መቋጫ አልባው የአባይ ዲፕሎማሲና ተገለባባጩ የግብፅ አቋም !!
ንጉሥ ወዳጅነው( ድሬቲዩብ)
“የናይል ተፋሰስ አገራት የጋራ ስምምነት ማዕቀፍ ’’ ላይ በመመስረት ስራዉ የጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) ዋና ተልዕኮው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ነው ፡፡ ይህም የሱዳንንም ሆነ የግብጽን መሰረታዊ ጥቅም እንደማይጐዳ ፣ እንዲያውም ለሁለቱም የሚጠቅም መሆኑንና ጉልህ ተጽዕኖ እንደሌለው አገራችን ደጋግማ ስታስረዳ ቆይታለች ፡፡
ኢትዮጵያ የግብፅን የኖረ ስጋት ለመቀነስ ከአመታት በፊት፣በአለም አቀፍና ከሶስቱ አገራት በተውጣጡ የዘርፉ ሊቃውንት ፕሮጀክት አስከ ማስመርመር ደርሳለች ፡፡ ምክረ ሃሳቡንም ከሞላ ጎደል በቅንነት ተቀብላለች ፡፡ የግድቡ ዲዛይን አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን በአለም አቀፍ የሞያተኞች ቡድን አረጋግጣለች ፡፡ እነዚህ ሁሉ እዉነታዎች ታዲያ ለጋራ ተጠቃሚነት ሲባል የተከፈሉ የሰጥቶ- መቀባል እሳቤዎች እንጂ ፣ በማንም ተፅኖ በመንበርከክ የተካሄዱ ሽንፈቶች አልነበሩም ፡፡
እስከአሁን በተካሄዱ ሙያዊ ግምገማዎች፣በተለይ ዋናው የኃይል ማመንጫ ግድብ በጠንካራ አለት ላይ ያረፈ መሆኑን ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ የማያሰጋው እንደሆነና በብዙ ሺ አመታት አንድ ጊዜ ጐርፍ ቢከሰት እንኳን፣ማሳለፍ እንደሚችል በጥናት መረጋጋጡ ለግብፅም ሆነ ለሱዳን እፎይታ የሚሰጥ መሆን ነበረበት፡፡ ግን አልሆነም እንዳውም ንትርኩ እየተባባሰና እየተለዋወጠ ነው የቀጠለው፡፡
ሌላዉ ይቅር ከአመታት በፊት የሙያተኞቹ ቡድን ባቀረበው ምክረ ሃሳብ (ሪኮሜንዴሽን) መሠረት ቀጣዩ ሥራ ምክረ ሃሳብን ተግባራዊ ለማድረግ የሶስቱን አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብጽ) ማዕቀፍ ማደራጀት ሆኖ ሲያበቃ እንዴት ቸል እንደተባለ የሚታወቅ ነገር የለም ፡፡ ሶስቱ አገሮች ተገናኝተው ገና ከመነጋጋራቸዉ፣ግብጽ በማዕቀፉ አባላት ላይ ተቃውሞ ማምጣቷም ቢሆን ገና ከጅምሩ ድርድሩን የፈለገችዉ ጊዜ ለመግዛትና ለማደናቀፍ ብቻ እንደነበር አሳይቶ አልፏል ፡፡
በወቅቱ ኢትዮጵያና ሱዳን ከሶስቱም አገሮች የተውጣጡ ሞያተኞች ሥራውን መከታተል ይችላሉ ሲሉ ግብጽ ግን ‹‹ አይሆንም የአለምአቀፍ ሞያተኞችም ካልገቡበት አሻፈረኝ ›› ነበር ያላቸዉ ፡፡ የአተገባበሩን የማዕቀፍ ኮሚቴ ለማቋቋም ሌላ አለም አቀፍ ኮሚቴ አያስፈልግም ብትባልም ‹‹ አይሆንም ›› ብላ ነበር ፡፡ እርግጥ ይህንንም ‹‹እሺ›› ቢሏት ሌላ ተቃውሞ ማምጣቷ ግን አይቀርም ነበር፡፡ ደግሞም አምጥታለች፡፡
በመሰረቱ በግንባታዉ ሂደት ላይ ስለአተገባበር ማዕቀፍ ምስረታ አጀንዳ ተይዞ እያለ ፤ ከአጀንዳው ውጭ የሆነና በሌሎቹ አገሮች ተቀባይነት የሌለውን የመተማማኛ ማጠናከሪያ ሲስተም የሚል ባለሰባት ነጥብ ዶሴ ተሸክማ የመጣችዉ ግብፅ ነበረች ፡፡ የአንድ ትውልድ እድሜ በጠየቀ ውጣ-ውረድና ድርድር የተረቀቀውን ስምምነት አገራችን ስትፈርምና ስታፀድቅ፣ ግብጽ የአገሯን አለመረጋጋት ሰበብ እያደረገች ‹‹ቋሚ መንግስት ካልመሠረትኩ አልፈርምም›› እያለች ስታጓትት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ አባባሏን በትእግስት ያሰለፈችው ይህ ቀን እንደሚመጣ ተዘንግቶ አልነበረም ፡፡
ከአመታት በፊት ካርቱም ውስጥ በተካሄደ “የምስራቅ ናይል አገራት የምክክር መድረክ” ላይ አዘጋጆቹ ኢትዮጵያና ሱዳን በህዳሴው ግድብ የግንባታ ሒደት ዙሪያ ያላቸውን ተመሳሳይ አቋም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የባለሙያዎች ማብራሪያ አስደግፈው አቅርበው ነበር ፡፡ በዚህ ምክንያት ፣ የምክረ ሃሳብ ሒደቱን ለመታዘብ በስፍራው ከታደሙ የበርካታ አገሮች አምባሳደሮች ዲፕሎማሲያዊ ከበሬታን አግኝተው እንደነበርም አይዘነጋም ።
ቀደም ሲል የዚሁ “የምስራቅ ናይል አገራት የምክክር መድረክ’’ የተሰኘው ተከታታይ ውይይት አባል የነበረችው ግብፅ በአንፃሩ፣ መድረኩን ጥላ እንደወጣችና ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን የህዳሴ ግድብ ለማስቆም ያለመ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ ፊቷን ወደ ምዕራባውያኑ ሃያላን መንግስታት እንዳዞረች አይዘነጋም። በዚህም የአሜሪካ ፣ አለም ባንክና የአለም ገንዘብ ድርጅት በሆላም የአረብ ሊግን በር ብታንኳኳም፣አገራችን የተቀበለችው የአፍሪካ ህብረትን አደራዳሪነት ብቻ በመሆኑ ጥረቷ ፍሬ አልባ ሆኗል ፡፡
የአባይ ዉሃን የፍትሃዊና ምክነያታዊ አጠቃቀም ዲፕሎማሲ መቋጫ አልባ ያደረገው የካይሮ ተለዋዋጭ ሃሳብና የቀኝ ግዛት አቋም ላይ መቸከል ነው ፡፡ ይሄ ደግሞ የኢትዮጵያን ጉዞ የሚያስቆም ባይሆንም፣የካይሮ ፖለቲከኞች የግብፅ ህዝብን አፍ እያዘጉበት ነው ፡፡መፍትሄው ግድባችንን አጠናቅቆ ፣ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ፍሬ መልቀም ብቻ ነው፡፡