አማራን ሌላው የሚገድለው አንሶ ለምን በትርምስና በኢኮኖሚ ትገድሉታላችሁ?
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ለአማራ ብሎ አማራን መግደል። ሰላም መንሳትና ማስጨነቅ ምን የሚሉት ትግል ነው? ለአማራ ህዝብ ብሎ በውክልና የሚሞት ልዩ ኃይልን ምን እንዲከፍል ተፈልጎ ነው? ልዩ ኃይሉ ሰላም ለማስፈን ተበተኑ ሲል እሺ ማለት የሚደማመጥ ኃይል መሆን ነው። በጥቂት ከንቱዎች ሳቢያ ይሄ ትሁትና ጀግና ህዝብስ ስለምን አይደማመጥም ይባላል?
በአማራ ላይ በየቦታው የሚደርሰው ሰቀቀን ሞት ስደትና እልቂት አማራው የት እፎይ ብሎ ይኑር አስብሎናል። አማራው አማራ ክልል ሳይቀር ስቃይ ላይ ነው። በሌሎች ከተማው ይወድማል በጅምላ ይሞታል። በራሱ ልጆች ስልት አልባ ትግል ፍዳውን ይበላል።
ሰሞኑን የህዝቡ ቅሬታ በየከተሞቹ ጎዳናዎች ታይቷል። አብንን ከአማራ ብልፅግና ጠላት ለማድረግ የሰራው ማን ነው? ይሄን ዞሮ ማሰብ አልተቻለም። ሰልፉን ማን መራው? ማንም አያውቅም። የህዝብ ብሶት ብቻ በሚል ሰልፍን ያኽል ነገር ያለ መሪና አስተባባሪ በየቀኑ ማድረግ ውጤቱ ምንድን ነው?
ዛሬ ባህር ዳር ስራ ማቆም አድማ ተደርጓል።
ማን ነው ጠሪው? ስንት ቀን? ምን ውጤት ለማምጣት? ደጋግሞ ማሰቡ ይጠቅማል። ኮቪድ የገደለው ክልል ነው። የጁንታው ጦርነት ኪሱንም ድባቡንም ገድሎታል። በዚህ ላይ ነዋሪውን የሚያደቅ ጠሪው የማይታወቅ የስራ ማቆም አድማ ማድረግ ግቡስ ምንድን ነው? ጠላት ከገደለው የተረፈውን በችግር ለመግደል ያሰበ ካልሆነስ ምን ይረባል?
አማራ ክልልን የትርምስ ስቃይና ሰላም የለሽ ቀጠና ለማድረግ የተደገሰው ድግስ እንዴት እንደሚከሽፍ ማሰብ እንጂ ለአማራ ብሎ ጁንታው ለባህር ዳር የደገሰውን ማድመቅ አይጠቅመንም። የአማራ ህዝብ ህልውና በብዙ አቅጣጫ ተወጥሯል ችግሩን የሚመጥን የመፍትሔ ቡድን ይሻል።
ስራ የሌለው ሰው ስራ ማቆም አድማ ሲጠራ ሆ ብሎ መተግበር ለጥፋት ቅጥረኛ መገዛት ነው። ትግል በባቢሎን ቋንቋ ያከስራል። የአማራ ብልፅግና ተወደደም ተጠላም የክልሉ መሪ ነው። ክልሉ የሚናቅ መንግሥት እንዲኖረው ማድረግ ብልጠትም አማራን መውደድም አይደለም። አማራ ባልተግባባ ፖለቲካ እንዲባትል አድርጎ አማራን መታደግ አይቻልም።
የባህር ዳር ጎዳና ለምን ድንጋይ ተኮለኮለበት? ለምን ደሃ ስራ ውሎ እንዳይገባ ተፈለገ? ባህር ዳር ከመቀሌ እንድትከፋ የፈለገው ማን ነው? የባህር ዳር ወጣት ጠላት የፈለገውን እንዲያደርግ መሳሪያ ሆነ። አማራ በገዛ መዲናው እንቅልፍ እንዲያጣ መደረጉ ያማል።
አሁንም ነቅቶ መጠበቅ ቀሪውን ጨለማ ይገፈዋል። በገዛ መንደሩም ሰላምን አይሻም ለሚሉ ቧልተኞች ቅጥረኞች ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጥሩ ማድረግ ያስፈልጋል። አማራ ልዩ ኃይል ላይ ድንጋይ መወርወር ኦነግ ሸኔ ካደረገው ቢከፋ እንጂ አያንስም።
አላበቃም። አማራ መሞት የለበትም ሀገር መፍረስም የለበትም። ሁለቱ ምንም አይቃረኑም ከስካርና ከዓላማ ቢስነት ያልወጣ አርበኛ እንዲመራ ማድረግ ውጤቱ ይከፋል። ባህር ዳርን ያመሳችሁት አማራ በሚያሳዝን ሁኔታ አንገቱን ሳይደፋ እንዳይውል ማድረጋችሁን እወቁት። ሰላም በማጣት ለሞተ የሚታዘነው የሟች ወገንን ሰላም በመንሳት አይደለም።