Connect with us

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ኢትዮጵያን ቆፍጠን ብለው ይምሯት፤ ህግን በአለንጋዎ ያስከብሩ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ኢትዮጵያን ቆፍጠን ብለው ይምሯት፤ ህግን በአለንጋዎ ያስከብሩ፤ አሊያ ቀጣዩ ሲመትዎ በሻሻ ብቻ መከበሩ አይቀርም
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ኢትዮጵያን ቆፍጠን ብለው ይምሯት፤ ህግን በአለንጋዎ ያስከብሩ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ኢትዮጵያን ቆፍጠን ብለው ይምሯት፤ ህግን በአለንጋዎ ያስከብሩ፤ አሊያ ቀጣዩ ሲመትዎ በሻሻ ብቻ መከበሩ አይቀርም

(ስናፍቅሽ አዲስ~ ድሬቲዩብ)

በዓለ ሲመትዎን በኦሮሚያ ደረጃ ስለመከበሩ ሰማሁ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በየቀኑ አማራ በማንነቱ እየተገደለ፣ በትግራይ ያለው ቀውስ ወደ ቦታው ሳይመለስ፣ የአፋርና የኢሳ ፍጥጫ መፍትሔ ሳያገኝ፣ መተከል የደም መሬት መሆን ሳያቆም፣ የአጣዬ ሞት አርባው ሳይወጣ፣ በድፍን ኢትዮጵያ በዓለ ሲመትዎን ማክበር አይቻልም፡፡ ምናልባትም ዘንድሮ በኦሮሚያ ብቻ የተከበረው ሲመት ቆፍጠን ካላሉ በቀጣይ አመት በሻሻ ብቻ ላለማክበሯ ዋስትና የለዎትም፡፡

ምንም ማጋነን አያስፈልገውም፤ እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ እርስዎ የተፈተነ መሪ የለም፡፡ ለሀገርዎ ትልቅ ነገር ቢያስቡም ብዙ ትንንሽ ሀሳቦች በየቀኑ እየጠለፉ እረፍት ያሳጣዎት መሪ ስለመሆንዎት ለመረዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡

ግን መወሰን አቅቶዎታል፡፡ ያቀፉት የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ክልሉን መምራት አልቻለም፡፡ ለዓለም ቅርስነት የበቃው የገዳ ሥርዓት የደሃ ነፍስ ለመታደግ አደባባይ ሲቆም አልታየም፡፡ ፖለቲከኞችዎ ንጹህ እንዳይሞት ከማድረግ ይልቅ አደባባይ ወጥተው እንካ ሰላንቲያ ጀምረዋል፡፡

የአማራ ህዝብ ከጎንዎ በመቆም ቀዳሚው ነው፡፡ በስልጣን ዘመነዎ ግን እንደ ህወሃት ዘመን ስልጣንና ዲሞክራሲ አይደለም ያጣው፡፡ መኖር ተከለከለ፤ ሰላም ተነፈገ፡፡ እንደ በግ በየቦታው ታረደ፡፡ በሟች ቁጥር የሚዘባበት ሹም የንጹሃንን ህይወት ከመታደግ ይልቅ በመግለጫ ድራማ ይሰራ ይዟል፡፡

ሀገሩን እንደሚወድ ዜጋ እየሆነ ያለውን ነገር እረዳለሁ፡፡ ግብጽ ረዥም እጇን ልካለች፡፡ የህወሃት ርዝራዥ ያገኘውን አጋጣሚ መጠቀሙን ቀጥሏል፡፡ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሰላም ብርቅ የሆነው ለውጡን ተከትሎ ነው፡፡ ወያኔን ለመጣል ሆ ብሎ የተነሳው የወለጋ ጉብል ለምን ወደ ሰላም እመለሳለሁ ያለ እስኪመስል በየቀኑ ፍጅት ሆኗል፡፡

በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ሀገርን ሩቅ እያለሙ መምራት እውነት ለመናገር ያስከብራል፡፡ እየሆነ ያለውን ሁኔታ ላጤነ ግን ሩቅ አላሚ ቅርብ አዳሪ እንዳንሆን አሁን ጨከንና ቆፍጠን የሚሉበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡

የወለጋ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪ ነኝ ያሉትና በእርስዎ የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው ሲነገርላቸው የነበሩት ጃል መሮ ሰሞኑን በአሜሪካ ድምጽ ወደ አደባባይ ወጥተው እየሆነ ያለውን ገለልተኛ ወገን ያጣራው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ግድያውና ማፈናቀሉ መቆሚያ የሌለው ሲሆን ህዝቡ የኦሮሚያ መንግስት መሪዎችን መጠራጠር በጀመረ ማግስት ይሄ ቃለ ምልልስ የሚያሳድገው ጥርጣሬ እንዳለ ይሰማናል፡፡ ይሄንን ሁሉ ሊፈታ የሚችለው ግን በቃ ማለት ነው፡፡

እንደ መሪ ከዚህ የከፋ ምንም ነገር ሊገጥምዎት አይችልምና በቃ ይበሉ፡፡ ጠንካራ እርምጃ የሚያስፈልግበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ ከሃይልና ከጉልበት ይልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ትልቅ ጉዳይ ናቸው፡፡ ነገሩ የፖለቲከኞች ቁማር ይመስላል፡፡ ቁማሩ ውሎ አድሮ ከእርስዎ ውጪ ሊበላው ያሰበው ትልቅ ግብ የለውም፡፡ እያንዳንዱ ንጹህ ነፍስ እየተቀጠፈ ያለው እርስዎን ወደ መጣል በሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ ያን ጉዞ የመቅጨት በትሩ እጅዎ ላይ ነው፡፡

ፈተናዎቹ ከባድ ቢሆኑም የእርምት እርምጃዎቹ ማነስ ግን ችግሩን አብሶታል፡፡ ሀዘን መግለጫና ኢትዮጵያ ትቀጥላለች የሚለው ንግግርዎ በየቀኑ የዜጎች ነፍስ እንዳይቀጥል አድርጓል፡፡ እናም ቆፍጠን ብለው ህግን በአለንጋዎ ካላስከበሩ የአምናውን የሰው ልብ ከርሞ እያጡት መቀጠል ብቻ ሳይሆን የሚወዷትን ኢትዮጵያ ሊያደርሱ የሚፈልጉበት ሳይሆን ማየት የማይሹበት ይወስዷታል፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top