የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በኮንጎ የተካሄደውን የሶስትዮሽ የሚኒስትሮች ስብሰባ በተመለከተ ለአፍሪካ አምባሳደሮች ገለጻ ተሰጠ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በኮንጎ የተካሄደውን የሶስትዮሽ የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ በተመለከተ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑ ለአፍሪካ አምባሳደሮች ገለጻ ተሰጠ።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኪኒሻሳ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ስር የተካሄደውን ስብሰባ በተመለከተ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ለአምባሳደሮቹ ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በሶስቱም ሀገሮች ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ስር የሚደረገው ድርድር መቀጠል እንዳለበት ያላትን ጽኑ እምነት ገልጻለች።
ሶስቱ ሀገራት የአባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ያላቸው አማራጭ በትብብር እና በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ስሜት በጋራ መስራት እንደሆነ ለአምባሳደሮቹ አስረድተዋል።
ድርድሩን ስኬታማ ለማድረግ እና መተማመንን ለማጎልበት እ.ኤ.አ. በጁላይ 2020 በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የቢሮ ስብሰባ ወቅት በተደረሰው መግባባት እና በወጣው መግለጫ መሰረት በሁለት ደረጃ ማለትም፣ በቅድሚያ በግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እና ተያያዥ የውሃ አለቃቀቅ ጉዳዮች እና በመቀጠልም ሁሉን አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ስምምነት ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ኢትዮጵያ ገልጻለች።
በቀጣዩ ሐምሌ ወር የሚደረገውን የሁለተኛ ዓመት ሙሌት አስመልከቶ ኢትዮጵያ ለሱዳን እና ግብጽ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ በቅን ልቦና ተነሳሽነቱን በመውሰድ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር በኩል ለግብጽ እና ሱዳን አቻዎቻቸው ደብዳቤ የተላከ መሆኑ ተገልጿል።
ሚኒስትሩም ግብጽና ሱዳን የህዳሴውን ግድብ የአረብ አገሮች የውሃ ደህንነት ስጋት አድርገው የሚያቀርቡት ሁኔታ እንዳሳዘናቸው ገልጸው የአባይ ተፋሰስ አገራት ሁሉ አፍሪካዊ ሆነው ሳሉ ጉዳዩን ለፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል የሚያራምዱት አቋም ተቀባይነት የሌለውና ሁሉም በአጽንኦት ሊገነዘበው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወቅታዊ የድርድር ሁኔታ በተጨማሪ ለአምባሳደሮቹ የኢትዮጵያ-ሱዳን ወቅታዊ የድንበር ሁኔታን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተደረጉ ስምምነቶች እና ባሉት የድንበር አሰራር ማዕቀፎች አማካኝነት በድርድር ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጻለች።
በአምባሳደሮቹም በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ስር “አፍሪካዊ መፍትሔ፣ ለአፍሪካ ችግር” በሚለው መርህ መሰረት ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ ገልጸው ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በዚሁ ማዕቀፍ ድርድራቸውን እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።
የኢትዮጵያ-ሱዳን ድንበርን በተመለከተ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቹን ለመፍታት የወሰደችውን አቋም የሚያደንቁ መሆኑን ማመልከታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።(EBC)