የሰባት ቁጥር ምስጢርና የይባቤ አዳነ አዲስ ሥራ፡፡
ሰባት ቁጥርና ሕይወት፤
(አፈወርቅ ልሣኑ ~ ድሬቲዩብ)
ሰባት ቁጥር ብዙ ትርጉም አላት ከሚሉት የቁጥሯ ምስጢር አክባሪ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሰባት ፍጹም ቁጥር መሆኑን አምነው ተቀብለዋል፡፡ ዛሬ ተራራ ላይ ሳይቀር የሰባት ቁጥርን ምስጢር ለታሪክ ማኖር ተጀምሯል፡፡ በከንባታ የሀምበርቾ ተራራ ላይ የተሰራው የሰባት መቶ ሰባ ሰባት ደረጃ እንዲህ ካለው የሰባት ቁጥር ክብር ጋር ይቆራኛል፡፡
ይባቤ አዳነ በኢትዮጵያ ምስጢራዊ እሴቶች ላይ ማተኮር ከሚሹ ደራሲያን አንዱ ነው፡፡ ቀደም ሲል “አክሳሳፎስ” የተሰኘ ምስጢራዊ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ ጽፎ ነበር፡፡ አነጋጋሪ የሆነውን የአክሳሳፎስ ሥራው ተከትሎ ደግሞ ከሰባት ቁጥር ጋር መጥቷል፡፡
ሰባት ቁጥርና ሕይወት የይባቤ አዳነ አዲስ ስራ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በርካታ ሰዎች ሰባት ቁጥርን ራሱን ችሎም የስራቸው አካል ሆኖም በህትመት ስናነበው ቆይተናል፡፡ አዲሱ የይባቤ አዳነ ሰባት ቁጥርን ከሕይወት ያቆራኘ መጽሐፍ ግን ጠለቅ ያሉ ኢትዮጵያውያን ማጣቀሻዎችን መሰረት ማድረጉ ይለየዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
256 ገጾችን በያዘው ሰባት ቁጥርና ሕይወት ቅጽ ሁለት መጻሕፍት ከ33 በላይ ቀደምት ሰነዶችን በማጣቀሻነት ተጠቅሟል፡፡ ከዚያ ውስጥም መጽሐፈ አዕናቁዕ አንዱ ነው፡፡ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያው መምህር ጽጌ መዝገቡ በመጽሐፉ ሽፋን በሰጡት አስተያየት “ይህ ሰባት (፯) ቁጥር በሚል ርዕስ የቀረበልን መጽሐፍ ሐሳበ ኁልቁ (ነገረ ቁጥር) ላይ ተመስርቶ የተቀነበበ ስለኾነ ለርዕሰ ጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን በሕይወታችን ላይ የሚያመጣውን በጎም ኾነ መጥፎ ተጽእኖ ተረድተን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡” ይላሉ፡፡
ሰባት ቁጥር እና ሕይወት የፍልስፍና መሠረት ከሚለው ቁጥር ተነስቶ፤ ዲባ አካላዊነትን ከቁጥሮች ጽንሰ ሀሳብ ጋር እያሰናኘ፣ የቆጥሮች ተጣጥሞሽን ከቁጥሮች ዶግማ ጋር እየፈተሸ ቁጥርን ከሳይንስ አስታርቆ፣ ሰባት ቁጥር ከግለሰብ ህይወት ሲቆራኝ ያለውን ምጡቅነት እያስረዳ፣ ሰባት ቁጥርን ለምን? የት? እያለ ጠይቆ የሚመልስ ሥራ ነው፡፡
ደራሲው ይባቤ አዳነ ሰባት ቁጥር እና ሕይወት መጽሐፉን በተመለከተ ትናንት በቱሊፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ መጽሐፉን እንዴት እንዳዘጋጀው፣ ለምን እንዳዘጋጀው፣ ቀደምቶቹ ሊቃውንት ረቂቅነት ከምዕራቡና ከምስራቁ ዓለም ጋር አናጽሮ አብራርቷል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የታሪክ መምህሩ ታዬ ቦጋለ “ሰባት ቁጥር የብዙ ምስጢር ባለቤት መሆኑን በሚገባ ተረድቻለሁ፡፡ ስለ ቁጥሩ ጉግል ሳደርግ ያገኘሁት ምስጢር የትየለሌ ነው” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ይባቤ አዳነ ከዚህ ቀደም “አክሳሳፎስ” የተባለውን አነጋጋሪ ሥራውን ጨምሮ “የእግዜር ድርሰት” እና “ሥልጡን ድንቁር” የተባሉ ሦስት ስራዎቹን ለህትመት ያበቃ ሲሆን “ሰባት ቁጥር እና ሕይወት” አራተኛ መጽሐፉ ነው፡፡