እያረምን ወይስ እያበድን እንሂድ
(ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት)
ገበሬው ለሙግት ወደ ሸንጎ ሄዶ ሲመጣ የገዛ ወዳጆቹ የዘራውን እህል ሳያርሙ፣ ሳይኮተኩቱ ጠበቁት፡፡ ማሳውን እያየ ያብዳል፡፡ እንዴት እንደዚህ ይደረጋል? ይህን ያደረጉት እነ እንቶኔ ናቸው? ይህን ያደረጉት እኔን ሊጎዱ ነው? ድሮም እነርሱ አይወዱኝም ነበር፤ በቃ የሰው ነገር መጨረሻው እንደዚህ ሆነ ማለት ነው? በቃ የእርሻዬ ነገር አበቃለት ማለት ነው? እያለ ፀጉሩን እየነጨ ያብዳል፡፡
አንድ ሽማግሌ ከሩቅ አይተዉት መጡ፡፡ እየዛበረ የሚናገረውን ሰሙ፡፡ ከዚያም ‹እባክህ ረጋ በል› አሉት፡፡ ‹ምን ረጋ እላለሁ፤ እንዲህ ሲሆን እያዩት፤ ከዚህ በኋላ ምን ተስፋ አለኝ› እያለ ሲጮኽ ሽማግሌው ሰሙትና ‹ወዳጄ ይህ ሁሉ ቢሆንም፣ እያረምን እንጂ እያበድን መሄድ አለብን እንዴ› አሉት አሉ፡፡
ኢትዮጵያም እንዲህ ነው እየሆነች ያለችው፡፡ አንዱ ስንዴ፣ ሌላው እንክርዳድ ይዘራል፤ አንዱ ያቀናውን ሌላው ሊያጣምመው ይተጋል፡፡ በዚህ ሲደፈን በዚያ ይቦተረፋል፤ ራስ ሲነቃ እግ ይጎተታል፤ ብዙዎቻችን እንደዚያ ገበሬ የምናየውና የምንሰማው ለዕብደት እየዳረገን ነው፡፡ ማበድ ግን ሀገር አያቀናም፡፡ መቆጨት እንጂ መናደድ መፍትሔ አያመጣም፡፡ አበቃ፣ አለቀ፣ ደቀቀ፣ ሞተ ተቀበረ፣ ሄደ፣ አከተመ፤ ነጠፈ፣ ተሟጠጠ እያሉ ማልቀስ ነገሩን አይቀይረውም፡፡
አርበኞቻችን ሀገራችንን ከጣልያን ቀንበር ሊያላቅቁ ላይ ታች ሲሉ አያሌ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ገጥመዋቸዋል፡፡ የንጉሡ መሄድ፣ የአንዳንድ ታዋቂ ሰዎች ከጣልያን ጋር ማበር፤ ሌላው ቀርቶ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ ከጣልያን ጎን መቆማቸው፤ ለገንዘብና ለሹመት ሲል መረጃ እየሰጠ የሚሾልከው ባንዳ፤ በእነርሱ ላይ የሚወረወረው ፕሮፓጋንዳ፤ ስንቅና ትጥቅ ሲያልቅበት ተስፋ የሚቆርጠው ጭፍራ፤ ጣልያን እያሸነፈ ነው እያለ የሚቦተርፈው ወሬ በጉንጩ፤ የአንዳንድ ጀግና ዐርበኞች በጊዜ መሠዋት መክፈል፤ መንገዱን ረዥም ትግሉን መራራ አድርጎባቸው ነበር፡፡
የሀገር ነጻነት እንኳንስ ለማየት ለመስማት የሚቀርብ አይመስልም ነበር፡፡ ዓለም በሙሉ ከጣልያን ጋር ያበረ ነበር የሚመስለው፡፡ ንጉሡ በዓለም ማኅበር ያቀረቡትን ተማጽኖ ሊሰማ የወደደ አልነበረም፡፡ እየዋለ እያደረ ሲሄድ ደግሞ ነገሩ ሁሉ የተቆረጠና ያለቀ ይመስል ነበር፡፡
ያንን የመከራ ዘመን የተሻገርነው ማረም እንጂ ማበድ እንደማያዋጣ በገባቸው ዐርበኞች ትከሻ ነው፡፡ መቼምና ምንም ቢሆን የኢትዮጵያ ነጻነት የማይቀር እውነት መሆኑ ገብቷቸው፣ ከሚያጋጥማቸው ፈተና ይልቅ የሚገኙትን ድል በሚያስቡ ዐርበኞች ነው፡፡ አንድ ጥግ ይዞ ከመቆዘምና ፀጉር ከመንጨት ይልቅ ወደ መፍትሔው የሚደርስ አንዳች ነገር ማድረግ የተሻለ መሆኑን በተረዱ ዐርበኞች ክንድ ነው የተሻገርነው፡፡
የዐርበኞች ትግል ከተናጠል ወደ ኅብረት፣ ከኅብረት ወደ ትብብር፣ ከትብብር ወደ ግንባር እያደገ መጣ፡፡ በመጀመሪያው ዓመት የነበሩትን ነገሮች እያረሙ፤ የተሻለም መንገድ እየተለሙ ተጓዙ፡፡ ሌሎች በመቶ ሃምሳ ዓመት ያልገፉትን ቅኝ ገዥ እነርሱ በአምስት ዓመት አሰናበቱት፡፡
እገሌ እንዲህ አለ፤ እዚህ ቦታ እንዲህ ተዘፈነ፤ እገሌ ለጣልያን ገባ፤ እገሌም ከዐርበኞች ከዳ፤ እገሌ ደግሞ ወደ ዐርበኞች መጣ፤ እነ እገሌ ዐርበኞችን ደምስሰን ሀገሪቱን እንቆጣጠራለን አሉ፤ እነ እገሌም በመሣሪያ ኃይል ተደራጅተው ሊዘምቱብን ነው፤ የሚለውን ሐሞት አፍሳሽ ወሬ መስማት ተው፡፡
የማይሠሩትን ትተው ከሚሠሩት ጋር ብቻ ለመተባባር፤ ስለ ጠላት ከማሰብ ስለ ወገን ብርታትና ጥንካሬ ለማሰብ፤ ከማበድ እያረሙ ለመሄድ በመቁረጣቸው ከ1930 ዓ.ም. በኋላ የዐርበኞች ትግል እየተጠናከረና መልክ እየያዘ መጣ፡፡ የጸሎት ዐርበኞችና የጦር ዐርበኞች ተባብረው ባደረጉትም ትግል ኢትዮጵያ ቀንበሯን ሰበረች፡፡
ዛሬም የሚያስፈልገን እንደዚያ ይመስለኛል፡፡ በትንሽ በትልቁ በማለቃቀስና በማበድ ጉልበታችንን ሁሉ ለልቅሶና ለዕብደት ከምናውለው፤ ስሕተቱን እያረምን፤ ሰውን እያተረፍን መጓዝ ነው ያለብን፡፡ መሬቱ ላይ የበቀለ አረም ካለ አረሙን እናርማለን፡፡ መሬቱን ግን እንፈልገዋለን፡፡ ዛሬ አረም አበቀለ ማለት ለአረም የተፈጠረ መሬት ነው ማለት አይደለም፡፡
እነ እገሌ እንዲህ አደረጉ፣ እንዲህ ሆኑ፣ እንዲህ አሉ እያልን የተራረፈ ወሬ እየለቃቀምን የተጣለልን የአጀንዳ ፍርፋሪ እያነሣን ልባችንን አናድክመው፡፡ በራሳችን ዕቅድ ወደምንፈልገው ዓላማ እንሂድ፡፡ ኢትዮጵያን መድረስ ወዳለባት ሠገነት ለማድረስ የማንም ቡራኬና ፈቃድ አያስፈልገንም፡፡ ‹እህ›ም ተባለ ‹አሃ› መንገዳችንን አይለውጠውም፡፡ እያረምን እንጂ እያበድን አንሄድም፡፡