ስለ ብፅዕ አቡነ ማቲያስ ፓስፖርት ጉዳይ
(ቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 135 ጥቅምት 2005 ዕትም የተወሰደ)
ሰሞኑን ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ዜግነት ጉዳይ የመከራከሪያ ነጥብ ሆኖ በማህበራዊ ሚዲያው መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ይህ ክርክር የዛሬ ስምንት ዓመት ወደ ፓትሪያርክነት ሲመጡ ጀምሮ የነበረ ስለመሆኑ የቁም ነገር መፅሔት የወቅቱ ዘገባ ያሳያልና እነሆ፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 5ኛ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት መለያታቸውን ተከትሎ ስድስተኛውን ፓትሪያርክ ቅዱስ ሲኖዶስ ለመምረጥ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ይሁንና ሂደቱ በቤተክርስቲያኒቱ ህገ ደንብ ብቻ ለማካሄድ የታሰበው እቅድ የመንግስት ሰዎች እጃቸውን በማስገባታቸው የተነሳ ከወዲሁ መስተጓል ጀምሯል፡፡
እንደ ህገ ደንቡ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡኑ ጳውሎስ ህልፈት በኋላ ዐቃቤ ፓትሪያርክ መርጦ ከ 40 እስከ 80 ቀናት ባለው ጊዜ አዲስ ፓትሪያርክ ምርጫ መከናወን ነበረበት፡፡ ይሁን እንጂ ሰሞኑን ተሰብስቦ የነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ የአዲስ ፓትሪያርክ ምርጫ ከመከናወኑ በፊት አዲስ የምርጫ ህግ መቅደም አለበት የሚል ሀሳብ ያላቸው ቀሳውስት ብቅ ብለዋል፡፡ ይህ በመንግስት ሰዎች የሚታገዘው ሀሳብ አዲሱ የምርጫ ህግ በአጭር ቀናት ተረቆ ለምልዓተ ጉባኤው እንዲቀርብ በማለት ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲወስን ቀርቧል፡፡
ከዚያስ? ‹የምርጫ ህጉ መሻሻል አለበት› በሚሉትና‹ የለም ባለው ምርጫው ይካሄድ› በሚሉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መሀከል የተነሳው ውዝግብ የራሱ እውነት ይዞ ታይቷል፡፡ ‹መሻሻል አለበት ህገ ደንቡ› የሚሉት ሊቃነ ጳጳሳት ‹በአቡነ ጳውሎስ አማካይነት የወጡ ጨቋኝ ህጎች መሻሻል አለባቸው› ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ‹መንግስት የራሱን ሰው አምጥቶ ሊያስቀምጥ ስለሆነ መሻሻል የለበትም› ብለው ነበር፡፡
ህጉ መሻሻል አለበት የለበትም የሚለው ውዝግብ ባለበት ሰዓት ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ቀጣዩ ፓትሪያርክ ማን ሊሆን ቢሆን ይሻላል? የሚለው ጉዳይ ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መሀከል አንድነት እንደሌለ መታየት ጀመረ፡፡ በዋናነት ግን የደቡብ ወሎ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አትናቲዎስና የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ብፅዕ አቡነ ፊሊጶስ ለቦታው በቀዳሚነት የታጩ ሆኑ፡፡ በሌላ በኩል የማህበረ ቅዱሳን ቀኝ እጅና ደጋፊ መሆናቸው የሚነገርላቸው የሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፅዕ አቡነ ሉቃስም ለቦታው ይገባቸዋል በሚል ድጋፍ ከሚያሰባስቡት ውስጥ ሆነው ወስጥ ውስጡን ቅስቀሳው ጦፈ፡፡
ውድድሩ በእነዚህ ጳጳሳት መሀከል እንደሚሆን እየተነገረ ባለበት ወቅት ሌላ አንድ እጩ ጳጳስ ለፓትሪያርክነት መታጨታቸው ተሰማ፡፡ እሳቸውም በወቅቱ የእየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፅዕ አቡነ ማቲያስ ነበሩ፡፡ አቡነ ማቲያስ ከዚህ በፊት ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ለፓትሪያርክነት ተወዳድረው የነበረ ሲሆን ለረዥም ዓመት ከኢትዮጵያ ውጪ የኖሩ አባት ናቸው፡፡
ያም ሆኖ የአቡነ ማቲያስን ፓርትሪያርክ መሆን የማይፈልጉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ማን ሊያስመርጣቸው እንደፈለገ ስለገባቸው እሳቸውን ከውድድር ውጪ ለማድረግ የተለያዩ ስልቶችን መጠቀም ጀመሩ፡፡ የመጀመሪያውና ዋናው ፓትሪያርክ እስከሚመረጥ ድረስ በሀላፊነት የሚቀመጥ አቃቤ መንበረ ፓትሪያርክ መመረጥ ስላለበት አቡነ ማቲያስን አቃቤ መንበረ ፓትሪያርክ አድርገው ለማስመረጥ ጥቆማ አካሄዱ፡፡ ምክንያቱም አቃቤ ፓትሪያርክ ሆኖ የተሰየመ ጳጳስ ለፓትሪያርክነት እንዳይወዳደር ህገ ደንቡ ይከለክላልና ነው፡፡
ይህንን አካሄድ ደጋፊዎቻቸው የተቀወሙተ ገና በጠዋቱ ሲሆን ተቃውሞው በድምፅ ይለይ ተብሎ ለአቃቤ መንበረ ፓትሪያርክነት ሳይመረጡ ይቀራሉ፡፡ ሌላው አቡነ ማቲያስን ማግለያ ስልት ተብሎ የተያዘው በማህበረ ቅዱሳን ሰዎች ጭምር ሲቀነቀን የነበረው ስልት ከስድስተኛው ፓትሪያርክ ምርጫ በፊት ለ20 ዓመታት ቤተክርስቲያኒቱን ለሁለት የተከፈለው ከስደተኛው ሲኖዶስ ጋር እርቅ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነበር፡፡
ይህንን ሀሳብ የሚገፉ ሰዎች እርቁ ከተፈፀመ አራተኛው ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዮስ በህይወት የሚገኙ ስለሆነ ያለፈውን ስህተት ለማረም እሳቸውን ወደ መንበሩ መመለስና ማስቀመጥ ይቻላል በሚል ነበር፡፡ ነገር ግን የእርቅ ሀሳቡን ኢህአዴግ ክፉኛ ስለተቃወመው ሀሳቡ ብዙም ነፍስ ሳይዘራ በእዛው ቀረ፡፡ ሶስተኛው ሙከራ የዋናው ፓትሪያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ሲመረጥ አስመራጭ ጳጳስ ሆነው እንዲሰሩ መጠቆምም ሌላው ሙከራ ነበር፤ አስመራጭ ኮሚቴ ሲመረጥም አቡነ ማቲያስ ሳይካተቱ ይቀራል፡፡
ሌላኛውና የመንግስትን ፍላጎት ማኮላሻ መንገድ ተደርጎ የተወሰደው አቡነ ማቲያስን ማግለያ ካርድ ከዜግነት ጋር የተያያዘው የቤተክርስቲያኒቱ ህገ ደንብ ነበር፡፡ አቡነ ማቲያስ በወቅቱ በሚታወቅ ሁኔታ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው የሀይማኖት አባት መሆናቸውን የተረዱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ይህቺን ካርድ በመምዘዝ ከውድድር ውጪ ሊያደርጓቸው ሲሞክሩ ቀደም ሲል የአቡነ ጳውሎስ ህገ ደንብ መሻሻል አለበት ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት በፓትሪያርክ ምርጫ ላይ ያለው ህገ ደንብ መሻሻል አለበት ብለው ሽንጣቸውን ገትረው መከራከር ጀመሩ፡፡
ህግ ደንቡ እንዳለ ከተቀበሉ በኋላ ቋንቋ፤ ዜግነትና ዕድሜን የተመለከቱ አንቀፆች እንዲጨመሩ/እንዲሻሻሉ ተደረገ፡፡ ዕድሜን በተመለከተ ከ50 ዓመት በላይ የሆነው(ምክንያቱ ደግሞ ገና 50 ዓመት ያልሞላቸው ወጣት ሊቃነ ጳጳሳት ወደ መንበሩ በመጠጋት ስለነበሩ)፤የቤተክርስቲያኒቱ የቅዳሴ ቋንቋ ከግዕዝ በተጨማሪ አንድ የውጪ ሀገር ቋንቋ የሚናገር እንዲሁም ዜግነትን በተመለከተ ‹ኢትዮጵያዊ የሆነ› በሚለው ላይ የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ከሆነ ያንን ‹ለመተው› ፍቃደኛ የሆነ፤ የሚል አንቀፅ ተጨምሮ ፀደቀ፡፡
ከዚህ በኋላ ሱሪው በማን ልክ ተለክቶ እንደተሰፋ ግልፅ እየሆነ መጣ፡፡ የእጩ ፓትሪያርክ ጥቆማ ሲካሄድም የመንግስትን ፍላጎት ያነገቡ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ማቲያስን ጠቆሙ፡፡ አሜሪካዊ ዜግነት እንዳላቸው የሚያውቁ ሊቃነ ጳጳሳት ሳይቀር ጥቆማው ሲካሄድ ከመንግስት ሰዎች ጋር ላለመጋጨት ሲሉ የዜግነት ጥያቄውን ሳያነሱ ምርጫው ተካሂዶ አቡነ ማቲያስ ተመረጡ፡፡
ከምርጫው በኋላ ግን ጉምጉምታው እየበረታ ‹አሜሪካዊ ፓትሪያርክ ኢህአዴግ አስመረጠ› የሚል ስሞታ እየጨመረ ሲመጣ ብፅዕነታቸው ፍርጥም ብለው ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ ለዚህም ማስረጃ ሲጠየቁ ከእየሩሳሌም ወደ አዲስ አበባ ለምርጫው ተጠርተው በገቡበት ወቅት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጣቸውን ደብዳቤ አቀረቡ፡፡ ደብዳቤው ብፅዕነታቸው አሜሪካዊ ዜግነታቸውን በፍቃደኝነት መመለሳቸውና ኢትዮጵያዊ ፖስፖርት እንደተሰጣቸው ያትታል፤ከዚህ በኋላ ቄሱም ዝም መፅሐፉም ዝም ሆነ፡፡
(ጥያቄው አሁን እንደ አዲስ ይነሳ እንጂ በወቅቱ ተዳፍኖ የቀረው የዜግነት ጉዳይ መሠረታዊ ጥያቄዎች መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ አንድ ሰው አሜሪካዊ ዜግነት ለማግኘት የሚሄድበት የህግ መስመር እንዳለ ሁሉ ዜግነቱንም ለመመለስ የሚሄድበት ህግ እንዳለ ይታወቃል፡፡ የአቡነ ማቲያስን አሜሪካዊ ዜግነት የኢትዮጵያ መንግስት መሻር ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ እንደተንጠለጠለ ይገኛል፡፡ በቅርቡም አቶ ጃዋር መሀመድ አሜሪካዊ ዜግነቴን ትቻለሁ ሲል የነበረውን ውዝግብ ልብ ይሏል፡፡)