“ኑና ተመዝገቡ” እያሉ “የምርጫ ካርድ አልቋል” ምንድን ነው?
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ይህ በአዲስ አበባ የሆነ እውነት ነው፡፡ አንድ ቦታ ሳይሆን ተደጋግሞ ያጋጠመ ችግር መሆኑ ለጥርጣሬ ይጋብዛል፡፡ እርግጥ ነው የወይዘሪት ብርቱካን ምርጫ ቦርድ በቅልውጥና አይታማም፤ ግን የማያስተማምን ነገር ደግሞ ማየት ጀምረናል፡፡
ዜጎች የምርጫ ካርድ አልወሰዱም ብሎ ሌት ተቀን የሚቀሰቅሰው ምርጫ ቦርድ በሚዲያ ሌላ ምርጫ ጣቢያ ሌላ ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ ምርጫ ጣቢያ ሄደው ካርድ አልቋል የተባሉ ሰዎች ቅሬታቸውን በሚዲያ ጭምር አቅርበዋል፡፡ አዲስ አበባ የጸጥታ ችግር የለም፤ አስፈላጊውን ቁሳቁስ ለማንቀሳቀስና ምርጫ ጣቢያ ለማድረስ የሚያስቸግረው ምን እንደሆነም ግልጽ አይደለም፡፡ ግን ካርድ አልቋል ብሎ ሊመዘገብ የመጣውን መመለሱ ለሀሜት ይዳርጋል፡፡
አንዳንድ ቦታ አልቋል ብለው የሚመልሱትና አልቋል ካሉ በኋላ ለፈለጉት የሚሰጡበት አሰራር መኖሩ ሀሜት አስነስቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ ሰፊ ጥንቃቄ ጥቆማ የመቀበል ብቃትና ችግርን የማረም ስልት ያስፈልገዋል፡፡ እርግጥ አንድ ምርጫ ጣቢያ አንድ ሺህ አምስት መቶ ሰው የሚያስተናግድ ነው። ሲሞላስ? ብሎ ማሰብ ይኼንን አስልቶ አስቀድሞ ጎኑ ምርጫ ጣቢያ ማቆም ያስፈልገዋል። ምርጫ ጣቢያችን ሞልቷል ጣቢያ ፈልነህ ካርድ ውሰድ ግን በቅስቀሳ የመጣውን ቢቀርስ ያስብላል።
ፓርቲዎችም ደጋፊዎቻቸውን ሂዱና ለመምረጥ ተመዝገቡ ማለት ብቻ ሳይሆን ምርጫ ጣቢያ ያለውን ሁኔታ ተከታትሎ ለምርጫ ቦርድ የመጠቆምና ነውርም ካለ የማጋለጥ ስራ መስራት አለባቸው፡፡
ቀኑ እያለቀ ነው፡፡ ምርጫ ካርድ አልቋል ተብሎ ያልተመዘገበ ሰው እዚህም እዚያም ቅሬታው ሲሰማ ሰንብቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተቀመጠው ጊዜ ገደብ አለቀ ብሎ መደምደም ጀርባ መጣናት ያለበት ደባ ስለመያዙ የሚነግረን ነገር አለ፡፡
ብልጽግና የኢህአዴግ በኩር ልጅ ነው፡፡ ኮሮጆ መገልበጥ አበሳ እንደሚሆንበት በተረዳበት አዲስ አበባ የቀበሌ መታወቂያ አድሏል ሲባልና ሲታማ ከርሟል፡፡ ማድረግ አለማድረጉ በሀገራችን ደንብ ፍትህ እስከ ጥግ ተግባራዊ ስለማይሆን ሀሜቱ ከእውነት አልለይ ብሎናልና ቁርጥ ያለ ነገር ማለቱ ይከብዳል፡፡ በዚህ ስሜት ግን የከተማዋ ነዋሪ ካርድ አልቋል እየተባለ በተጣበበ ጊዜና ኑሮ ተመላልሶ ተስፋ እንዲቆርጥና የምን ምርጫ እንዲል ማድረግ አይገባም፡፡
ምርጫ ጣቢያዎች ተክለ ቁመናቸው ዓላማቸውና እየሰሩ ያሉትን ስራ መከታተል የጎደለውን መሙላት ያለ እናቴ መቀነት ከመደናቀፍ መዳን ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ያለ አሰራር ምርጫውን ምን ይዘትና መልክ እንደሚኖረው የሚናገር አንድ እድል ነው፡፡
ተጨማሪ የምዝገባ ቀናት ማራዘም አስፈላጊ ከሆነ ማራዘሙና መራጩ ተመዝግቦ እንዲጨርስ ማድረጉ የግድ ይመስለኛል፡፡ ምርጫ ጣቢያ ሄዶ ካርድ አልቋል በተባለ የመራጭ ፍላጎት ላይ ቀኑ አልቋል ብሎ ውሃ መቸለስ ኢ ዲሞክራሲያዊ ነው፡፡
ከዚያ ቀድሞ ቢያንስ አዲስ አበባ ለምርጫ ቁሳቁሱ መጋዘን ቅርብ ሆና ምርጫ ተመዝጋቢውን ቁሳቁሱ አልቋል ብሎ እንዲሰለቸው ማድረግ ልክ አይደለም፡፡ ምርጫ ቦርድ ጠዋት ማታ ኑና ተመዝገቡ፣ የሚፈልጉትን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥ መሰልጠን ነው፡፡ የሀገር ጉዳይ ችላ አይባልም እያለ ቀስቅሶ ምርጫ ጣቢያ ሲደረስ ያለምንም ስራ መመለስ ከሆነ ያስቸግራል፡፡
እንዳናማው የሚያደርግ ምርጫ ቦርድ ቢኖረንም እንድንፈራው የሚያስገድድ ምርጫ ጣቢያዎችን መዘርጋቱን መደበቅ የለብንም፡፡ በጊዜ ካልታረመ የምርጫው ቀን ሌላ ተአምር ስላለማምጣቱ እርግጠኛም አይደለንም፡፡
ምርጫ የስልጣኔ መገለጫ ነው፡፡ ይሄ ምርጫ አንድ ደረጃ ከፍ ብለን ስለ ዲሞክራሲና ነጻነት የምናስብበት ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ የሚያደበዝዝ የቱም ምክንያት በወቅቱ ቢቀረፍ መልካም ነው፡፡