እሾሁን በጋራ…
ሁሉም የሚያምረው በሀገር ነው።
(ሙፈሪያት ካሚል)
ሀገር ማለትም ሰዉ ነው፣ ሰዉነትም ነዉ። ሰውነት ደግሞ መከባበርን፣ መተሳሰብን፣ ርህራሄን፣ መደማመጥን፣ አንዱ የሌላዉን ህመም መታመምን ይሻል።
ሁሉም የሚያምረው በሀገር ነው፣ ሀገር ሰላም መሆንን ትሻለች። ለዚህ ደግሞ መንግስት፣ መላው ህብረተሰብ በተደራጀ መንገድ እያንዳንዳችን እንደ ዜጋ በጋራ አንድ ሆነን ስንቆም ነው።
ውድ ወገኖቼ!
እጅግ የሚያሳዝኑ፣ ልብ የሚሰብሩ፣ የሚያሳፍሩም ጭምር ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች በተለያዩ ጊዜያት አጋጥመዋል፣ እያጋጠሙም ይገኛል። ይቆጫሉ፣ ያበሳጫሉ፣ ያሳምማሉ፣ ያሳዝናሉ። መንስኤና መፍትሄዎቻቸውን ከመነጋገርና በጋራ ለመጋፈጥ ከመወሰን ውጪ አማራጭ የለንም።
ከራሳቸው ጥቅም አኳያ የኢትዮጵያ መንገድ ያልተዋጠላቸው ሀይሎች ከዉስጥና ከዉጭ ካሉ ቡድኖች ጋር በመመሳጠር ሰላሟን የሚነሱ ልማቷን የሚያስተጓጉሉ፣ የዴሞክራሲ ትልሞቿን የሚገዳደሩ ስሱ(sensitive) አጀንዳዎችን ለይተዉ መስራት ከጀመሩ ዋል አደር ብሏል። ይህ ከውስጥ ድካማችን ጋር ተዳምሮ ጠላቶቻችን የሚመኙት ሁኔታ ውስጥ እንደምንገኝ ምን ያህል አስተዉለናል?
ኢትዬጵያ ዉስጥ የብሄር ፣ የሀይማኖት ጉዳዮች እጅግ ስሱ (sensitive) መሆናቸው ይታወቃል። የጠላቶቻችን ስልትም እዚህ ላይ ያነጣጠረ ሆኖ የሞት የሽረት ትግል የሚያደርጉበት የዉስጥ ሁኔታችን ለዘመናት በዞሩ ዕዳዎችና በአዳዲስ ክስተቶች ድምር ውጤት መላጋት ምቹ ሁኔታ መሆኑን በመገምገም ይህን በተለያዩ ስልቶች በማባባስ እንዳንደማመጥም ጭምር ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ መድቦ ሰፊ ርብርብ እያደረጉ ይገኛል። ብዙዎቹን እንቅስቃሴዎች እና ሙከራዎች በተግባር እያየናቸው ነው።
እያስተዋልናቸው ነውን?
መኖር፣ መታመም፣ መሞት፣ በወጉ መቀበር ማበድም ጭምር ሰላማዊ ሀገር ይሻሉ።
ከያኒው እንዳለው “ሰው የሞተ እንደው በሀገር ይለቀሳል በሀገር …”
ዉድ ወገኖቼ ሰክኖ መነጋገር የሚሹ በርካታ ዕዳዎች አሉን የጀመርነው አለ አጠናክረን መቀጠል የሚጠይቀን። አብዛኞቹ ዕዳዎች የትውልዱ ያልሆኑ ግን ተነጋግሮ የመፍታት ሀላፊነትን የተሸከምንበት ነው። ደግሞም ማድረግ የምንችለውና የሚገባን። ሀገር በትዉልዶች ቅብብሎሽ ነውና የምትገነባው።
አዎ ባለዕዳዎች ነን።
ለምን በዚህ ወቅት ሀገሬን በሁሉም አቅጣጫ ሰቅዞ መያዝ ተፈለገ?
ለምን አንዴ በብሄር አንዴ በሀይማኖት እያፈራረቁ እርስ በእርስ በጥርጣሬ መተያየታችንን ማስፋት ተፈለገ? ቁስሎች ከመዳን ይልቅ የሚመረቅዙበት አማራጭ ላይ መረባረብ ተፈለገ?
በሌለን ተለዋጭ ሀገር እያንዳንዳችን ለእነዚህ እና ለሌሎች ጥያቄዎች ከስሜታዊነት ርቀን ምክኒያታዊነትን አስቀድመን ይህ የውስጥና የዉጭ ሀይሎች ፍላጎት እንዳይሳካ እኔ ምን አደረግኩ? ምንስ ላድርግ ማለት በየደቂቃው፣ በየሰዓቱ፣ በየዕለቱ የምናስበው፣ ለተግባራዊነቱ የምንረባረብበት፣ ወትሮ ከእናት አባቶቻችን የወረስነው የአይበገሬነት፣ የማይቻሉ የሚመስሉ በርካታ ተግዳሮቶችን የተወጣንበት: ይህ ትዉልድ የአያት የቅድመ አያቶቹ ብቻ ሳይሆን መፃፍ የጀመራቸው የራሱ ድንቅ ታሪኮችም ጭምር ያሉት ነዉና እነዚህንና መሰል አስተዉሎቶችን በመታጠቅ እሾሁን በጋራ የምንነቅልበት መንገድ ነው መዉጫ መንገዳችን።
የሰላም ባለቤት እርስዎ ነዎት!