Connect with us

ብልፅግና የአድርባይነትን ስርዓተ ቀብር ይፈፅም !!

ብልፅግና የአድርባይነትን ስርዓተ ቀብር ይፈፅም !!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ብልፅግና የአድርባይነትን ስርዓተ ቀብር ይፈፅም !!

ብልፅግና የአድርባይነትን ስርዓተ ቀብር ይፈፅም !!

(ገለታ ገ/ወልድ -ድሬቲዩብ )

 አድርባይነት የስብዕና (Personality) ምስክር ነው ፤ የአመለካከት ችግር ነው ፡፡ የሰዎች ስብዕናና አመለካከት የሚቀረፀው ደግሞ ከወጡበት ቤተሰብና  ከአደጉበት ማህበረሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ከሚሰሩበትና የሚውሉበት ከባቢም ነው፡፡  ሌብነትን ከሚፀየፍ ቤተሰብና ማህበረሰብ የተገኘ ልጅ ሌብነት ውስጥ ሊገባ አይችልም ፡፡ ወይም የመግባት እድሉ በጣም ጠባብ ነው፡፡

 በበታችነትና በተበደልኩ ስሜት ሲንቆላጭ ያደገ፤በስግብግብነትና ባልጠግብ ባይነት የበቀለዉ ደግሞ የፈለገዉን ያህል ቢምል ቢገዘት ህዝብ እየበደለ ከመዝረፍና የራሴ የሚለዉን ጥገኛ ከማደለብ አይቦዝንም ፡፡ ዛሬም ሆነ ትናንት ብዝበዛ የሚመነጨዉ ከእንዲህ ያለዉ ወረርሽኝ ነዉ፡፡ ለመመዝበር ደግሞ አድርባይነትና የትግል መዳከምን እንደመሰላል የሚጠቀመው ብዙ ነው ፡፡ ወደፊት ገዥው ፓርቲ ይህን ችግር አምርሮ እንዲል ታገለው ይጠበቃል ፡፡

 በሌላ በኩል  አድርባይነትን ከሚያስፋፉ ባህርያት አንዱ ስኬታማ የመሆን ጥማት  መሆኑን ማወቅ ይገባል ፡፡ ከሌሎች ሰዎች ተሽሎ የመገኘት፣ የማሸነፍ፣ በውጤት፣ በዝና በሀብት በልጦ የመገኘት (‹‹ወንዳታ›› የመባል) ውስጣዊ ፍላጎትን ሳያሸንፉ ህዝብ ማገልገል ሊኖር አይችልም ፡፡ በተለይ እንደ ብልፅግና (በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ በታዎችን ነቃቅሎ ለውጥ ለማምጣት እንደተነሳ ሃይል ) እንዲህ ያሉ አካሄዶችን ሳይታገስ ማረም አለበት ፡፡ ጥብቅ አሰራርም ሊዘረጋ ይገባዋል ፡፡

 ለአድርባይነት ከሚዳርጉ ምክንያቶች ሌላኛው የሰው ልጅ ያለው የስጋት (ስጋታምነት) ተፈጥሮ ነው፡፡ ሰው ለትንሹም ለትልቁም መስጋት ይወዳል፡፡ በሰላም አገር ‹‹ይገመግሙኝ ይሆን? ከደረጃ ዝቅ ያደርጉኝ ይሆን?… ይጠረጥሩኝ ይሆን?… ከቤተሰቤ ወደራቀ ቦታ ያዛውሩኝ ይሆን? ያባርሩኝ ይሆን?… ዕድገት ይከለክሉኝ ይሆን?” እያለ ይጨናነቃል፡፡

በዚህም መርህን ይጥሳል ፡፡ ለዚህ መድሀኒቱ ደግሞ ለትግል ዋስትና መስጠት ነው፡፡ለውጥ ፈላጊዎችን የልብ ታጋዮችን የሚደግፍ ስርአት ማበጀትም ነው ፡፡

 አድርባይነትና ጥገኛነት ሲበረታ  ሀሳብ አመንጭነትና ተነሳሽነት የጎደለው አስመሳይ እየበረከተ ይሄዳል ፡፡ ለድርጅቱም (ለተቋሙ) ሳይጠቅም ህዝቡ የጣለበትን አደራ ሳይፈጽም የትውልድ መዛባበቻና የዘመን መሳለቂያ የሚሆነውም ይበረክታል ፡፡ አዲሱ መንግስት ይህ አይነቱ አገርና ህዝብ ጎጂ አካሄድ እንዲከስምና ቀስበቀስ ከስሩ እንዲነቀል ነው መታገል ያለበት ፡፡ሳያሰልስም መስራት የሚገባው ፡፡

 የአድርባይነትን ጠባይ ከሚያበረታቱ ነገሮች መካከል የግለሰብ ወይም  የቡድን የስልጣን መጠንን አለመገደብ እንደሆነም መጠራጠር አይገባም ፡፡ ስልጣን ሲበዛ ብቻ ሳይሆን ካልተጠነቀቁ  ሁሌም ለሙስና ይጋብዛል፡፡ተጠያቂና ከልካይ የሌለበት፣ ፍፁማዊ ስልጣን ደግሞ ለፍፁማዊ ሙስና አይን ላወጣ አድርባይነት ይዳርጋል ፡፡

 (All power corrupts, and absolute power corrupts absolutely) ሰውዬው ከፍ ያለ ስልጣን ያለው ከሆነ ተቆጣጣሪ ስለሌለበት ያገኘውን መልካም አጋጣሚ ሁሉ ለግል ጥቅሙ የሚያውልበት ሰፊ እድል አለው፡፡ይህን መፍቀድም አይገባም !!

 የሙስና እናት ለሆነዉ አድርባይነት መኖር በር የሚከፍተው ሌላኛው አመለካከት ደግሞ ‹‹እኔ ባላደርገው ሌላው ያደርገዋል… ስለዚህ ለምን እኔ አላደርገውም ›› የሚለው ስንኩል አመለካከት ነው፡፡ ሌላው መጥቶ አጋጣሚውን ለራሱ ጥቅም የሚያውለው ከሆነ እኔስ እጄ ባለው አጋጣሚ ብጠቀም ሃጢአቴ እምኑ ላይ ነው ብሎ ያስባል፡፡  በዚያ ለላይ ሰዉ የበላይ አለቆቹንም ያያል፡፡

 ሲጠቃለል የመጭዉ ጊዜ ትልቁ የመንግስት መዋቅራዊ የቤት ስራ ተመሳሳዩን ወንጀልና ወንጀለኛ እየፈተሸ የህዝብን ጥቅም ማስከበር ላይ ሊሆን ይገባል ፡፡አሁን የተጀመረዉ ለዉጥ በአድርባይነትና በበሰበሰ ንቅዘት ተቦርቡሮ ሀገርን እንዳይጎዳ ብቻ ሳይሆን ከታሪክ ተምሮ አዲስ ታሪክ ለመፃፍም በፅናትና ህዝብን ባሳተፈ መንገድ አድርባይነትና ሌብነትን መታገል ይገባል፤ ያስፈልጋል!!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top