብለዋል::
እንደ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ገለጻ 400 ሺህ የአስትራዜኒካ ክትባት ከጥቂት ቀናት በፊት ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ገልጸው የመጀመሪያውን ዶዝ ስርጭት እና አጠቃቀምን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለሁሉም ክልልሎች የሁለተኛው ዶዝ ክፍፍል እና ስርጭት እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡
ህብረተሰቡም ይህንን በመገንዘብ የመጀመሪያውን ክትባት በወሰደበት የጤና ተቋም በመሄድ በአዲስ አበባ ከነገ ሮቡዕ- ሀምሌ 7/2013 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ከአርብ ሀምሌ 9 /2013 ዓ.ም ጀምሮ የመጀመሪያውን ክትባት ከወሰዱ 3ወር የሞላቸው ሁሉ ሁለተኛውን ክትባት መውሰድ ይችላሉ ብለዋል።
አሁን ላይ ካለው የኮቪድ-19 ክትባት እጥረት ጋር ተያይዞ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር በቅጅትና በትብብር በመስራት እንደሚገኝ እና ተጨማሪ ክትባቶች በቅርቡ የሚገቡ ሲሆን ከዚህ ቀደም የተገፕው የሳይኖፋርም ክትባትን በአዲስ አበባ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ባሉ ጤና ተቋማት መሰራጨታቸውን አስታውስዉ በሥራ ባህርያቸው በተለየ ተጋላጭ ለሆኑ ሠራተኞች በአዲስ አበባ በአቅራቢያቸው ባሉ ጤና ጣቢያዎች በመሄድ መታወቂያቸውን በማሳየት ብቻ መከተብ እንደሚችሉም ጭምር ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ እነዚህም:-
- የትራንስፖርት ዘርፍ ሰራተኞች፣ የአውቶብስ፣ ሚኒባስ ሾፌሮች
- የመንግሥትና የግል ባንኮች ሰራተኞች
- የገቢዎችና ጉምሩክ ቢሮዎች ሠራተኞች
- የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
- የማረሚያ ቤቶች እና የፍርድ ቤቶች ሠራተኞች
- የውልና ማስረጃ እንዲሁም ማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች
- መምህራን-የህፃናት መቆያ፣ የመደበኛና የኮሌጅ መምህራን
- የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ሠራተኞች
- የሚዲያ ሠራተኞች
በአዲስ አበባ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የመንግሥት ጤና ጣቢያዎች የሚሰጥ መሆኑን አዉቀዉ የተዘረዘሩት ተቋማት ሰራተኞች የመጀመርያ ዙር ያልወሰዱ እየሄዱ መከተብ እንደሚችሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የኮቪድ 19 ምርመራ ማጠናከርን አስመልክቶ ሚኒስትሯ እደተናገሩት በ20 ደቂቃ የሚደርስ የፈጣን የኮሮና ምርመራ ማድረጊያ በሁሉም ክልሎች የተሰጠ እደሆነና ማንኛውም ሰው የኮቪድ19 ህመም ምልክት ሲሰማውና በኮቪድ መያዙ ከተረጋገጠ ሰው ጋር ንክኪ የነበረው ከሆነ በሁሉም ጤና ጣቢያዎች በመሄድ ምርመራውን በነጻ ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡
አዳዲስ የኮቪድ 19 ዝርያዎች ስርጭትን በተመለከተ በአገራችን አልፋ እና ቤታ የሚባሉት የቫይረሱ ዝርያዎች ከዚህ በፊት ስናደርጋቸው በነበሩት ምርመራዎች መገኘታቸው የተረጋገጠ ሲሆን አሁን የመጣው የዴልታ ቫይረስ መኖሩን ለማረጋገጥ ገና ምርመራ እየተጀመረ እንደሆነና ዝርያው በበርካታ ሀገሮች ካለው ስርጭት አኳያ ሊኖር እንደሚችል የሚጠበቅ በመሆኑ ህብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ እናሳስባለን።
ቀጣይ የዝርያ ማረጋገጥ አቅምን ለማጠናከርም ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በቅርቡ አዲስ የጋራ ኘሮጀክት የጀመርን ሲሆን ውጤቱንም በቀጣይ እናሳውቃለን በማለት በመግለጫቸው ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡(ጤና ሚኒስቴር)