ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ!
(ሙሼ ሰሙ)
ስምንት ወር ከፈጀ፣ ከፍተኛ የሰው ኃይልና የንብረት ውድመት በኋላ የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ለቆ ወጥቷል፡፡ መንግስት ለውይይት ፈቃደኛ መሆኑንም ገልጿል፡፡ ከእርዳታ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን እንደሚፈታ፣ መንገዶችንም ክፍት እንደሚያደርግና በረራም መፍቀዱ እየተሰማ ነው፡፡
ውሳኔው በማንኛውም መስፈርት በጎና ተራማጅ ጅምር ነው፡፡ በዚሁ ልክ ከምዕራባውያን የሚጠበቀው ነገር ሕዝብን ከሚጉዱ ተግባራት የተቆጠበ፣ ሁሉንም በፍትሐዊነት የሚያይና ጅማሮው እንዲቀጥል ሚናቸውን ያገዘፈ መሆን ነበረበት፡፡
በዚህ ደረጃ ብዙ ርቀት ሊያስኬድ የሚችል አማራጭ ከቀረበ በኃላ፣ ዛሬም ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቡ ተጠናክሮ እንደቀጥል መወትወታቸው፣ ችግራቸው ከጦርነቱ ጋር ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ከማስራብና ከማስጠማት ጋር እንደሆነ ግልጽ ያደረገ ነው።
ለኢትዮጵያ ሉዕላዊነትና ለሕዝቦቿ ልዕልና ተቆርቋሪነት የሚተጉ የሚመስሉት ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ ይደጉሙት የነበረውን € 540 ሚሊየን ማቀባቸውና ሌሎች ሀገርት ይህንኑ አቋሙ እንዲከተሉት ጥሪ ማድረጋቸው ማንነታቸውን ያጋለጠ ነው፡፡
አስደናቂው ነገር የበጀት ድጎማ መከልከላቸው ሳያንስ፣ በጀት እንዲለቀቅ ጥሪ አድራጊ ሆነው የመቅረባቸው ጉዳይ ነው፡፡ “Double Standard” ይሉሃል እንግዲህ ይሄ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እርዳታዎችንና ብድሮችን የምታውለው ለረጅም ዓመታት የተወጠኑና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማስጨረስ፣ ለሪከረንት በጀት መሸፈኛ፣ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለእዳ መክፈያና ከፍተኛ ጉድለት ያለበትን የውጭ ምዛሪ ፍላጎት ለማሟልት ነው፡፡ ድጋፉን ማቋረጥ ማለት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ስራ ማሳጣት፣ እቅድ የተያዘላቸውን ፕሮጀክቶች ማሰናከል፣ አገልግሎት ሰጭውን ሰራተኛ ደሞዝ መከልከልና የተዳከመውን አቅርቦት በማባባስ የዋጋ ንረትና ቀውስ መፍጠር ነው፡፡
ይህ ማለት ደግሞ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎችንና ቤተሰቦቻቸውን በሂደት አስርቦና አስጠምቶ ወደ ጎዳና እንዲወጡ በማድረግ ለአመጽና ለግጭት መገፋፋት ነው፡፡ በአንድ የፖለቲካ ወቅት የተፈጠረ ግጭትን ሰበብ አድርጓ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጅምላ ማስራብና ማደህየት በጠላትነት ተሰልፎ ከመውጋት የሚተናነስ አይደለም፡፡
ከዚህ ደግሞ አንድ ፊቱኑ ታጥቆና ሰንቆ በኢትዮጵያውያን ላይ ግልጽ ጦርነት ማወጅ የሚሻል ይሆናል፡፡ ምዕራባውያን ሊረዱት የሚገባው ነገር እንዲዚህ ዓይነቱ ዓይን ያወጣና በሕዝብ ላይ የታቀደ ግፍና ሴራ ውጤቱ ተያይዞ መውደቅ ነው፡፡ ምዕራባውያን ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ።