Connect with us

ብሔሩንም ሃይማኖቱንም ለማይገባቸውና ሃላፊነት ለማይሰጣቸው ሰጥተን ሀገር አናናውጥ፤

ብሔሩንም ሃይማኖቱንም ለማይገባቸውና ሃላፊነት ለማይሰጣቸው ሰጥተን ሀገር አናናውጥ፤
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ብሔሩንም ሃይማኖቱንም ለማይገባቸውና ሃላፊነት ለማይሰጣቸው ሰጥተን ሀገር አናናውጥ፤

ብሔሩንም ሃይማኖቱንም ለማይገባቸውና ሃላፊነት ለማይሰጣቸው ሰጥተን ሀገር አናናውጥ፤

(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)

ሀገሩ እንደሆነ የደፋርና የተላላኪ ሆኗል፡፡ ተላላኪውና ደፋሩ መልኩን እየቀያየረ አክስሮ ሜዳ ሊያስቀረን በሺህ አጀንዳ ይመጣል፡፡ እኛ እኮ ቤታችንን ለአፍጥር ሰጥተን አፍጥር ወገን ቤት ገብተን አፍጥረን፣ ተጋምደን የኖርን ህዝቦች ነን፡፡ የአንዳችን ጥቃት የሌላችን እንደሆነ መማማል የማያስፈልገን አንድ ሆነን ያለ ልዩነት የምንኖር ህዝቦች ነን፡፡

እየሆነ ያለው ግን የሚያሳዝን ነው፡፡ ስፍራውን ሁሉ ለደፋር እየለቀቅን በሀገራችን ጉዳይ ባይተዋሮች ሆንን፡፡ ትልቁ እሴት እጃችንና ልባችን ውስጥ እያለ እኛ ግን እከሌ እንዲህ አለ በሚል ጎራ ለመለየት ተጣደፍን፡፡

ብሔራችንን ነጻ እናወጣችኋለን ለሚሉ የማንነት ተጠቂዎች ለቀን በብሔር እንታመሳለን፡፡ ከአእምሮ ህመም ነጻ ባልወጡ ነጻ አውጪዎች እጣ ፈንታችን እየተወሰነ ሞት ስደት መከራና ስቃይ በዛብን፡፡

ብሔሬን ሌላ ወስዶ እኔን ሆኖ በእኔ ጉዳይ እየወሰነ እኔ ሀሳብ ስሰጥ እንኳን አያገባህም የሚል ነጻ አውጪ መጣብን፡፡ ይሄንን የሚያግዝና ኢትዮጵያን ቆማ ማየት የማይፈልግ ሃይል የቻለውን እየደጎመ ሀገር ታማ ኑሮዋን ትገፋለች፡፡

አሁን ደግሞ በሃይማኖት ለመምጣት ጥረቱ ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ የተሳሳተ ሆኖ አያውቅም፣ ክርስቲያን ወገኖቻቸውን የሚጎዳ ጥያቄም አንስተው አያውቁም፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ተገን አድርጎ ቅጥረኛው ሀገር የሚያምሰው ግን በሃይማኖት ሽፋን ነው፡፡

ትናንት ድምጻችን ይሰማ ብለው ሲጮሁና ከዳር ዳር እምነታችን ጣልቃ አይገባበት ብለው የመብት ጥያቄ ሲያነሱ ከአፋኙ ጋር አብረው የቆሙ ሙስሊሞች መኖራቸውን ረስተዋል፡፡ ክርስቲያኑም ቢሆን ወያኔ ዘርን አምላክ አድርጋ ቤተ ክህነቱን ስታምስ ጳጳሳትን ስትደበድብ ገዳማትን ስታርስ አይዞሽ ይላት የነበረ ኦርቶዶክስ መኖሩን ረስቶታል፡፡

ዛሬ እኛን መስለው የራሳቸውን ሀሳብ እያራመዱ ያሉት ወገኖች በእምነት ስም ተስፋ አላት የምንላትን ሀገር ተስፋ ለማጨለም ግፋ ይላሉ፤ እኛ የት ነው የምንገፋው? እኛን ሆኖ ሆ የሚለው ማን ነው እሱ? ብለን አንጠይቅም፡፡

ከእኛ የወገነ ከመለሰን ጋር ሁሉ እየወገንን መከራ ላይ ወደቅን፡፡ እስቲ ጥያቄውን እንመዝን፤ እስቲ ያለ ግጭት ያለ ጩኽት ያለ መጠላላት ያለ ክፉ ቃል ሀሳቦቻችንን እንካፈል፤ እኛ እኮ አንድ ነን፡፡ ልዩነታችን ያለው ለልዩነታችን አበል በልተውና ተቀጥረው ብዙ ጎራ በሚያሰልፉን ጠላቶች ምክንያት ነው፡፡

አሁን ብሔሩን በእምነት አስደግፎ ኢትዮጵያ አበቃላት ለማለት ብዙ ጫጫታ እየሰማን ነው፡፡ ጫጫታውን ዝም አስብለን ከተደማመጥን ግን አንዳችን የሌላችን ዘብ ነን፡፡ ለሁሉም ሃይማኖት እኩል የማትሆን ሀገር ለየቱም ሃይማኖት እንደማትሆን ጤነኛ ሃይማኖተኛ በደንብ ያውቀዋል፡፡

ግን ደጋግመን ማሰብ አለብን፡፡ የጠበበን ግርግሩን የምናይበት ጊዜ መንፈስና ልቦና እንጂ አደባባይ አይደለም፡፡

በሁሉም ወገን ሆ ሲባል የሚንጫጫውና ከችግሩ በላይ የሚጎነው ሀሳብ ችግሩን እንዳንፈታ ብቻ ሳይሆን እንዳናውቀውም የሚያደርግን ግርግር ነው፡፡ ይሄንን ለማሸነፍ እንደ ህዝብ ሰከን ብለን ማሰብና ወዴት ነው የምንሄደው ማለት አለብን፡፡ ለፍትሐዊ ጥያቄዎች ሁሉ አንዳችን ከሌላችን ጎን መቆም አለብን፡፡

ፍትሐዊ ጥያቄዎች እንዲታፈኑ እና ጥያቄ እንዲነሳባቸው የሚያደርጉ ጠላቶቻችን ሁሉም ጎራ ቆመው ሊያባሉን ያሰቡ ናቸው፡፡ ከተደማመጥን የማይመለስ ጥያቄ የለም፡፡ ካልተደማመጥን ተያይዘን ገደል እንገባለን እንጂ መንገዱን አናገኘውም፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top