Connect with us

የሰው ነፍስ ዜሮ ድምር ጨዋታ (Zero Sum Game)

የሰው ነፍስ ዜሮ ድምር ጨዋታ (Zero Sum Game)
ዶ/ር ሀይለመስቀል ሀይለማርቆስ

ነፃ ሃሳብ

የሰው ነፍስ ዜሮ ድምር ጨዋታ (Zero Sum Game)

የሰው ነፍስ ዜሮ ድምር ጨዋታ (Zero Sum Game)

ለውይይት መነሻ እንዲሆን ሃሳቤ እነሆ

(ከዶ/ር ሀይለመስቀል ሀይለማርቆስ)

የዜሮ ድምር ጨዋታ በዘመናዊ ማኔጅሜንት አመራር እና ምጣኔ  ሐብት  እንዲሁም መሰል ማህበራዊ  መስኮች ምርምር በስፋት በበጎ ጎኑና ትርጉም ባለው  መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለ ሃሳብ ነው፡፡  በዜሮ ድምር ጨዋታ ህግ ለአንዱ ማሸነፍ የሌላው ወገን መሸነፍ የግድ ነው፡፡ ሁለቱም ማሸነፍ የሚችሉበት እድል በዜሮ ድምር ጨዋታ ህግ ላይ የለም፡፡ 

እንደ እኔ ዕይታ  ከሆነ ባለፉት  በርካታ ዓመታት  በሀገራችን የምናስተውላቸው የመንግስት፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውሶችና ውጥንቅጦች  የዜሮ ድምር ጨዋታ  አሉታዊ  ውጤቶችና ውርሶች ናቸው፡፡ 

ለቅሶአችን የሃዘን ስሜታችንን ያበርድልን እንደሆን እንጂ የጉዳዩን አነሳስ ከስሩ እና አቀጣጠል ከምድራችን  ሊያጠፋው አይችልም፡፡ አሰቃቂ ግድያዎችን  በየዙሩ ለምን እናያለን ካልን  መልሱ  የዜሮ ድምር ጨዋታ (Zero Sum Game) አስተሳሰብ  የበላይነት በፖለቲካው መስክ ከዚያም  ቀላል በማይባል ሰው በመወረሱ ምክንያት  የተፈጠረ  ቀውስ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግስታችን ከቀውስ ወደ ቀውስ መንግስትነት እየተለወጠ ያለዉ፡፡

በዜሮ ድምር ጨዋታ  ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ  ወገኖች መካከል በሚደረግ ውድድር /ድርድር አሸናፊ ለመሆን የተቀናቃኙን  ሃብት/ጥቅም/መብት/ ወዘተ…..  ሙሉ በሙሉ በመውሰድ ነው፡፡ የነፍስ ማጥፋት  የዜሮ ድምር ጨዋታ የመጨረሻ ጫፍ ነው፡፡ 

የሰው ልጅ በሰው በግፍ ሲገደል ስናይ ገዳዮችና ተመልካቾች (እኔንም ጨምሮ) የቀጣይ ተረኞች መሆናችንን ልብ ያልን አንመስልም?  ከመለማመዳችን የተነሳ  የእንትና አገዳደል/ሞት ብለን እየተዘራዘርን፣ እየተመራረጥን ለመሞቱ ተገቢነት እና  ምክንያት የምናብራረበት ወይም ሁኔታስ አይተውታል?  መገዳደሉስ እየተግተለተለ እና እየቀጠለ ከእርስዎ በአጭር ርቀት እንዳለስ አውቀዋል?  መገዳደሉ ዘር፣ ፆታ፣ ስልጣን፣ ዕድሜ፣ ፖለቲካ ሳይለይ በቅጥልጥሎሽ እየፈጠነ ያለ መቅሰፍት መሆኑንስ የተረዳን አይመስልም? ይህንን ኢሰብአዊነት ከመካከላችን ሊያርቅልን የሚችል  ሰው ለምን አጣን ብለው ጠይቀው ያውቃሉ?  እንዴት ይህንን የዘመናችን ከሰውነት ተራ ያወረደንን ጭካኔ ተሸክመን እስከየት እንጓዝ? 

እኔን የሚያስጨንቁኝ የወቅቱ የሀገሬ ኢትዮጵያ ሁኔታ ጥያቄዎቼ ናቸው፡፡

ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ተቆራርጦ ፣ ተዘቅዝቆ ፣ ተቀጥቅጦ፣ ተቃጥሎ  በደቦ ፍርድ በተደጋጋሚ  ሲገደል ከማየት በላይ የሚዘገንን ምንም ግፍ እና አሰቃቂ ነገር በህይወት ዘመኔ አላየሁም፡፡ አልሰማሁምም፡፡ 

ከዚህ በላይ የማንነታችን መሰረት፣ የሰውነታችን ክብር ዘቅጦ ሰው በሰው ላይ የአውሬነቱንና ጭቃኔው የመጨረሻ ጫፍ እንደ ትርኢት በአይኖቻችን ሲገቡ አይቶ ማለፍ ፍጹም መፍትሄ አይሆንም፡፡ ድርጊቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ብልሽት መሆኑ በግልጽ ይነገር፡፡ ሁሉም  ዓይነት ውይይት ይደረግ፡፡ ችግሩን አይተን መፍትሄ ሳንጠቁም አንለፍ፡፡ ምክንያት አንፈልግ፡፡ 

መንግስት ይህንን ድርጊት  ከማውገዝ በተጨማሪ  ችግሩ  እንዳይቀጥል የሚያስችሉ እቅዶችን ይንደፍ፣ ተገቢ የሆነ ሃብት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች ህይወት እና ደህንነት ጥበቃ ይመደብ፡፡

ወገኔ ተራው የእኔ ነው ብለህ አስብ፣ ራስህን ጠብቅ፣ ቤተሰብህን እና ጎረቤትህን ጠብቅ፣ ከምንም መንግስት ደካማ መንግስት ይሻላልና ከመንግስት ጋር አብር፣ ተባበር፣ አክብርም፡፡ 

ያኔ መንግስትም የችግሩን ስፋት፣ ጥልቀት፣ ዓይነት፣ መልክ፣ ምክንያት፣ ሁኔታ፣ ማህበራዊ ፣ ህሊናዊ እና ፖለቲካዊ  ጫናዎችን መርምሮ አስተማማኝ  ማህበራዊ ደህንነትን  ለማስፈን እንዲተጋ  አቅም ይሆነዋል፡፡ በዜሮ ድምር   ጨዋታ ያለቦታው  ያውም በሰው ነፍስ ላይ ውጤቱ ለጊዜው መግደል ከዚያም መገደል በሂደት  መጠፋፋት ነውና ንቃ ወገኔ!!!

በሰው ነብስ የሚደረግ የዜሮ ድምር   ጨዋታ(ፖለቲካ)  እንዲቆም አሁን ማሰብ ጀምር፡፡

ከተሳሳትኩ አርሙኝ፡፡

አመሰግናለሁ፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top