ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ወረቀት የህትመት ሂደትንና የደህንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አስጎበኘ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች እና ሚዲያዎች የተወጣጣ የልኡካን ቡድን ወደደቡብ አፍሪካ በመላክ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመትን እንዲጎበኙ አደረገ።
በቦርዱ ከፍተኛ አመራር ፍቅሬ ገብረ ሕይወት ለተመራው ከፓርቲዎች እና ከሚዲያዎች ለተውጣጣው ልኡክ የድምፅ መስጫ ወረቀት የኅትመት ሂደቱን፣ የቴክኒክና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን በዝርዝር ማሳየት መቻሉ ተነግሯል።
ቦርዱ የፍትሐዊ አሠራሩ አንዱ ማሳያ አድርጎ ከሚወስደው የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተል መወሠኛ ሎተሪን በይፋ ካስጀመረበት ከመጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመቱ የተጀመረ ሲሆን፤ ይህንንም ሥራ ከሚያካሂዱት ሁለት የኅትመት ድርጅቶች አንዱ በሆነውና በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የሬን-ፎርም ኅትመት ማኅበር ከፓርቲዎች እና ከሚዲያዎች የተወጣጣ የታዛቢ ቡድን አባላት ጎብኝተውታል ተብሏል።
በጉብኝቱም የሥራ ሂደትና የኅትመቱ የደኅንነት አጠባበቁን ምን እንደሚመስል በኅትመት ኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ተሰጥቷል።
ጎብኝዎች ግልፅ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉትን ነገር በሥራ ኃላፊዎቹና በቦርዱ አመራር ፍቅሬ ገብረ ሕይወት አማካኝነት ማብራሪያ መሰቱን ተጠቅሷል።
የኅትመት ሂደቱ ምን እንደሚመስል፤ ከጥሬ ማቴሪያል ምርት አንሥቶ እስከ ኅትመት ሂደቱና የማሸግ ሥርዓቱ ድረስ ያለውን አጠቃላይ ሂደት የተመለከተ ጉብኝት መካሄዱ ተገልፇል።
ፓርቲዎቹም ከጉብኝቱ በኋላ ለብዙኃን መገናኛ በሰጡት አስተያየት፤ ባዩት ነገር መደሰታቸውን፤ ጉብኝቱም የቦርዱን ግልጽ አሠራር ማሳያ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፤ የጉብኝት አጋጣሚውም ፓርቲዎቹ ተቀራርበው ለመወያየት አጋጣሚን የፈጠረ እንደነበር ገልጸዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው ኅትመት የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመቱን 45 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን፤ ይህውም የደ/ብ/ብ/ክ፣ የአማራ ክልል፤ የሲዳማ ክልልና የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሣኔን ያካትታል።
ቀሪውና 55 በመቶ የሚሸፍነው የኅትመት ሥራ ዱባይ በሚገኘው አል-ጉህራር ማኅበር እየተከናወነ እንደሚገኝ የምርጫ ቦርድ በማህበራዊ ገጹ ይፋ አድርጓል ።
ለአራት ቀናት በቆየው ጉብኝትም የብልጽግና ፓርቲ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የህብር ኢትዮጵያ ተወካይ (ህብር)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው እና የሚዲያ አካላትም መሳተፋቸው መጠቀሱን ኢዜአ ዘግቧል።
(አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ)