አረንጓዴዋ አርባ ምንጭ ላይ አረንጓዴ ካባ መደረብ
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በአርባ ምንጭ ቆይታው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ላይ ተሳትፏል፡፡ አርባ ምንጭ ውብና ለምለም ከተማ ናት፡፡ አረንጓዴዋን ከተማ ከነ ውበቷ ለማኖር የሚደረገው አረንጓዴ የማልበስ ዘመቻን አንድ ኩነት እንዲህ ዘግቦታል፡፡)
(ሄኖክ ስዩም – ድሬ ቲዩብ)
አርባ ምንጭ የሺህ ውበት ምድር ናት፡፡ የሁሉም መነሻና መድረሻ ግን ልምላሜዋ ነው፡፡ በማለዳ ለማስ ስፖርት ኩነቱ ለምለም አደባባይ የከተተው ተሳታፊ መዲናውን ለምለም ለማድረግ እጆቹ ችግኝ አንስተዋል፡፡
አርባ ምንጭን በማስ ስፖርት ፌስቲቫል ያደመቃት የ”ትውልድ ማሻገር” ፕሮጀክት በ120 ሚሊዮን ብር ገደማ ሊያስገነባው ካሰበው የስፖርት ማዕከል ባሻገር ሌላው ዓለማ በሥነ ምግባር በታነጸ ራዕይ ያለው ትውልድ ንጹህና ውብ ከተማን ከአረንጓዴ ቀለም ጋር እውን ማድረግ ነው፡፡ ይህም (Green & Clean City) ሲሆን ይሄንን ያስመሰከረበትን ኩነት በመጀመሪያው የአደባባይ ትዕይንት እውን አድርጎታል፡፡
የችግኝ ተከላው የትነበርሽ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ የተከናወነ ሲሆን የማስ ስፖርቱ ተሳታፊዎች አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
አርባ ምንጭ ከአረንጓዴ ውበት ጋር ጥብቅ ምስጢር ካላቸው የሀገራችን ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ውበትና ልምላሜ ትርጉሙ የሚነገራት ሳይሆን እየኖረችው ያለው ህይወት ነው፡፡ ሙቀት በዛፍ ጥላ ድል ሲደረግ ለመመስከር የምትችል የኢትዮጵያ መዲና ናት፡፡ ቀለም ምን ያህል የሰው ቀልብ እንደሚስብ ለመረዳት አረንጓዴው ምድሯ ማርኮት ልቡን የሰጠውን መቁጠር ነው፡፡ አርባ ምንጬ፤
የአረንጓዴ አሻራው ተግባር ቀድሞ ጀምሯል፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሻራቸውን አኑረዋል፡፡ ገና እንደሚቀጥል ሰምቻለሁ፡፡ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የዓለም ሬንጀር ቀንን በብሔራዊ ደረጃ ሲያስተናግድ አረንጓዴ አሻራው ደምቆ ይቀጥላል፡፡
አርባ ምንጭ መገለጫዋ ብዙ ነው፡፡ ሥጋ ቤቶቿ ሚዛናቸው ያልከፋ ዋጋቸው የማያስደነግጥ ነው፡፡ ሽማግሌዎቿን ተማምና፣ በባህሏ ጉልበት ኮርታ በአናቱ ተስፋ ያለው የነገ ጎዳና ላይ ነች፡፡
አርባ ምንጭ የደረሰ በውብ ሪዞርቶቿ አፋፍ ቆሞ ቁልቁል ማየት አልያም ወርዶ ከምንጮቿ መጎንጨት ይችላል፡፡ የበረከት ምድር ዋና ከተማ ናት፡፡ የጥበበኞች መዲና የመኾኗን ያህል ገና ብዙ ያልተሰራ ስራ አለ፡፡ አዲስ የሽመና አብዮትን እውን የሚያደርግ ድንቅ ፕሮጀክት ልጎበኝ ነው፡፡ አብራችሁኝ ትሄዳላችሁ፡፡ የነገ ሰው ይበለን፡፡