በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ የማይወስዱ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አሳሰበ
– የግዥ መመሪያን በመጣስ የብር 1 ነጥብ 2 ቢልየን ብር ግዥ ተፈጽሟል፣
– በ30 መ/ቤቶች ብር 475 ሚልየን የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብለት ወጪ የሆነ ሲሆን፣ 62 መ/ቤቶችና 11 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ደግሞ መመሪያን ሳይከተሉ የብር 96 ነጥብ 8 ሚልየን ከደንብና መመሪያ ውጪ ክፍያ መፈጸማቸው ተረጋግጧል፣
በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ የማይወስዱና የመንግስትን ሀብት በአግባቡ የማያስተዳድሩ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክትትሉንና ቁጥጥሩን ማጠናከር እንዳለበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ አስገነዘቡ፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች ላይ ያካሄደውን የ2012 በጀት አመት የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 22/2013 ዓ.ም ባቀረቡበት ወቅት በኦዲት ተደራጊዎች ላይ ለበርካታ አመታት በኦዲት ግኝትነት የሚጠቀሱ ችግሮች አሁንም ሳይታረሙ እንደቀጠሉ ገልጸዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት የኦዲት ግኝቶቹ በየአመቱ ተደጋግመው የሚከሰቱት በመንግስትና ህዝብ ሀብት ላይ ጉዳት በሚያደርሱና የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ በማይወጡ የመንግስት ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ላይ አስተማሪ የቅጣት እርምጃ ባለመወሰዱ ነው ብለዋል፡፡
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ኦዲቱን በታቀደለት ጊዜ መጀመር አልተቻለም ያሉት ምክትል ዋና ኦዲተሯ በዚህም ምክንያት የእቅድ ክለሳ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም በ118 መ/ቤቶችና 36 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ላይ የፋይናንሻል ኦዲት ለማድረግ እንዲሁም 23 አዲስና 4 የክትትል የክዋኔ ኦዲቶችን ለማከናወን ታቅዶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የእቅድ አፈጻጸሙን ሲገልጹም የ117 መ/ቤቶችና የ35 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የፋይናንሻል ኦዲት (99.1 በመቶ) ተጠናቋል ብለዋል፡፡ በክዋኔ ኦዲት ረገድም 17 አዳዲስ የክዋኔ ኦዲቶችና 3 የክትትል ኦዲቶች ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቃቸው አፈፃፀሙ 74% እንደሆነና ፤1 መደበኛ ኦዲት ባለመጠናቀቁ ወደ 2013/2014 ኦዲት አመት እንደተሻገረ ቀሪዎቹ 5 ኦዲቶችም ስራቸው ተጠናቆ የመውጫ ስብሰባና የኦዲት ተደራጊዎችን ምላሽ የሚጠባበቁ በመሆኑ ሲጠናቀቁ አፈፃፀሙ 92.59% እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት የፋይናንሻል ኦዲቱ የወጡ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ህጎችን በአግባቡ ባለመተግበር ምክንያት የታዩ ግኝቶችን አሳይቷል ብለዋል፡፡ ከነዚህ ግኝቶች ውስጥ ከጥሬ ገንዘብና ከባንክ ሂሳብ አያያዝ፣ ከውዝፍ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች፣ ከህግ ውጭ ከሚፈጸሙ ግዥዎችና የጥቅማጥቅምና ሌሎች ክፍያዎች፣ ከውል አስተዳደር ግድፈቶች፣ ከመንግስት ገቢ አተማመንና አሰባሰብ እንዲሁም ከውዝፍ ገቢ አሰባሰብ፣ ከበጀት አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲሁም ከንብረት አጠቃቀምና አያያዝ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡
በዚህ መልኩ ሪፖርቱ ከጠቀሳቸው ግኝቶች ውስጥ ለአብነት ያህል በመቱ ዩኒቨርስቲና በማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በድምሩ ብር 77 ሺህ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መገኘቱና በሁለት መ/ቤቶች ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ መደረግ የነበረበት በባንክ ያለ ብር 39.1 ሚልየን መኖሩ ተጠቅሷል፡፡
በውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ በኩልም በ90 መ/ቤቶችና 12 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ብር 7.48 ቢልየን በወቅቱ ሳይወራረድ መገኘቱንና ለዚህም ትልቁን ድርሻ ከሚወስዱ ተቋማት መካከል የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንደሚገኙበት ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
በገቢ አሰባሰብ በኩልም በድምሩ ብር 390 ሚልየን በተለያዩ ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶች ሳይሰበሰብ የቀረ ሲሆን በገቢዎች ሚኒስቴር ስር ባሉ በ6 ቅርንጫፎች እና በጉምሩክ ኮሚሽን ስር ባሉ 6 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በታክስ አዲት/ድህረ እቃ አወጣጥ ኦዲት ውሳኔ መሰረት ያልተሰበሰበ ብር 7.7 ቢልየን ውዝፍ የገቢ ሂሳብ መኖሩ ተገልጿል፡፡
በወጪ ረገድም በ30 መ/ቤቶች ብር 475 ሚልየን የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብለት ወጪ የሆነ ሲሆን፣ 62 መ/ቤቶችና 11 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ደግሞ መመሪያን ሳይከተሉ የብር 96.8 ሚልየን ከደንብና መመሪያ ውጪ ክፍያ መፈጸማቸውን፣ ይህን ክፍያ ከፈጸሙት ውስጥም ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ፣ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ፣ እንጅባራ ዩኒቨርስቲ፣ ወልድያ ዩኒቨርስቲና ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ዋና ዋናዎቹ መሆኑን አሳይቷል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ተቋማት አላግባብ በብልጫ የተከፈለ ብር 63.4 ሚልየን እንዳለ በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በግዥ በኩልም የግዥ መመሪያን በመጣስ የብር 1.2 ቢልየን ግዥዎች መፈጸማቸውና ይህንን ከፈጸሙ