Connect with us

የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ ይጀመራል

የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ ይጀመራል
ኢዜአ እና ኢኘድ

ዜና

የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ ይጀመራል

የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ ይጀመራል

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በሆነችው በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ አደራዳሪነት የሚካሄደው የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ከመጋቢት 25 – 26/2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተሰማ።

ድርድሩ የሚካሄደው ዲሞክራቲክ ኮንጎ ለሦስቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የውሃ ሚኒስትሮች ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት ነው ተብሏል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ውጣ ውረድ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውሃ ሙሌት መከናወን መላ ኢትዮጵያውያንን በደስታ አስቦርቋል።

አስር ዓመታት በግንባታ ላይ የቆየው ግድብ ውሃ መያዝ በመጀመሩ ሱዳንና ግብጽ ያልተገባ ቅሬታ ቢኖራቸውም ለኢትዮጵያውያን ግን የስኬት መንገዱን አሳይቷል።

የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ከራስ ባለፈ ለጎረቤት አገራት ከፍተኛ የልማት አማራጭ ይሆናል።

ግብጽ የአባይን ውሃ በጋራ ለመጠቀም ከኢትዮጵያ ጋር ባለመስማማት ወደ ራሷ ፍላጎት ያዘነበለና ሁሉን አቀፍ የምትለው ስምምነት እንደሲታሰር እየወተወተች ትገኛለች።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ከመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም አንስቶ የተለያዩ ፈተናዎችን፣ ውጣ ውረዶችንና የጊዜ ሂደቶችን በማለፍ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡

ግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ላለፉት አስር ዓመታት በአባይ ጉዳይ እየተደራደሩ ቢሆንም በሁለቱ አገራት በቻ እበላ ባይነት ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ መግባባት ላይ መድረስ አልቻሉም።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአስር አመት ጉዞን በማስመልከት ወሳኝ የተባሉ እውነታዎችን በአጭሩ ለመዳሰስ እንሞክራለን፤ የተጠቀሱት ዓመተ ምህረቶች ሁሉም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ናቸው።

2003 መጋቢት፡ 

የኢትዮጵያ መንግሥት በአባይ ወንዝ ላይ ሊገነባው ያሰበውንና በአፍሪካ ትልቁ እንደሚሆን የተነገረለትን የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ጉባ ላይ ይፋ አደረገ።

ይህን ተከትሎ በሚያዝያ 2003 ዓ.ም የግድቡ ግንባታ በይፋ ተጀመረ።

ግንቦት ወር ላይ ግብጽ ሱዳንና ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅረው ጥናት ማካሄድ ጀመሩ።

2004 ግንቦት፡ 

ከሦስቱ አገራት የተውጣጣ ኮሚቴና አራት የውጭ አካላትን ያካተተው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የግድቡን ተጽእኖ ማጥናት ጀመረ።

በጥቅምት 2005 ላይ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ግድቡ የሚገነባበትን ቦታ ሄዶ ጎበኘ። 

2005 ግንቦት፡

ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ የጉዞ አቅጣጫ በመቀየር ወሳኝ የተባለውን የግንባታ ሂደት ተሻገረች።

የባለሙያዎቹ ቡድን በዛው ዓመት ሰኔ ላይ የመጨረሻ የጥናት ሪፖርቱን ቢያቀርብም ኢትዮጵያና ግብጽም በሪፖርቱ አተረጓጎም ላይ መስማማት አልቻሉም።

የወቅቱ የግብጽ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሙርሲ በግድቡ ዙሪያ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን በመያዝ በቴሌቪዥን በሚያደርጓቸው ንግግሮችና ውይይቶች ላይ ኃይል መጠቀም የሚለውን ሀሳብ በተደጋጋሚ ያነሱ ነበር።

ግብጽ በተደጋጋሚ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደምትወስደው ብትናገርም ብዙም ሳይቆይ አገራቱ የባለሙያዎቹ ቡድን ያቀረበውን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ፖለቲካዊና ቴክኒካዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስማሙ።

በ2006 መስከረም፡

ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጠቃላይ ስብሰባ በኒውዮርክ ሲካሄድ ሁለቱ አገራት ባደረጉት የጎንዮሽ ስብሰባ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ድርድሩን ለማስቀጠል ተስማሙ።

በኅዳር እና በታህሳስ ወር ላይ የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ካርቱም ላይ ተሰባስበው ባለሙያዎቹ ያቀረቡትን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት ቢያደርጉም ያለስምምነት ተጠናቀቀ።

2006 ጥር፡

የኢትዮጵያ፣ የግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ለሦስተኛ ጊዜ በካርቱም ተገናኝተው በቀሪ ጉዳዮች ላይ መስማማት ስላልቻሉ ከዚህ በኋላ ስብሰባ ላለማድረግ ተስማሙ።

የካቲት ወር ላይ ደግሞ የኢትዮጵያና የግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች ብቻ በአዲስ አበባ ቢሰበሰቡም ምንም አይነት ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።

መጋቢት ወር ላይ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የግብጽን አቋም ለዓለምዓቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅና በጎኑ ለማሰለፍ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ግብጽ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የጀመረቸውን ዘመቻ እንድታቆምና ወደ ሦስትዮሹ ድርድር እንድትመለስ ጥያቄዋን አቀረበች።

ሰኔ ወር ላይ የግብጽና የኢትዮጵያ መሪዎች በኢኳቶሪያል ጊኒ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ላይ በተጓዳኝ ውይይት በማድረግ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በድጋሚ ሥራውን እንዲጀምር ተስማሙ።

በነሐሴ ወር ላይ ደግሞ የሦስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች በካርቱም ድርድራቸውን በድጋሚ ጀመሩ። 

በዚያውም በባለሙያዎቹ ቡድን ምክረ ሀሳብ መሰረት አገራቱ በገልተኛ ዓለም አቀፍ ድርጅት የሚመራና ከሦስቱ አገራት የተውጣጡ አባላት ያሉት ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማሙ።

2007 መስከረም፡ 

የግብጽና የሱዳን ውሃ ሚኒስትሮች የግድቡን የግንባታ ሂደት ከጎበኙ በኋላ የሦስትዮሽ ኮሚቴው አባላት በአዲስ አበባ ውይይት አደረጉ።

ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ የግድቡን አጠቃላይ ጥናት የሚያካሂድ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅትን ለመምረጥ በካይሮ ስብሰባ አደረጉ።

2007 ጥር፡ 

ግብጽ የግድቡን 74 ቢሊየን ኪዪቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅምና የግድቡን ከፍታ አልቀበለውም አለች።

መጋቢት ላይ ካርቱም በተደረገው ሦስተኛው ዙር የሦስትዮሽ ኮሚቴ ስብሰባ አገራቱ በመርህ ደረጃ በሚያስማሟቸው ጉዳዮች ላይ ተፈራረሙ።

በተመሳሳይ ወር የግብጹ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ንግግር አደረጉ።

2007 ሚያዝያ፡

የሦስትዮሽ ኮሚቴው በአዲስ አበባ በመገናኘት የግድቡን አጠቃላይ ጥናት የሚያከናውኑ ሁለት የአውሮፓ አማካሪዎችን መረጡ።

በሐምሌ ወር ላይ ደግሞ የኮሚቴው አባላት በካይሮ ባደረጉት ስብሰባ የሁለቱ አማካሪዎች የመጀመሪያ ዙር ምክረ ሀሳብን ገመገሙ።

2008 ኅዳር፡ 

የሦስትዮሽ ኮሚቴው በካይሮ ባደረገው ስብሰባ በሁለቱ የአውሮፓ አማካሪዎች መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ተገለጸ። 

ታህሳስ ወር ደግሞ ኮሚቴው ካርቱም ላይ በደረሰው ስምምነት መሰረት የግድቡን አጠቃላይ የጥናት ሥራ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅና ከአማካሪነት ራሱን ባገለለው ድርጅት ፈንታ አዲስ አማካሪ ለመምረጥ ተግባቡ።

2008 ጥር፡

የግብጽ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አዲስ አበባ ውስጥ በመገናኘት የካርቱሙን ስምምነት ለማክበርና ከመግባባት ላይ ለመድረስ ተስማሙ።

የካቲት ወር ላይ ደግሞ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በካርቱም በመሰብሰብ ግድቡ በግብጽና በሱዳን ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ በፈረንሳይ አማካሪ ድርጅት በተሰራው ጥናት ላይ በመወያየት ግምገማ አካሄደ።

2009 መስከረም፡

ሦስቱም አገራት በዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን የቀረበውን ምክረ ሀሳብ ለማስፈጸም ‘ቢአርኤልአይ’ ከተባለው የፈረንሳይ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራረሙ።

2009 የካቲት፡ 

ሁለቱ የፈረንሳይ አማካሪ ድርጅቶች ያቀረቡትን የመጀመሪያ ዙር ሪፖርት ግብጽ ስትቀበለው ኢትዮጵያና ሱዳን ግን ውድቅ አደረጉት።

ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ የግብጽ ፕሬዚዳንትና ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካይሮ ውስጥ ተገናኙ። 

2010 ጥቅምት፡

የሦስትዮሽ ኮሚቴው ካይሮ ውስጥ በመሰብሰብ በሁለቱ የፈረንሳይ አማካሪ ድርጅቶች በቀረበው ምክረ ሀሳብ ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ዙሪያ ምክክር አደረገ።

ሕዳር ወር ላይ ደግሞ በድጋሚ ኮሚቴው በካይሮ ቢሰበሰብም ምንም ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ቀረ።

በዚያው ወር ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብጽ ችግር እየፈጠረች ነው በማለት ከሰሰ።

2010 ጥር፡ 

የግብጹ ፕሬዚዳንት ድርድሩ ተስፋ ሰጪ ነገር እየታየበት አለመሆኑ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ የዓለም ባንክን በጉዳዩ ለማስገባት ሀሳባቸውን አቀረቡ።

ነገር ግን ኢትዮጵያ የግብጽን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደረገችው።

በዚያው ወር ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ዓመታዊ የሦስትዮሽ ስብሰባ ለማካሄድና በአንድ ወር ውስጥ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የመሰረት ልማት ፈንድ በማቋቋም የሦስቱንም አገራት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማሙ።

ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሚኒስትሮችና የደኅንንት ኃላፊዎች በካርቱም ተሰበሰቡ።

ነገር ግን ስብሰባው ፍሬያማ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችል ተበተነ።

ግንቦት ወር ላይ የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውጭ ጉዳይ፣ የደህንንትና የውሃ ሚኒስትሮች በድጋሚ ስብሰባቸውን በአዲስ አበባ ላይ አደረጉ።

ግብጽም ስብሰባው ስኬታማ እንደነበረ ገለጸች።

ሰኔ ወር ላይ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብጽን ሲጎበኙ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ የግብጽን የውሃ ድርሻ እንደማይጎዳ ተናገሩ።

2011 መስከረም፡

ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ ግብጽ ስምምነቱን አልፈርምም አለች።

2011 ጥር፡

በሱዳን እየተካሄደ በነበረው ከፍተኛ ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ምክንያት የግድቡ ድርድር መቋረጡን ግብጽ አስታወቀች።

ሐምሌ ወር ላይ የግብጹ ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካይሮ ውስጥ ተገናኙ። 

በዚያውም የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማስቀጠል ተስማሙ።

2012 መስከረም፡

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድርድሩ መጓተት አሳስቦኛል ሲል ኢትዮጵያ ደግሞ ግብጽ ከግድቡ አሞላል ጋር በተያያዘ ያቀረበችውን ሀሳብ በድጋሚ ውድቅ አደረገችው።

ግብጽ በበኩሏ ኢትዮጵያ ግድቡን ወደ ሥራ እንዳታስገባ ያስጠነቀቀች ሲሆን ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ ዋይት ሐውስ ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ መግለጫ አወጣ። 

ግብጽም በግድቡ ድርድር ላይ አሜሪካ እጇን እንድታስገባ ጥያቄዋን ስታቀርብ ኢትዮጵያ ደግሞ የግብጽን ጥሪ ተቃወመች።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር ማንኛውም አይነት ኃይል ኢትዮጵያን ግድቡን ከመገንባት እንደማያስቆማት ተናገሩ።

ግብጽ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በመተቸት በአሜሪካ ዋሽንግተን ለመነጋገር የቀረበውን ሀሳብ እንደምትቀበለው ተናገረች።

ሁለቱ አገራት በሶቺ በተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ላይ በመገናኘት የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማስቀጠል ቢስማሙም ኅዳር ላይ ደግሞ በአሜሪካ አደራዳሪነት አዲስ ውይይት ተጀመረ።

የሦስቱ አገራት የውሃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በዋሽንግተን ድርድራቸውን ካደረጉ በኋላ በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሁለተኛ ድርድራቸውን በአዲስ አበባ አካሄዱ።

ታህሳስ ወር ላይ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በካይሮ፣ ዋሽንግተን እና ካርቱም በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሦስት ስብሰባዎችን አካሄደ። 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ስብሰባው ውጤታማ እንደነበረና ግብጽም ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ ያቀረበችውን ሀሳብ እንደተወችው አስታወቀ፣ ነገር ግን ግብጽ አልተውኩትም በማለት አስተባበለች።

2012 ጥር፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብፅ የህዳሴ ግድብን እንደምታፈርስ መናገራቸውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርን በመጥራት ማብራሪያ ጠይቋል።

ዶናልድ ትራምፕ በስልክ ንግግራቸው “ግብፅ ግድቡን ታፈነዳዋለች” ከማለት በተጨማሪ ኢትዮጵያ የገነባችው የህዳሴ ግድብ ውሃ ወደ ናይል እንዳይፈስ ያደርጋል ብለዋል።

የአገራቱ የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች ዋሽንግተን ሁለት ጊዜ ሲገናኙ የውሃ ሚኒስትሮች ብቻ ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ተገናኝተዋል።

ሕጋዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ቡድን ደግሞ ካርቱም ውስጥ ከተገናኘ በኋላ በተደረሱ ስምምነቶች ዙሪያ ለየቅል የሆኑ መግለጫዎችን ወጡ።

ሕጋዊና ቴክኒካዊ ቡድኑ እንዲሁም የውሃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በአሜሪካ ዋሽንግተን በተደጋጋሚ ቢወያዩም የመጨረሻዎቹን ሁለት ስብሰባዎች ኢትዮጵያ አልተካፈለችም። 

ግብጽ ደግሞ ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ አሸማጋይነት የቀረበውን ሀሳብ ተቀብላ ስምምነቱን ፈረመች።

መጋቢት ወር ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃላፊዎች በግድቡ ላይ የሚፈጸም ማንኛውም አይነት ጥቃትን ለመመከት ዝግጁ መሆናቸው አስታወቁ።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አሜሪካ በድርድሩ ላይ ወደ አንድ ቡድን ያጋደለ አቋም እንዳራመደች በመግለጽ ቅሬታውን አቀረበ።

ግብጽ በበኩሏ ወደ አረብ አገራት በመሄድ አቋሟን እንዲረዱና እንዲደግፏት ዘመቻ አደረገች ነገር ግን ኢትዮጵያም በአረብ ሊግ የቀረበውን ሀሳብ አልቀበልም አለች።

ግንቦት ላይ የግድቡን ሙሌት የተመለከተውንና በኢትዮጵያ የቀረበውን ሀሳብ ግብጽ እንደማትቀበለው አሳወቀች።

ኢትዮጵያ ደግሞ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅና የውሃ ሙሌት ሥራውን በተገቢው መንገድ ለማከናወን የግብጽን ይሁንታ እንደማትፈልግ በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ጻፈች።

ግብጽ ደግሞ ቀደም ብላ ሁለቱ አገራት ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ ግድቡን የመሙላት ሥራውን እንዳትጀምር ለጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ደብዳቤ አስገብታ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ ሁለቱ አገራት አለመግባባታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱት ሀሳቡን አቅርቧል።

ሰኔ ወር ላይ ሱዳን ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ሁለቱ አገራት ውይይት ሳይካሄድ ምንም አይነት ውሳኔ እንዳያስተላልፉ ስትል ጠየቀች።

ሁለቱ አገራት በሶቺ በተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ላይ በመገናኘት የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማስቀጠል ተስማሙ።

የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን አምስት ተከታታይ ድርድሮችን ሲያደርጉ ግብጽ ድርድሩ ተስፋ ሰጪ አይደለም ስትል ኢትዮጵያ በበኩሏ ድርድሩ ውጤታማ የማይሆነው በግብጽ ምክንያት ነው ስትል ከሳለች።

ሰኔ 26 ላይ ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሰብሳቢ ሲሪል ራማፎሳ ከሦስቱ አገራት መሪዎች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተገናኘተው ተወያዩ።

በዚህም ስምምነት ላይ ለመድረስ የተስማሙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በተከታይነት በነበሩት ሳምንታት እንደምትጀምር በመግለጽ የግድቡን ሥራ ለማከናወን አገራትን መለመን እንደበቃት አስታወቀች።

ሐምሌ ላይ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ወታደራዊ አማራጭ እንደሚከተል ገለጸ።

በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት ሦስቱንም አገራት በማሳተፍ የተካሄደውም ድርድር ያለምንም ስምምነት ተጠናቀቀ።

በዚሁ ወቅት ክረምቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሌት መጀመሩን ይፋ ማድረግ ጀመሩ። 

ሱዳን በበኩሏ የሙሌት ስራው ተጀመረ ከተባለ በኋላ የ90 ኪዩቢክ ሜትር ቅናሽ ማየቷን አስታወቀች።

2013፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጪው ሐምሌና ነሃሴ ወራት ሁለተኛውን ዙር ውኃ ከመያዝ የሚያግደው ነገር እንደሌለ የተገለጸው በያዝነው ወር ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት የአምስት ዓመት ጊዜ በላይ በእጥፍ ጨምሮ 10ኛ ዓመቱን ሲይዝ የግንባታ አፈጻጸሙ 79 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ በዘገየ ቁጥር የግንባታ ወጪውም በዚያው ልክ እየጨመረ በመሄዱ ግንባታው ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅም ተገልጿል።

በተያዘው ዕቅድ መሰረትም በዘንድሮ ክረምት ግድቡ ሁለተኛ ዙር ውኃ መያዝ የሚያስችለው ሥራ እየተሠራ ነው ተብሏል።

በዚህ ሳምንትም የግብጹ መሪ ተመሳሳይ ማስፈራሪያቸውን በመሰንዘር ከድርድር ይልቅ ለጠብ ማሰፍሰፋቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

ግድቡን በተመለከተ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መፍትሔ እንዲመጣ ከፍተኛ ፍላጎት አላት” ሲሉ የመንግስት አካላት ተናግረዋል።(ኢዜአ እና ኢኘድ)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top