Connect with us

ግንቦት ሰባት-የዛሬ አስራ ስድስት አመት፤የዲሞክራሲያችን እንቁልልጭ የአንድ ጎረምሳ እድሜ!

ግንቦት ሰባት-የዛሬ አስራ ስድስት አመት፤የዲሞክራሲያችን እንቁልልጭ የአንድ ጎረምሳ እድሜ!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ግንቦት ሰባት-የዛሬ አስራ ስድስት አመት፤የዲሞክራሲያችን እንቁልልጭ የአንድ ጎረምሳ እድሜ!

ግንቦት ሰባት-የዛሬ አስራ ስድስት አመት፤የዲሞክራሲያችን እንቁልልጭ የአንድ ጎረምሳ እድሜ!

(ስናፍቅሽ አዲስ – ድሬቲዩብ)

ግንቦት ሰባት ለኢትዮጵያ ዝም ብሎ ቀን አይደለም፤ እንደውም የግንቦት ሃያ ማርከሻው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለአዲስ አበቤ ሰው ቀኑ ብዙ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ በቀጣፊ መንግስት አስራ አራት አመት መመራቱን ያወቀበት የታሪክ ክስተት ነው፡፡

ዲሞክራሲን ስንራብ በመረጥነው መተዳደርን ስንፈልግ የአንድ ጎረምሳ እድሜ አስቆጠርን ከአድዋ፣ ከዋግ፣ ከበለሳ፣ ከሞጣ፣ ከአሰላ፣ ከነቀምቴ፣ ከጉርሱም፣ ከአዳባ፣ ብቻ ከሀገሪቱ ገጠር ተጭኖ እየመጣ ሰፈራችን የሚወዳደረውን የማናቀውን ሰው በሚገባው ቋንቋ ያነጋገርንበት ቀን ነው፡፡

የዛሬ አስራ ስድስት አመት በዚህ ሰዓት ተሰልፈናል፡፡ ሀገር ከፋፋይ፣ ብሔር አጋጭ፣ ቋት መዝባሪን መንግስት ከጫንቃችን እናወርዳለን ብለን፡፡ የምንመርጠው የአካባቢያችንን ትልልቆች እንደሆነ የማንመርጠው መንግስት ገብቶታል፡፡ ይህ ቀን ለወያኔ መራሹ መንግስት መራር ነበር፤ በመጨረሻም የጠላው ደረሰበት፡፡

ግንቦት ሰባት ከፓርቲም ስምም ከምርጫ ቀንም በላይ ሌላ ትርጉም ያለው መገለጫ ነው፡፡ የህዝብን ፍላጎት ለመረዳት እንዲህ ያለው ቀን ብቻውን በቂ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ያ ረሃብ አልታገሰም፡፡ የሚፈልጉትን በነጻነት የመምረጥና በሚፈልጉት የመመራት ጉጉት ግንቦት ሰባት ቋምጦ እንደቀረ ነው፡፡

የምርጫ ማግስት ግጭቶች ብርቅ በማይሆኑባት አፍሪቃ ያልተመረጠው መንግስት አኩርፎ ቁጭ አላለም፡፡ ምርጫ ለዘለዓለም በኢትዮጵያ ምድር ፌዝ እንዲሆን አደረገ፡፡ መቶ ፐርሰንት ማሸነፍ የሚችልበትን ድራማ ተጫወተው፡፡ ተቋማት ፈረሱ፡፡ በመጨረሻም ራሱ ሀገር እጥላለሁ ያለው ወንበዴ ወደቀ፡፡

ግን ጠባሳው ከባድና አሁን እንኳን አልለቅ ብሎን ብመርጥ ባልመርጥ ምን አመጣለሁ ባይ እንድንሆን አደረገን፡፡ አሁንም መንግስት በካርድ አይወርድም የሚለውን ሀሳብ ይዘን ግራ በመጋባት ለዲሞክራሲያዊ ልምምድ አእምሯችንን እንዘጋ ዘንድ ምክንያት ሆነ፡፡ ኢህአዴግ ለዘረፈው ብር፣ ለአሳፈራት ሀገር፣ ለአወደመው ገንዘብ ሁሉ ተቆጥሮ ተብጠልጥሏል፡፡ እንዲህ ላለው የትውልድ የሞራል ጫናና በዲሞክራሲ ልምምድ መንግስት እቀይራለሁ የሚል መንፈስ እንዲሰበር ላደረገው ቆሻሻ ስራ ግን በምን ህግ እንደሚጠየቅ አላውቅም፡፡

የምርጫን እፍርትና ሽንፈትን ተከትሎ የሚፈጸም ነውርን በማስተማር በኩል እንደ ዝርፊያውና ሀገር ማውደሙ ለኢህአዴግ መገለጫ ብለን ልንወስድለት የምንችለው አንድ እሴቱ ነው፡፡ አዲስ አበባ ግን የቱ ጋር እንደቆመች በቅጡ ያሳየችበት የታሪክ ቀን ግንቦት ሰባት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነባት ሁሉ በምርጫ ውጤት የማፈር ብቻ ሳይሆን ዛሬ ድረስ የቂም መአት እንዲወርድባት ምክንያት ሆነ፡፡ 

የዘንድሮው ምርጫ ጉጉትም ግዴለሽነትም ታይቶበት መራጩ ተመዝግቦ ጨርሷል፡፡ ቀጣዮቹ የምርጫ ቅስቀሳዎችና ነባሮቹ ቁጭቶች የቱ ወገን ማንን እንደመረጠ ለማወቅ የምርጫውን ቀን እንጠብቃለን፡፡

የግንቦት ሰባት የኋላ ታሪክ ግን ቀኑ ዲሞክራሲን እንቁልልጭ የተባልንበት ጥሩም መጥፎም የታሪካችን ክስተት ሆኖ ይኖራል፡፡ በዚያ ወቅት የነበሩት ደማቅ የውድድርና ለመመረጥ የሚደረጉ የፍክክር መንፈሶች እስር መልካቸውን እስኪቀይረው ዲሞክራሲ ባህላችን ላይ ጫና ፈጥረው ነበር፡፡ ያ ጫና በጎ ጫና ሆኖ ሲታወስ ይኖራል፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top