ዩኒቨርሲቲዎች በሸቀጦች ዋጋ ንረት ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገዋል
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር በተያያዘ ለተማሪዎቻቸው ምገባ ከፍተኛ ወጪ እያወጡ መሆኑን አስታወቁ። የገንዘብ ሚኒስቴር የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ባማከለ ሁኔታ የተማሪ ምገባ ባጀቱ ሊስተካከል እንደሚችል ገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ10 ዩኒቨርሲቲዎች ያደረገውን የመስክ ምልከታ ተከትሎ ግብረመልስ ለመስጠት ከትናንት በስቲያ ውይይት ባደረገበት ወቅት የ10ሩም ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ከሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር በተያያዘ ለተማሪዎቻቸው ምገባ ከተያዘላቸው በጀት በላይ ከፍተኛ ወጪ እያወጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንደገለጹት፤ በዋጋ መናር ምክንያት ዩኒቨርሲቲው የምግብ ግብአት አቅራቢዎች እጥረት አጋጥሞታል። ተማሪዎችን መመገብ የግድ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ወጪ እያወጣ ይገኛል።
ለአንድ ተማሪ የተመደበው የምግብ አቅርቦት በቀን ከ16 ብር አይበልጥም ያሉት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን የዘይት ፣ የስንዴ እና ሌሎች የምግብ አቅርቦቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በማሳየታቸው ዩኒቨርሲቲው በጨረታ የሚገዛቸው ግብአቶች ዋጋ በአማካይ ለአንድ ተማሪ 30 ብር መድረሱን ገልጸዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ጣሰው ከሆነ፤ ዩኒቨርሲቲው የሚያወጣው ተጨማሪ ወጪ በኋላ ላይ የኦዲት ግኝት ተብሎ መምጣቱ ስለማይቀር ከወዲሁ የግዥ ሥርዓቱን ማስተካከል ይገባል። ለአንድ ተማሪ በቀን የሚወጣውን ወጪ ከፍ ማድረግ እና ዩኒቨርሲቲዎች በውስጥ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ለመፍታት በእራሳቸው ቦርድ አማካኝነት በነጻነት እየወሰኑ እንዲሰሩ የሚያደርግ አሰራር ያስፈልጋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ብርሃኑ ገድፍ በበኩላቸው ፤ በአማራ ክልል የሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የምግብ አቅርቦት ችግር ገጥሟቸዋል። በተለይ በ75 ብር እንዲገዙ የተወሰነው በርበሬ ከዋጋው በላይ ሲገዙ ቢቆዩም አሁን ላይ ከ250 ብር በመግባቱ አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ግብአቱን አላገኙም።
የምግብ ግብአት አቅርቦት ለማድረግ ጨረታዎችን የሚያሸንፉ ድርጅቶችም በየጊዜው የዋጋ መናር በመፈጠሩ ምክንያት ውል የገቡበትን ምርት ሳያቀርቡ ያቋርጣሉ ብለዋል።
በተፈጠረው የአቅርቦት ችግር ምክንያት እንደባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመጋቢት በኋላ ለተማሪዎች ምግብ ለማቅረብ የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ብርሃኑ፤ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ከዩኒቨርሲቲዎች አካላት የተሳተፉበት ጥናት ማድረግ እና የግዥ ሥርዓቱን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የአፋር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አደም ቦሪ እና የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ወጪ እያወጡ ግብአት መግዛታቸውን ቀጥለዋል። አሁን ላይ ደግሞ ዋጋው በመናሩና የስንዴ አቅርቦት ባለመኖሩ ለተማሪው በዘላቂነት ዳቦ ለማቅረብ እክል ፈጥሯል።
በየጊዜው ያለው የዋጋ ንረት የዳቦ ዋጋ አራት እጥፍ ባደገበት ወቅት የዩኒቨርሲቲዎች የግብአት ግዥ አሰራር አለመሻሻሉና የዋጋ ውድነት መባባሱ በዩኒቨርሲቲዎቹ የምገባ ስርዓት ላይ እክል እየፈጠረ ነው። ችግሩን በመገንዘብ የዩኒቨርሲቲዎችን የምገባ ወጪ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ ከዓመታት በፊት በዩኒቨርሲዎች ለሚገኙ ተማሪዎች የምገባ ወጪ በነፍስ ወከፍ በቀን 18 ብር ከ33 ሳንቲም ያስፈልጋል የሚል ጥናት እንደተደረገ አስታውሰዋል።
በወቅቱ የባጀት እጥረት ስለነበር ግን ለአንድ ቀን የምገባ ወጪ 15 ብር ይበቃል የሚል ውሳኔ መሰጠቱን አስረድተዋል። የተቀመጠው ዋጋ ግን አሁን ያለውን የገበያ ሁኔታ የማያገናዝብ በመሆኑ ሊሻሻል እንደሚገባው ገልጸዋል።
እንደ ዶክተር ሳሙኤል ከሆነ፤ ገበያው በየጊዜው ሲጨምር እነጂ ሲቀንስ አይታይም። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎች ያጋጠማቸውን የምግብ ግብአት አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚረዳ እና ያሉበትን ሁኔታ ሊያስተናግድ የሚችል ህግ ያስፈልጋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ክፍል በበኩሉ የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ባማከለ ሁኔታ የተማሪ ምገባ ባጀቱ ሊስተካከል እንደሚችል ገልጿል። ዩኒቨርሲቲዎቹ ህጋዊነት ባለው መልኩ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት የሚኒስቴሩ ባጀትና እቅድ ዝግጅት ክፍል ወቅቱን ያገናዘበ የአንድ ተማሪ የቀን ባጀትን ከፍ በማድረግ ችግሩን የማቃለል አሰራር እንዳለውም አስታውቋል።
እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ ከሆነ፤ በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የተማሪዎች የቀን ምገባ ባጀት አነስተኛ መሆኑን ሚኒስቴሩ ቢረዳም ጥያቄው ህጋዊነት ባለው መልኩ ቀርቦ ይስተካከላል የሚል እምነት አለው። ዋጋው እስኪስተካከል ድረስ ግን በተቀመጠው የባጀት አሰራር መሰረት ክፍያቸውን እይፈጸሙ የፋይናንስ ህጉ የሚጠይቀውን አሰራር መተግበር ያስፈልጋል።(ኢፕድ)