“በአማራ ክልል የተካሄዱ ሰልፎች ሰላማዊ ኾነው እንዲጠናቀቁ ላደረጉ ወጣቶች እና የክልሉ ሕዝብ ምስጋና አቀርባለሁ” አቶ አገኘሁ ተሻገር
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ወቅታዊ የክልሉን ሁኔታ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ ሕዝቡ እየደረሰበት ያለውን ጥቃት በሰላማዊ እና በሰለጠ መንገድ መግለጹ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተካሄዱት ሰልፎች ሰላማዊ እንደነበሩም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በባሕርዳር በዛሬው እለት የታየው ምልክት ልክ ያልሆነ እና ከዓላማው የተለየ መሆኑን ገልጸዋል። ድርጊቱ የሰልፉን ዓላማ ለማስቀየር ያለመ ነውም ብለዋል። በዚህም መሰል ሁኔታዎች አንዳይቀጥሉ የክልሉ መንግሥት ሕግ ለማስከበር እንደሚገደድ በሰጡት መግለጫ አስገንዝበዋል።
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ላይ ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል ያሉት አቶ አገኘሁ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በወለጋና በመተከል አካባቢዎች ሕዝባችን እረፍት የሚነሳ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል ብለዋል። በተለይ ኦነግ ሸኔ ለዚህ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድም ገልጸዋል።
አቶ አገኘሁ የአማራ ሕዝብን ሞትና መፈናቀል ለማስቆም ጥረት እየተደረገ ነው፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋርም በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል።
የፌዴራል የጸጥታ ኀይልም በጉዳዩ ላይ መስዋት እየከፈለ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ሰሞኑን በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰው ጥፋት ጥቃት ፈፃሚዎችን ለሕግ ለማቅረብ ከፌዴራል የጸጥታ ኀይል ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በጥቃቱ የመንግሥት መዋቅር ጭምር ተሳትፏል ብለዋል። “እኛም መዋቅራችንን እየፈተሽን ነው፣ ይህ ሁሉ ውድመት ሲከሰት የጸጥታ ኀይላችን የት ነበር፣ የመረጃ እና የደኀንነት መዋቅራችን የት ነበር የሚለውን እያጣራን ነው” ብለዋል በሰጡት መግለጫ።
“ሕብረተሰቡም ይህን ለመቃወም ሞት በቃ ለማለት ሳር አንኳን ሳይረግጥ በሰላም ሀሳቡን መግለጹ ተቀባይነት ያለው ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የሰለፉን ዓላማ አንዳንድ ኀይሎች ለመጥለፍ ሙከራ አድርገው ነበር ብለዋል። በዚህም ሕዝብን ለማለያየት የወጣው መልእክት የአማራን ሕዝብ እና የሰልፉን ዓላማ እንደማይወክል ተናግረዋል። ዛሬ በተካሄዱት ሰልፎችም ሕዝቡ እራሱ ይህንን አውግዟል ብለዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንን አንዲረዳ እንፈልጋለን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም የምናደርገውን ትግል በማገዝ ከጎናችን አንዲቆም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ መንግሥትም በተለያየ አቅጣጫ ተወጥሮ ሳለ ችግሮችን ለማባባስ ጥረት የሚያደርጉ አካላት ላይ ሕግ ለማስከበር እንደሚገደድ አስገንዝበዋል። (አሚኮ)