Connect with us

የጠ/ሚኒስትሩ ገራሚ ንግግር ሲታወስ

የጠ/ሚኒስትሩ ገራሚ ንግግር ሲታወስ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የጠ/ሚኒስትሩ ገራሚ ንግግር ሲታወስ

የጠ/ሚኒስትሩ ገራሚ ንግግር ሲታወስ

ዶ/ር  ዐብይ አሕመድ የዛሬ ሶስት ዓመት በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙና ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ያደረጉት ንግግር በህዝብ ዘንድ  ከፍተኛ አክብሮትንና ተወዳጅነትን አስገኝቶላቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ያደረጉትና አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስደነቀው ይህ ንግግራቸው ዛሬ ከሶስት ዓመት በኋላ ሲያስታውሱት ምን ተሰማዎት? በጨዋ ደንብ ሀሳብዎን በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ላይ ማስፈር ይችላሉ። ንግግሩ ለትውስታ ቀርቧል፤ መልካም ንባብ።

***

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች

ክቡራትና ክቡራን!

ሀገራችን ኢትዮጵያ በመንግስት አስተዳደር ስርዓቷ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በምታከናውንበት በዚህ ታሪካዊ ቀን በተከበረው ምክር ቤት ፊት ቀርቤ ይህንን ንግግር ለማድረግ ስለበቃሁ የተሰማኝን ልዩ ክብር ለመግለጽ እውዳለሁ።

ከሁሉ አስቀድሜ፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአገራችን ለተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የመፍትሄ አካል ለመሆን፤ የሀገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ በአዲስ አመራር ሊጠበቅ ይችላል ብለው በማሰብ፣ ለአህጉራችን ምሳሌ በሆነ መልኩ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ላሸጋገሩት ለክቡር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከፍ ያለ አክብሮቴን እገልጻለሁ። በተመሳሳይ የመንግስታዊ ስልጣን ሽግግሩ ያለ እንከን እንዲከናወን ልዩ ሚና ሲጫዋቱ ለቆዩት ሁሉ በመላው ህዝባችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ዕለቱ ለሀገራችን ታሪካዊ ቀን ነው!

በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር እድሎችን አግኝተን ብዙዋቹን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል። አሁንም፣ ይህ የስልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ እድል ነው፤ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል።

ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ እድልኦ ለመላው ዜጎች ይደረስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ … ይደክማሉ።

በሀገር ውስጥና በውጪ ሆነው ስለ ሀገር አድነትና ሰላም … ስለፍትህና እኩልነት … እንዲሁም ስለብልጽግና ይጮሃሉ … ይሞግታሉ … ይሟታሉ።

ይህ የሥልጣን ሽግግር ሁለት አበይት እውነታዎችን የሚመላክት ነው። ክስተቱ፣ በአንድ በኩል በሀገራችን ዘላቂ፤ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ የህገ-መንግሥትታዊ ስርዓት መሰረት ስለመጣላችን ማሳያ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜው የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና በህዝብ ፍላጎት፤ ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ሥርዓት እየገነባን መሆኑ ያመለክታል።

ወቅቱ ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው!

መሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመሩን አጥብቆ በመያዝ ሀገራችንን ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ባስተዳደረበት ወቅት በሁሉም መስክ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ህገ-መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ገንብቷል።

ዓለም በአንድ በኩል በጥሞና፣ በአግራሞትና በጉጉት በሌላ በኩል ደግሞ በስጋት እየተመለከተው ያለ ሀገራዊ ለውጥ ላይ እንገኛለን። ያሳካናቸው በርካታ ድሎች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መቀረፍ የሚገባቸው በርካታ ጉድለቶች እንዳሉም እናምናለን።

ከስህተቶቻችን ተምረን ወደ ደፊት በመራመድ ማተኮር ያለብን ጉዳይ የተሻለች ሀገር ለሁላችንም በመገንባቱ ላይ ነው። ዋናው ቁም ነገር፤ አገራችንን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሸጋገሩ እና አንድነቷን ጠብቃ የምትቆይበትን ሁኔታ በቀጣይነት እያረጋገጡ መሄዱ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን እውነታ በጊዜያዊ ችግሮች ተሸንፎ መውደቅን ሳይሆን ፈተናዎችን ወደ ዕድልና መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ድል መቀዳጀትን ነው። ትላንት፣ አባቶቻችን በመተማ፣ በማይጨውና በካራ ማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆይዋት አገር አለችን። እኛ እድለኞች ነን። 

ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንን እናውቃለን። በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ህዝብ ነን። ህብረታችን ለዓ ለም ምሳሌ መሆን ይችላል። ጠላቶቻችንን አንበርክኳል። ሉዓላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይ ለሌሎች ህዝቦችም የነጻነት ትግል አርአያ ሆኗል። ማንነታችንን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳትነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣የተዋደደ እና የተዋሀደ ነው!

አማራው በካራ-ማራ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራ-ማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራዋይ በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉል፣ ወላይታ፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሀዲያው እና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል።

አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ ሀገር እንሆናለን። የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ስጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን።

ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!

በአንድ ሀገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሀሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመስርተን መግባባት ስንችል የሀሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሀሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሄ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ።ስንደመር እንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም… አገር ይገነባል። 

የኔ ሀሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብን ያፈርሳለ። ያለችን ኢትዮጵያ ነች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊ አንድነት ይበልጣል። አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝሃነታችንን በህብረ-ብሔራዊነት ያደመደቀ መሆን አለበት።

እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነጻነት ያስፈልገናል፣ ይገባናልም!

ዲሞክራሲ ለኛ ባዕድ ሃሳብ አይደለም። በዓለም ውስጥ በብዙ ማሕበረሰቦችና ሀገራት ዲሞክራሲ በማይታወቅበት ዘመን በገዳ ሥርዓታችን ተዳድረን ለዓለም ተምሳሌት ሆነን፣ ኖረናል። አሁንም ዲሞክራሲን ማስፈን ከየትኛውም ሀገር በላይ ለኛ የሕልውና ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን። ዲሞክራሲ ያለነጻነት አይታሰብም።

 ነጻነት ከመንግስት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም። ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንሱ ሰው የተፈጥሮ ጸጋ እንጂ። ነጻነትን በዚህ መልኩ ተረድቶ እውቅና የሰጠውን ህገ-መንግሥታችንን በአግባቡ መተግበር፣ የሰባዓዊ እና ዲሞክራዊ መብቶች በተለይም ሃሳብን የመግለጽ፣ የመሰባሰብና የመደራጀት መብቶች በሕገ-መንግሥታችን መሰረት ሊከበር ይገባል።

 የዜጎች በሀገራቸው የአስተዳደር መዋቅር በዲሞክራሲያዊ አግባብ በየደረጃው የመሳተፍ መብትም ሙሉ በሙሉ እውን መሆን አለበት። ሁላችንም መገንዘብ ያለብን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መደማመጥን ይጠይቃል። ሕዝብ አገልጋዩን የመተቸት፣ የመምረጥ፣ የመጠየቅ ሙሉ መብት አለው።

መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ ነው። ምክንያቱም ገዥ መርሃችን የህዝብ ሉዓላዊነት ነውና። በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ፣ የመጀመሪያው የመጨረሻውም መርህ፣ በመደማመጥ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ የጋራችን፣ የኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉም ድምጽ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን።

ዲሞክራሲ ሲገነባ መንግሥት የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ማክበር አለበት። ዲሞክራሲን ከዜጎች ሰላማዊ እንቅስቀቃሴና ከመንግስት መሪነት፣ ደጋፊነትና ሆደ ሰፊነት ውጭ ማዳበር አይቻልም። በመሆኑም መንግሥት የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓገል በጽናት ይሰራል።

በተመሳሳይ ዜጎች ሀሳባቸውን ሲገልጹ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሆን ይገባዋል። የራስን ዲሞክራሲያዊ መብት እየጠየቁ የሌለውን መብት መጋፋት እርስ በእርሱ ይጣረሳል፤ ዲሞክራሲያንም ያቀጭጫል። 

መንግስት ህግን ማክበር አለበት፤ ማስከበርም ግዴታ ነው፤ ታጋሽነትም ኃላፊነቱ ነው። የመንግስት ታጋሽነት ሲጓደልም ዲሞክራሲ ይጎዳል። በሁለቱም አካሄድ የምንናፍድቀው ዲሞክራሲ ሊመጣ አይችልም።

በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የህግ የበላይነት መስፈን ይገባዋል። የህግ የበላለይነትን ለማስፈን በምናደርገው ደትግል መርሳት የሌለብን ቁም ነገር ሕዝባችን የሚፈልገው የሕግ መኖርን ብቻ ሳይህን የፍትህ መረጋገጥንም ጭምር ነው።

የሕዝብ ፍላጎት ከፍትህ የተፋታ ደረቅ ሕግ ሳይሆን፣ በፍትህ የተቃኘ፣ ለፈትህ የቆመ የሕግ ስርዓትን ነው። የሕዝብ ፍላጎት የሕግ አስከባሪ ተቃማት ገለልተኛና ለፍትህ ታማኝ፣ ለዜጎች መብት ቀናኢ እንዲሆኑ ነው። 

ሕግ ሁላችንንም እኩል የሚዳኝ መሆን አለበት። እንዲህ ሲሆን ሕግ በተፈሮ ያለንን ሰብዓዊ ክብራችንን ያስጠብቅልናል። ይህን እውነታ በመረዳት በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ነጻነትና ፍትህ እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ያለውን ክፍተት እንሞላለን።

ለሰላም መሰረቱ ፍትህ ነው። ሰላም የግጭት አለመኖር ብቻ አይደለም። ሰላም በመግባባት ላይ የተመሰረተ ጽኑ አንድነታችን ነው፣ ሰላም- መተማመናችን ነው። ሰላም-በሁላችንም ፈቃድ ዛሬም የቀጠለ የአብሮነት ጉዞችን ነው። ሰላም አለመግባባትና ተቀርኖዎችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት የሚያስችል መንገድና ግባችን ነው።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ

ክቡራትና ክቡራን

ያለንበት ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ በቀውስ ውስጥ ያለበት፣ ብዙ የየራሳቸው ፍላጎትና ዓላማ ያላቸው ኃይሎች የሚራኮቱበት፣ ውስብስብ መጠላለፍ በቀጠናው ያለበት ወቅት ነው።

በዚያው ልክ ደግሞ በደም፤ በባህል፣ በቋንቋ እና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ያለንበት አካባቢ ነው የውጭ ግንኙነታችንን በተመለከተ ሀገራችን የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት፣ የአፍሪካ ህብረት መስራችና መቀመጫ፣ የቀድምት ዓለምአቀፍ ተቋማት መስራችና በአለም አቀፍ፤ በአህጉር አቀፍ እንዲሁም ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ጉልህና ገንቢ ሚና የምትጫወት ሀገር ናት። ይህንኑ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተውን ፖሊሲያችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።

ከአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ወንድሞቻችን ጋር በአጠቃላይ፤ እና ከጎረቤቶቻችን ጋር በተለይ በችግርም በተድላም አብረን እንቆማለን። ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለአመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። የበኩላችንንም እንወጣለን። በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለት ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለለጽኩ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስዱ በዚሁ አጋጣማ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ

የተከበራችሁ የም/ቤት አባላት

ክቡራትና ክቡራን

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕዝባችንን ብሶት ካጋጋሉ ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ሙስና አንዱ ነው። ሙስናን ጸረ-ሙስና ተቋም በመመስረት ብቻ መከላከል እንደማይቻል ተረድተን፤ ሁላችንም፣ ኢትዮጵያችን፣ አንዱ ሰርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ በትህትና እጠይቃችኋለሁ።

ትናንት የተፈጠረን ሃብት ከሌላው በመቀማት ሂሳብ ለማወራረድ የሚተጋ አገርና ሕዝብ ወደፊት ለመራመድ አይችልም። ገበታው ሰፊ በሆነበት፣ ሁሉም ሰርቶ መበልጸግ በሚችልበት ኢትዮጵያችን አንዱ የሌላውን ለመንጠቅ የሚያስገድድ ይቅቅርና የሚያሳስብ ምንም ምክንያት ይለም። ይልቁንም ወቅቱ የፈጠረልንን ልዩ አጋጣሚና ሀገራዊ አቅማችንን አቀናጅተን የእጥረትና እጦት አስተሳሰብን በማስቀረት ለጋራ ብልጽግና እንትጋ። 

ታዋቂው የህንድ የነጻነት ንቅናቄ መሪ ማህተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት እንደተነገረው፣ አገር ለሁሉም የሚሆን በቂ ሀብት አላት፤ ሁሉም እንደልቡ የሚዘርፈው ሀብት ግን ሊኖራት አይችልም። አሁን በጀመርነው አዲስ ምዕራፍ፣ ዘረፋን፣ የሀብት ብክነትን እና የተደራጀ ሙስናን፣ መላው ህዝባችንን በሚያሳትፍ እርምጃ ለመመከት ሌት ተቀን እንተጋለን።

ክቡራትን ክቡራን

ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ባስመዘገባችው ፈጣን እድገት የተነሳ በድህነት ቅነሳ፣ በመሰረተ-ልማት ግንባታ፣ በሰው ሀይል ልማት እና በመሳሰሉት ያገኘናቸው ስኬቶች ለሁሉም የሚሰታዩ ናቸው።

ከዚህ አኳያ መንግሥት የዋጋ ንረት እና የውጪ ምንዛሬ ዋጋን ለማረጋጋ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለመጠበቅ፣ ለኢኮኖሚ የሚቀርበውን የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት እና አካታችነትን ለማስፋት፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝትን እንዲሁም ቁጠባን እና ኢንቨስትመንት ለማበረታታት፣ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የሕዝቡን የነፍስ ወከፍ ገቢ ለማሳደግ እንዲሁም አስከፊ ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የፖሊሲ እና የትግበራ አርምጃዎችን ወስዷል።

በአንፃሩ፣ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት የኢኮኖሚ እድገቱን እና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋቱን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ተከስተዋል። ከእነዚህም ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ የውጪ ንግድ በምንፈልገው መጠን አለማደጉ፣ ይሄን ተከትሎ የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ የውጪ እዳ ጫና እና የሀገር ውስጥ ቁጠባና ኢንቨስትመንት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ናቸው።

በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረየታች ቢሆኑም ዘርፉን በተገቢው ሁኔታ በቴክኖሎጂ መደገፍ ባለመቻሉ እንደ ሀገር ማግኘት የሚገባንን የኢኮኖሚ ትሩፋት ሳናገኝ ቆይተናል።

እንደ ደትልቅ ሀገር እና ሕዝብ ከምናስበው የስኬት ጫፍ ላይ መድረስ የምንችለውና ችግሮቻችንን የምንፈታበትን ዋና ቁልፍ የምናገኘው በትምህርት እና በትምህርት ብቻ እንደሆነ በማመን መንግሥት ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም በተለይ የትምህርትን ጥራት ከማስጠበቅ አንጻር እጅግ ብዙ የቤት ሥራዎች ከፊታችን እንዳሉ በውል በመገንዘብ በርካታ ስራዎች ይሰራሉ።

የትምህርት መስፋፋት ይበል የሚያስኝ የመንግስታችን ስኬት ቢሆንም ይህ የትምህርት ሽፋን እድገት በጥራት እስካልተደገፈ ድረስ ልፋት ጥረታችን ሁሉ የምንተጋለትን ውጤት ሊያመጣልን አይችልም። በመሆኑም ከመጀመርያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉትን የአውደደቀት አለሞቻችንን በጥራት ላይ አትኩረው እንዲሰሩ መንግሥት በፍጹም ቁርጠኝነት ይረባረባል። በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቻችን እና ከቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች የሚያወጡት ተማሪዎቻችን ከሚገበዩት እውቀት የሚነጻጸር ከህሎት እንዲኖራቸው ከፍተኛ ጥራት ይደረጋል።

እነዚህንና ሌሎቹንም ችግሮቻችንን ለመቅረፍ የሁለሰደተኛውን የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን የሁሉት ዓመት ተኩል አፈጻጸም በመገምገም አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ለማስቀጠል እንታገለን።

ውድ የሀገራችን ወጣቶች

ኢትዮጵያ የናንተ ነች፣ መጭውም ዘመን ከሁሉ በላይ የእናንተ ነው አሁንም አገሪቷን በመገንባት ግንባር ቀደም ሆናችሁ መሳተፍ ይኖርባችሀል። የወጣቱ ጥያቄ የኢኮኖሚ የእኩል ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲና የፈትህ ነው ብለን እናምናለን። የሁሉም ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ማሕበራዊ ፍትህ እና ፖሊቲካዊ ተሳትፎ ከማሳደግ አጻር ክፍተቶች ነበሩ።

አገራችን፣ ጥሩ የሚባል ኢኮኖሚያዊ እድገትን እያስመዘገበች እንደሆነ ቢታወቅም እድገቱ በቅርፅና በይዘት ተለዋዋጭ የሆነውን የወጣቱን ትውልድ ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ የሚያረካ አልነበረም። ይህም፣ ህዝባችንን ለብሶት እንደደረገው እንገነዘባለን። ያለውጣቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት አገር የትም ልትደርስ እንደማትችልም እንረዳለን።

ኢትዮጵያ ለወጣቶቿ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ፣ ተስፋ የምታስቆርጥ አገር እንዳትሆን የምንችለውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ። በሚቀጥሉት ጊዜያት ለወጨጣቱ የሥራ እድል መፍጠር ብቻቀ ሳይሆን ወጣት ባለሀብቶች በብዛት እንዲፈጠሩ እንሰራለን። 

ለዚህ እንቅፋትና መስናክል ለሚሆኑ አመላካከቶችና የተንዛዙ አድሏዊ የሆኑ አሰራሮችን አስወግደው ፍትሃዊ የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት እንዲኖረን መንግሥት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። መርሳት የሌለብምን ሀቅ ግን ለራሱም ሆነ ለሀገሩ በሥራውና በጥራቱ ሀብት የሚፈጥረው ወጣቱ እራሱ መሆኑን ነው።

ውድ የኢትዮጵያ ሴቶች

በብዙ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያን ገንብታችሁ፣ ታሪክ ሰርታችሁ፣ ትውልድ ቀርጻችሁ ዛሬ ላይ ደርሰናል። በትግላችሁም የተሻለች ሃገር እንድትኖረን ብዙ መስዋዕትነት ከፍላችኋል። 

ትግላችሁ የፍትህ ትግል ነው፣ ትግላችሁ ክቡር ትግል ነው፣ ትግላችሁ ትግላችን ነው። መንግስት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና በሃገራችን ሁለንተናዊ የእድገት ግስጋሴ ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኝ ቢሆንም አሁንም ከሰራነው ይልቅ ያልሰራናቸው ስራዎች እጅግ እንደሚበዙ እናምናለን። 

በመሆኑም በቀጣይ የሃገራችን ሴቶች ተፈጥሮ እና ኑሮ የሰጧችሁን በረከቶች ተጠቅማችሁ ለሃገራችን እድገት እና ብልጽግና እንዲሁም ለፖለቲካችንም ስምረት አዎንታዊ ሚና እንደምትጫወቱ ተስፋዬ የላቀ ነው።

አገራዊ ማንነታችን ያለ እናንተ ያለ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ምንም ነው። አገሪቷን የገነቡ፣ ያገለገሉ፣ ያቆሙ ሴቶችን እውቅና በመንፈግ ሀገራዊ ትንሳኤን ማረጋገጥ አይቻልም። መንግስታችን ለሴቶች መብትና እኩልነት የሚቆመው፣ ለሴቶቻችን ውለታ ለመዋል ሳይሆን ለሁላችንም ብለን ነው። ግማሽ አካሉን የረሳን ሀገር ሙሉ የሀገር ስዕል ይኖረው ዘንድ ከቶ እንደማይችልና ወደፊትም እንደማይራመድ መንግስት በውል ይገነዘባል። 

በመሆኑም መንግስታችን ከዚህ ቀደም ከነበረው ፍጥነት እና የትግበራ ስኬት በላቀ መልኩ ለሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት ይሰራል።

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

ጥሪ የተደረገላቸሁ እንግዶች

ክቡራትና ክቡራን

ችግሮቻችን በርካታ እና ፋታ የማይሰጡ ናቸው።

የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል አለመኖር፣ ሥር የሰደደ ድህነት፣ የተደራጀ የሙስና እና ብልሹ አሰራር መስፋፋት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ተደማምረው ሰፊና ውስብስብ ፈተና ደቅነውብናል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ወገኖቻችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው ለመፈናቀል፣ ለህይወት እና ንብረት መጥፋት ተዳርገው እንደነበር ይታወሳል። ዜጎች በሃገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እና ሃብት የማፍራት መብታቸው መከበር አለበት። 

በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንዲያበቃና ዳግም እንዳይፈጠር መሥራት ይኖርብናል።ችግሮቻችንን፣ ተለያይተን ቀርቶ ተባብረን እና ተዋደንም ለመፍታት ዓመታት ያስፈልጉናል። በመሆኑም የባከነውን ግዜ በማካካስ ወደፊት መጓዝ እንችል ዘንድ በአዲስ መንፈስ መረባረብ ይጠበቅብናል።

ሁሉም ችግሮቻችን በአንዲት ጀንበር ሊፈቱ አይችሉም። ነገር ግን የጀመርነውን የተሻለች ሀገር የመገንባት ሂደት ማፋጠን እንችላለን። የተሻለች አገር መገንባት የሚያስችል ጠንካራ ተነሳሽነት አለ። ጠንካራ አገር ለመገንባት ሁላችንም ሀላፊነት አለብን። 

እንደ ተለያየ አገር ዜጋ በባእድነት እና ባይታወርነት ሳይሆን፣ ሁላችንም እንደ ባለቤቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን መጓዝ ይጠበቅብናል። ይህ ሲሆን ስንወድቅም፣ ስንነሳም በጋራ ይሆናል። በቀሪው የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዓመታት ቀሪ የልማት መርሀ-ግብሮቻችንን በፈጠነ ጊዜ ለማሳካት ጥረት ይደረጋል። ከመደበኛው የሥራ ሰዓታችን በሚሻገር ጊዜ፣ ከፍ ባለ ፍጥነትና ተነሳሽነት በመሥራት በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የደረሰብንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ለማካካስ አገራዊ ንቅናቄ እንድናደርግ ከአደራ ጭምር መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ

የተከበራችሁ የም/ቤት አባላት

ክቡራትና ክቡራን

በውጭ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለስራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለውም ለዚህ ነው። ሁላችሁም በታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁ እና የትም በሚከተላችሁ የሀገራችሁ የጨዋነት ባህሪ የኢትዮጵያና የዕሴቶቿ እንደራሴዎች ናችሁ።

አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው ነገር ግን እጅግ በበለጸጉ ሃገራት ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙት ስለሃገራችሁ ቁጭት ሳይሰማቹ አይቀርም። ሁላችንም ውስጥ ያ ቁጭት አለ። እንደገሀር ያለንን ሃብት አሟጠን ለመጠቀም የምናደርገው ጥረት በቂ ሳይሆን ሲቀር መቆጨታችሁ አይቀርም። 

መቆጨትም አለባችሁ። ይሄንንም ሁኔታ ለመለወጥ ለሁላችንም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ ሀገር አለችንና እውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ ሃገራችሁ መመለስና ሃገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን። 

በውጭ ሃገራት ኑሯችሁን ላደረጋችሁትም ቢሆን በማንኛውም መልኩ በሃገራችሁ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑና ሃገራችንን በሙሉም መልክ ለመቀየር ለምታደርጉት አስተዋጽኦ መንግስት ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።

ውድ የልማት አጋሮቻችን

እስካዛሬ ባደረግነው የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ከጎናችን የቆማችሁ የልማት አጋሮቻችን የአገራችን ጥብቅ ወዳጆች እንደሆናችሁ እንገነዘባለን። የአገራችንን ልማት እና ሰላም ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት እንደ ወትሮ ሁሉ ከጎናችን እንደምትቆሙ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው!

ሀገራችን ፍትህ፣ ነጻነትና ሰላም የሰፈኑባት፣ ዜጎችዋ በሰብዓዊነት የሚተሳሰቡት፣ በእህት/ወንድማማችነት የተሳሰሩባት እንድትሆን እንፈልጋለን፡፡ ይህ ህልማችን እውን የሚሆነው ከእንቅልፋችን ነቅተን ስንሰራ ነው፡፡ መመኘታችን መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ምኞታችን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ መሥራት፣ መትጋት፣ መታገል ይጠበቅብናል፡፡ በመጀመሪያ ሥራችን ልናደርገው የሚገባንና ትግላችን ማተኮር ያለበት ራሳችን ላይ ነው፡፡

አመለካከቻችንን ከጥላቻ፣ ከቂም በቀል ስሜትና ከዘረኝነት ማጽዳት ይገባናል፡፡ በብሔር፣ በጾታ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በኃይማኖት… ወዘተ ያሉንን ልዩነቶች እንደ በረከትነታቸው በፍቅር በማስተናገድ ከልዩነቶቹ የሚነሳ አለመግባባት ቢኖር እንኳ ከፍትህ እንጂ ከበደል ጋር ባለመተባበር ሞራላዊ እይታዎቻችንን ልናስተካክል ይገባል፡፡ ፍትህ ዋናው መርሃችን ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርና ክብር የሞራል መልህቃችን ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ሰርተን የማናገባድደው፣ ሁሌም ልፋት፣ ትግል የሚጠይቅ የእድሜ ዘመን ሁሉ የቤት ሥራ ነው፡፡

ሀገራችን በአሁሉ ወቅት ለደረሰችበት ምእራፍ በርካታ ትውልዶች መስዋእት ሆነዋል፡፡

አዲሱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን እውን እንዲሆንም አእላፎች ተሰውተዋል፡፡

ታዳጊውን ዴሞክራሲያችንን ለማዳበር ግን ተጨማሪ የህይወትም ሆነ የአካል መስዋእትነት አያስፈልገንም፡፡ ባለፉት ዓመታት እንደመንግሥትም እንደ ዜጎችም ከዴሞክራሲ ባህላችን አለመዳበር ጋር ተያይዞ በታዩብን እጥረቶች በዜጎቻችን ህይወት እና በግልም በጋራም ንብረቶቻችን ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሳል፡፡ ይህንን ሁላችንም ማስቀረት እንችልና ይገባንም ነበር፡፡

በተለያየ ጊዜ፣ መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኛች፤ በቅጡ ሳይቦርቁ ህይወታቸውን ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፤ ለስነልቦናዊና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ 

እንዲሁም ሰላም ለማስከበርና ህገመንግሥታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ህይወታቸውን ላጡ የፀጥታ ኃይሎች አባላት ለከፈሉት መስዋእትነት ያለኝን አድናቆትና አክብሮት ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ህዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍ እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ክቡራን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፡-

ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር እንደተቃዋሚ ሳይሆን እንደተፎካካሪ፣ እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፡፡ 

ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር በመንግስት በኩል ጽኑ ፍላጎት ያለ በመሆኑ ስለሰላምና ፍትህ በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና ሀገራዊ ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

የሀገራችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ በሁሉም ደረጃ የምትገኙ የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎች፣ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ በገጠርም ሆነም በከተማ የምትገኙ የተለያየ ሞያ ባለቤቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ ዋቄፈታዎች እንዲሁም ሌሎች ኃይማኖቶችን የምትከተሉ ወገኖች፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምእራብ የምትገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ሁላችንም የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት እንረባረብ! አገራችንን ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት እንትጋ! ዘረኝነትና መከፋፈልን ከአገራችን እናጥፋ! የተማረና በምክንያት የሚከራከር ዜጋ እንፍጠር!

የዛሬው እለት በአኩሪ ኢትዮጵያዊ ወኔ የተጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሰባተኛ ዓመት ነው፡፡ በዚህ ግድብ ግንባታ የታየው አንድነት እና መሰባሰብ የሀገራችንን ችግሮች በሙሉ መቅረፍ እና መሻገር እንደምንችል ያረጋገጠልን በመሆኑ ይህንኑ መንፈስ ይዘን ከግድቡ መጠናቀቅ ባሻገር የሀገራችንን ብልጽግና እስከምናረጋግጥበት ከፍታ ድረስ እንድንዘልቅ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በመጨረሻም በዚህ ወቅት ሀገሬን እና ህዝቤን ለማገልገል ይህንን ከባድ ኃላፊነት ስቀበል አመሰግናቸው ዘንድ የሚገቡኝን አካሎች እንዳመሰግን ትፈቅዱልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ፤

በመጀመሪያ ለዚህ ኃላፊነት የመረጡኝና እምነት የጣሉብኝ ድርጅቴ ኢህአዴግን እና የአገሬን ህዝብ በተለየ አክብሮት እና ፍቅር አመሰግናለሁ፡፡

ሁለተኛ የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ እንዲህ ከፊታችሁ እንደምቆም የምታውቅ እና ይህንን ሩቅ ጥልቅ እና ረቂቅ ራእይ በውስጤ የተከለች፣ ያሳደገች እና ለፍሬ ያበቃች አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት እንዳመሰግን በትህትና እጠይቃለሁ….. ይህች ሴት እምዬ ናት፤

እናቴ ከሌሎቹ ቅን የዋህ እና ጎበዝ ኢትዮጵያውያን እንደ አንዶቹ የምትቆጠር ናትና ቁሳዊ ሀብት ብቻ ሳይሆን አለማዊ እውቀትም የላትም፡፡ በእናቴ ውስጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ እናቶች ዋጋ እና ምሥጋና እንደመስጠት በመቁጠር ዛሬ በህይወት ካጠገቤ ባትኖርም ውዷ እናቴ ምሥጋናዬ ከዐፀደ ነፍስ ይደርሳት ዘንድ በብዙ ክብር ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡

ሌሎች ኢትዮጵያውያን እናቶቼ በልጆቻቸው የነገ ራእይ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው በመገንዘብ ነገ ለሚያጥዱት መልካም ፍሬ ዛሬ ላይ የሚዘሩት ዘር ዋና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለሚከፍሉት መስዋእትነት ያለኝን በምንም የማይተካ አድናቆት ምስጋና እና ክብር በብዙ ልባዊ ፍቅር ሳቀርብ በቀጣይም ልጆቻችን የዚህች ሀገር ህዳሴ እንዲረጋገጥ ዋና ተዋንያን መሆን እንዲችሉ እናታዊ አይተኬ ሚናችሁን እንድትወጡ አደራ በማለትም ጭምር ነው፡፡

ሦስተኛ የሚስቶች ስኬት ሁለት-ሦስት ነው፡፡ ሁለት ሲሆን፣ አንዱ የራሳቸው ሌላው የባላቸው፡፡ ሦስት ሲሆን ደግሞ የልጆቻቸውም ይጨመርበታል፡፡ አንዳንዴ ድል ስኬታቸው ከዚህም ይሻገራል፡፡ የእናቴን ራእይ ተረክባ በብዙው የደገፈችኝና የእናቴ ምትክ የሆነችልኝ ውዷ ባለቤቴ ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ከነዚህ ሚስቶች ተርታ ትመደባለችና እጅግ አድርጌ ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም ከትግል ጓዶቼ እና በዝለት ብርታት፤ በድካም ጊዜ ኃይል ከሆኑኝ የቅርብ-የሩቅ ወዳጆቼ ውጪ ዛሬ እኔ ከፊታችሁ መቆም ባልቻልኩ ነበር፤ ለሁላችሁም ከልብ የመነጨ ምሥጋና አቀርባለሁ፡፡

“ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!”

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!

አመሰግናለሁ!!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top