Connect with us

ከአባይ ወንዛወንዙ እስከ ደሞ በአባይ 

ከአባይ ወንዛወንዙ እስከ ደሞ በአባይ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ከአባይ ወንዛወንዙ እስከ ደሞ በአባይ 

ከአባይ ወንዛወንዙ እስከ ደሞ በአባይ 

          (ክፍል ሦስትና የመጨረሻው)

 (እስክንድር ከበደ ~ ድሬቲዩብ)

የሙዚቃ  ደራሲያን ጥበባቸውን ለማህበራዊና ለፖለቲካዊ  ፍትህ መጓደልን ለመቀየር መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ ሙዚቃቸው ውስጥ የሚያስተላልፉት መልእክት ኃያል በመሆኑ  የህዝባቸውን እይታዎች   በሚስብና ውብ ጥበብ ይገልጹታል፡፡ ሙዚቃና ፖለቲካ የሚገናኙበት አማካይ ነጥብ ወደ ጎን ትተን  ወደ ሦስቱ የአባይ ዘፈኖች ቅኝት እንዝለቅ፡፡

የዘፈን ግጥሞቹንና የዜማ ቅላጼ ማወዳደሩን ለጊዜ ትተን ፤አባይን በዘፈኑበት ውስጥ ምን ነገሩንʔ ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ ቢያንስ የዘፈኑበት ጊዜና አውድ ስለሚለያይ የዘፈኖቹን ሚዛንና ያነሱት ጉዳይም ልዩነት አላቸው፡፡ እንደ አንድ የልብወለድ ድርሰት መቼታቸውና የተቀዱበት የስሜት  ጉርጓዶች በሦስት ዘመን ቀንብቦ መተንተን ይቻላል፡፡ 

የጂጂ ”አባይ” የሕዳሴ ግድብ  ውዝግብ ከመነሳቱ አመታት ይቀድማል፡፡ ጂጂ ግድቡ  ከነመፈጠሩም በማታውቅበት ዘመን ያዜመችው ውብ ዘፈን ነው፡፡ የጋሽ አበራ ሞላ ” የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና” ብሎ የሚቀነቅነው የአባይ ዘፈን የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ፤የሶስቱ ሀገራት ድርድር ሄድ መለስ በሚልበት ዘመን ነው፡፡ የቴዲ አፍሮ ”ደሞ በአባይ” (ከሞከሩንማ) ከርእሱ ጀምሮ የቁጣ ድምጸት ያለው  የአባይ ዘፈን  የግብጽ መሪዎች  ኢትዮጵያን ደጋግመው በሚያስፈራሩበት የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ዘመን  ነው፡፡

ጂጂ ”የሀገር ጸጋ ..የሀገር ልብስ” የምትለው ወንዙ ፤ በረሃ ሲሳይ መሆኑን አራት ጊዜ ደጋግማ አጽንኦት ትሰጠዋለች፡፡  ”አባይ ወንዛወንዙ፤ብዙ ነው መዘዙ” ብላ   አንድ ውልአልባ መዘዝ እንዳለው ፤ብትነካው የሚነኩ መኖራቸውን ታዜምለች፡፡ በዚህ ዘፈን ውስጥ ጂጂ ”ብነካው ተነኩ ” ስትለን ሀገር ሆና ምትነግረን ይመስለናል፡፡ 

ብነካው ተነኩ፤ አንቀጠቀጣቸው

መሆንህን ሳላውቅ፤ ስጋና ደማቸው

የሚበሉት ውሃ ፤የሚጠጡት ውሃ

በዚህ የጥበብ  ስራዋ ሁለት አንጓዎች  የአባይ  ወንዝ ገጽታ ትጭርብናለች፡፡ የዘፈኑ የላይኛው አንጓ ውበቱን፣ቁንጅናውን ፣የሀገር ግርማ ሞገስና የሀገር ልብስ መሆኑን  ከላይ ከላይ አሳይታን ፤ከታችኛው አንጓው ከመራር ሀቅ ጋር ታጋፍጠናለች፡፡ ወንዙን መብልም ሆነ መጠጣቸው አድርገው አትንኩት የሚሉ ፤ ኢትዮጵያ ግን መራብ፤መጠማቷ የማይገባቸው እንዳሉ ሳትነግረን ይገባናል፡፡

የጂጂ ”አባይ” ዘፈን ወንዙን  ግርማ ሞገሱን ፤ የሀገር ጸጋ መሆኑን ያወሳል፡፡ ጂጂ ወንዙን ስትጠራ ” አባ ..ይ”  ዘለግ አድርጋ ስታወደስው ”አባ ” የሚለው በውስጣችን ተሰንቅሮ ይቀራል፡፡  ”አባ..ይ” የሚወዱትን አባት አቆላምጦ እንደመጥራት ያለ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ጂጂ በቃላት ብቻ ሳይሆን ከፍ ዝቅ በሚል ቅላጼ መልእክቷን ታስታልፋለች፡፡

ጋሽ አበራ ሞላ ”አባይ” ዘፈኑ ባለፉት አስር አመታት ውስጥ ”ህዳሴ ግድብ” መጀመሩን ተከትሎ መሆኑን ከይዘቱ ማጤን ይቻላል፡፡ ” የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና…የአፍሪካ ልጆች መጡ ” ብሎ ወንዙን ከፍጥረቱ ጀምሮ ልክ እንደ ሰው አካል ዘርግቶ ፍሰቱን ከሜዲትራኒያ ….ካይሮ..ካርቱም አድርጎ ያቀነቅናል፡፡  ጂጂ” አባይ ወንዛ ወንዙ ..ብዙ ነው መዘዙ ” ብላ እንደዋዛ የምታልፈውን ጋሽ አበራ ሞላ ” ዘጠኝ ሞት መጣ ቢሉ አንዱን ግባ በለው…” እያለ  በወንዙ  የፍርሃትም ፤ የመጣው ይምጣ መንፈስ ያዜማል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ካይሮ በአባይ ላይ ያለውን የውሃ ፖለቲካ እያጦዘችው በፊት ለፊት በጠረጴዛ ድርድር ፤ በእጅ አዙር ”ዋ !” እያለች  አንዲት ጠብታ ከወንዙ የነካ  አካባቢው ይበጠበጣል እያለች አለምን ዞራ ፤በአሜሪካ ኢትዮጵያን የምታስፈራራበት ብሎም ማአቀብ ለማስጣል ደፋ የምትልበት ወቅት ደረሰ፡፡ የመጀመሪያው ሙሌት ሊካሄድ መዳረሻ ላይ የቴዲ አፍሮ ” ደሞ በአባይ” (ከሞከሩንማ) የሚል ዘፈን እንደሚያወጣ ተሰማ፡፡  በድንገት የዘፋኝ ሀጫሉ ሁዴሳ መገደል ተከትሎ ፤ የተፈጠረውን ግርግርና ሀገራዊ ሀዘን በኋላ ዘፈኑ እንዲወጣ ሆነ፡፡የቴዲ ”ደሞ አባይ”

”ደሞ በአባይ” የቴዲ አፍሮ ዘፈን ፤ ከጂጂና ጋሽ አበራ ሞላ የአባይ ዘፈኖች ይለያል፡፡ የቴዲ ዘፈን የግጥም  ይዘትና ዜማ በጦርነት ዋዜማ  የተለቀቀ ”ሽለላ ”  ይመስላል፡፡ የቴዲ አፍሮ  ”ደሞ በአባይ” (ከሞከሩንም)  የግብጽ ሞገደኛ አካሄድ  አስቆጥቶት እንደ ጥበበኛ ለሀገሩ በሙያው የተሰለፈበት ነው፡፡

” ደሞ በአባይ ድርድር

  ደሞ በአባይ

  ማን ዝም ይላል ሆኖ ዜጋ

  ደሞ በአባይ

  አባይ…አባይ

”ደሞ በአባይ ”  ያኔ ቢዘፈንም ለዛሬም እንደሚሰራ የሚገባን  የሀገራችን የውስጥ ችግሮች በካይሮና በካርቱም ሴራ የተባባሰበት ፤ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ  በትእቢት ”ከአባይ ውሃ አንድ ጠብታ ብትነኩ ኢትዮጵያም ሆነ ቀጠናው ላይ መከራ ይደርሳል በማለት በጦር መሳሪያ ጋጋታና የወታደር ብዛት እያስፈራሩ ባለበት ዘመን ነው፡፡

አባይ የግሌን ፤ባልኩኝ ለጋራ

ካቃራት ምስር፤ግፍን ሳትፈራ

የተቆጣ እንደው፤ፍቅር ታግሶ

የሚባላ እሳት፤ይሆናል ብሶ

ይህ  የቴዲ አፍሮ ዘፈን ”ከእንግዲህ አይኖርም ነገር ማለሳለስ ” በሚል  ”ፍቅር ”  ብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ ህዝብ  ብዙ መታገሱን እሱ ምስር ለሚላት ግብጽ  ፡፡

አባይ ለጋሱ ፤ግብጽን አርሶ

አገሬን ባለ፤ልይ ተመልሶ

ብሎ አሻፈረኝ፤ለሳበ ቃታ

እኔን አያድርገኝ፤የነካኝ ለታ

ሳንጃው ጸብ አይመርጥም

ይሁን ይበጅ ለኔም ለእሱዋም

ብዬ እንጂ  ሯ…ሯ..ሯ

ማንንም አልፈራ

የቴዲ አፍሮ  የጥንት ቀረርቶና ሽለላ ከሬጌ ምት ጋር አዋህዶ በአርበኝነት ይዘፍናል፡፡  ከቅኝ ግዛት ነጻ  በመውጣት  የመጨረሻው  እንደሆነች የሚነገርላት ዙምባቤ   እ.ኤ.አ በ1979  የነጻነት ቀን   አዲሷ ዙምባቤ የተነፈሰችው የመጀመሪያ አረፍተ ነገር ” ክቡራትና ክቡራን ቦብ ማርሊና ዘዌለር ” እና ለነጻነቷ ቦብ  Zimbabwe  የሚለውን ከ  Survival አልበም የመጀመሪያውን ስንኝ እንዲህ ሲል ዘፈነ

Every man gotta right to decide his own destiny,

And in this Judgment there is no partiality.

So arm in arms, with arms, we’ll fight this little struggle,

‘Cause that’s the only way we can overcome our little trouble. 

ቦብ ማርሊ በሚነዘር የሙዚቃ ቅላጼ እውነትም የዘፈነው ስለአፍሪካ በተለይ ስለ ዙምባቤ ህልውና ነበር፡፡ ቴዲ አፍሮም ” ደሞ አባይ” የኢትዮጵያን ሽለላ ከሬጌው ንጉስ ስልተምት ጋር አዋህዶ ሲዘፍነው ኢትዮጵያ ዳግም አደዋ ተብሎ የሚቆጠረውን  የህዳሴ ግድብ  በውጫሌ መሰል  ውል  እንደማትገባ ለጠላትም፤ ለወዳጅ ያወጀበት ዘፈኑ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህቺ ሀገር ኢትዮጵያ ስለሆነች!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top