ድሉ የጋራችን ነው!!
(ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ)
በእውቀት አንፆ በክብር ያሳደገኝን ማህበረሰብ ዝቅ ብዬ ስለማገልገል ስል ተወዳደርኩ ህዝቤም በነቂስ ወጥቶ መርጦ አደራውን አሸከመኝ:: እውነተኛ ድምፁ ለመሆን የገባሁለትን ቃል ተቀብሎ ከጀርባየ ለተሰለፈው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን አገልግሎቴን ለመስጠት በቁርጠኝነት ተነስቻለሁ::
ትላንት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት መሠረት ድምፅ ከሰጠው 49 ሺ 364 መራጭ ሕዝብ ውስጥ 37 ሺ 705 ድምፅ ለኔ በመስጠት 76 ነጥብ 3 በመቶ ውጤት በማስገኘት በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማህበረሰቤን እንድወክል ህዝቡ እምነቱን በኔ ላይ በመጣል ከፍተኛ ሀላፊነት በማሸከም በካርዱ ድምፁን ለኔ መስጠቱ ትልቅ ድል ነው:: ድሉ የኔ ብቻ ሳይሆን የእናንተም ነው:: ለዚህም እንኳን ደስ አለን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ::
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንደ ሀገር ያለንበት ወቅት ውስብስብ ችግሮች የተጋረጡበት መሆኑ እሙን ነው:: ለነዚህ ችግሮቻችን የመፍትኄ አካል እንድሆን ኢትዮጵያውያንን በእኩልነት እንዳገለግል የተሰጠኝ አደራ እንዳለ ሆኖ ሁለተናዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ቀን ሌት ሳልል ባለኝ እውቀት እና ሀብት በዬትኛውም አቅጣጫ ላይ ያለውን ህዝቤን በእኩልነት እና በታማኝነት እንዲሁም በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኔን ላረጋግጥላቹ እወዳለሁ::
ከዚህን ቀደም በተለያዩ መንገዶች ስገልፅ እንደቆየሁት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ይፋ ከተደረገበት እለት ጀምሮ የተለያዩ ፓርቲዎች እንድቀላቀላቸው ቢጠይቁኝም በአንድ ፓርቲ አስተሳሰብ ስር ከመግባት በግል መወዳደርን መወሰኔ ይታወሳል ሆኖም ህዝባችን እምነቱን ጥሎብኝ እንዳገለግለው ስለመረጠኝ ደስ ብሎኛል:: ያለኝ ምስጋናም የላቀ ነው::
ላሳደገኝ ማህበረሰብ ዳር ሆኜ ከንፈር ከመምጠጥ በመጫወቻው ሜዳ ላይ በመሆን እንድ ዞን ያሉበትን ችግሮች ለአብነትም የአከባቢው የጤና ዘርፍ እጅግ መበላሸት የትምህርት ጥራቱ ክድጡ ወደ ማጡ አይነት መሆን የመሰረተ ልማቶች ችግር በተፈጥሮ በታደልች ምድር የስራ አጥ ቁጥር ማሻቀብ ለብዙሃኑ መትረፍ የምትችል ኢሉ አባቦር ለራሷም መሆን አለመቻሏ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደ ዞን ብቻ ሳይሆን እንድ ሀገር የችግሮቹ የመፍትኄ አካል ለመሆን ያለኝን ሀገራዊ ቅቡልነት በመጠቀም በግሌ ስታገል ከነበረዉ በተጨማሪ ወደ ፖለቲካው ሜዳ በመቅረብ ለመረጠኝ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ላልመረጠኝም በእኩልነት ለማገልገ በከፍተኛ ተነሳሽነት ዛሬም እንደትላንቱ ቃል እገባለሁ::
በዚህ ምርጫ ኡስታዝ ካሚል እኛን ሊወክለን ይገባል ድምፃችን እንዲሆን እንሻለን ብላችሁ ከጎኔ በመቆም የሞራል ስንቅ የሆናችሁኝ ጊዜያችሁን እና ሁሉ ነገራችሁን ስጥታቹ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ክህዝባችን ጋር የተሳኩ ውይይቶችን እንድናደርግ የረዳችሁኝ ሁሉ ድሉ የናንተም ነውና እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ደስ ያለን:: ሁላችሁም ላበረከታችሁት ሚና በእኔና በማላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስም አመሰግናለሁ::
በመጨረሻም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በማሸነፌ ደስታችሁን በመግለፅ ከጎንህ ነን ላላችሁኝ መላው የሀገሬ ዜጎች ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረብኩ ሀገራችን ኢትዮጵያን ከገባችበት ውስብስብ ችግሮች ማላቀቅ ከሁላችን የሚጠበቅ መሆኑን ተገንዝባችሁ ባላቹ አቅም ሁሉ በእኩልነት ህዝባችንን እንድናገለግል ጥሪየን ለማቅረብ እወዳለሁ::
***
የአዘጋጁ ማስታወሻ:- ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ በኦሮሚያ ክልል መቱ ዞን ኢሉአባቦራ ወረዳ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተወዳድረው ያሸነፉት በግል ነው።