ዜጎች በማንነታቸው ከመሞት፣ ከመሰደድና ከመሰቃየት የማይታደግ ሹም ግብር ምን ብሎ ይሰበስባል? ለሀዘን መግለጫስ እንዴት ቪ8 መኪናና ደመወዝ ይሰጣል?
(ስናፍቅሽ አዲስ- ድሬቲዩብ)
ሞት በዛ፤ መንግሥት እንደ ሌለው ህዝብ እየሞትን ነው፡፡ አንድ ቦታ ላይ ብዙ ጊዜ ደጋግመን ስንሞት የሚነግረን የሚታደግ አካል የሌለን ህዝቦች መሆናችንን ነው፡፡ የሀገራችንን ውጥረት ስለማንረዳ አይደለም፡፡ ግን አንድን አካባቢ እያስተዳደርኩ ነኝ የሚል መንግስት ለማስተዳደሩ ማስረጃው ምንድን ነው?
ከመንግስት አካል የሚጠበቀው አንድ ችግር አንድ ህዝብ ላይ ደጋግሞ እንዳይከሰት መጠበቅ ነው፡፡ የታደሉት መሪዎች ህዝባቸውን ከተፈጥሮ አደጋ ጭምር ይጠብቃሉ፡፡ ያልታደልነው በየቀኑ በአንድ ገዳይ ስም ብዙ ሰው ሲሞት መንግስትም እንደ ህዝብ ከንፈር ይመጣል፡፡
ከንፈር ለመምጠጥ ምን መታጠቅ ያስፈልጋል? ከንፈርን በመምጠጥስ የሰው ህይወት እንዴት መታደግ ይቻላል? መንግስት በመጠጠው ከንፈር ልክ ቢሆን ኖሮ እኮ ዛሬ እንኳን የሰው ልጅ ሞት ጉልበተኛ ደሃውን በጥፊ ባልመታው ነበር፡፡
ግፍ በዝቷል፡፡ ግፍን ለማስቆም፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበር፣ ዜጎችን ለመጠበቅ አለመቻል ብቻውን መንግስት አለመሆን ነው፡፡ ደሃ ለምን ይገብራል? ግብር መክፈል እኮ ለሚጠብቅ መንግስት ቀለቡን መስፈር ነው፡፡ አሁን ግን እየሆነ ያለው ሳይሰራ የሚባለው ሹም በዛ፡፡
አንድ ሹም አስተዳድረዋለሁ በሚለው አካባቢ የበላይነቱን ገዳይና ሽፍታ ከያዘው ሁሌም እንደ ህዝብ እያለቀሱና እያወገዙ በአንዳንድ ወገኖች ደግሞ የለም ግድያው ላይ እጁ ሳይኖርበት አይቀርም በሚል እየታሙ እስከመቼ ይኖራል?
መግለጫ ቀላል ስራ ነው፡፡ ገዳዮችን ማስፈራራትማ ማንም ያደርገዋል፡፡ ገዳዮችን አደብ ማስገዛት ካልተቻለ ለመኮነንና ሟችን ነፍስ ይማር ለማለት ደመወዝ መቀበል ምን ያደርጋል? በቪ8 መኪና የሚንፈላሰሰው ባለስልጣን ምንድን ነኝ ብሎስ ያስባል? መሪ እረኛ ነው፤ ህዝቡን ከተኩላ ያስጥላል፡፡ ተኩላ የበላውን የሚቀጥር እረኛ ምን ስጠብቅ ውዬ መጣሁ ይላል? የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ነገር እንዲያ ሆኖብናል፡፡
በየቀኑ ሞት ነው፡፡ እዚያው ትናንት ሰዎች የሞቱበት ቦታ ዛሬም ሰው ይሞታል፡፡ ቦታውን ሳይቀይር የሚፈጸም ግድያን ማስቆም ካልተቻለ ወይ ህዝቡን ገዳይ ይምራው፡፡ ህዝቡን እንዳሻው የሚያደርገው ሌላ መሪህ ነኝ እያለ ጫንቃው ላይ ቁጭ ብሎ የሚጫወትበት መከረኛ ሆኗል፡፡
አሁን ኦሮሚያን እየመራ ያለው መንግስት ባለፉት አመታት ክልሉን ከመራው ሁሉ በባሰ በየቀኑ አስክሬን እየቆጠረ፣ ገዳይን እያወገዘ ሞትን ባለማስቆም የታወቀ ሆኗል፡፡ አንዳንዶች ማማት ጀምረዋል፡፡ አለበት ይሉታል፡፡ ጥርጣሬያቸው ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በከፋ መረጋጋት ያቃተው፣ ሰው የሞሞትበት፣ ፍትህ የጠፋበት ሆኖ ለምን ቀጠለ የሚለው ጥያቄ መልስ ስላጣ ነው፡፡
አሁንም የፌዴራሉ መንግስት ደጋግሞ ሊያጤነው የሚገባ ነገር አለ፡፡ ክልሉን የሚመራው አካል ምን መራሁ እያለ እንደሆነ ይታይ፣ እንዳቃተው ለመረዳት ሌላ ሳይንስ አይፈልግም፤ የኦሮሚያ ክልል በክልሉ የሚፈጸምን ግድያና ጭፍጨፋ የሚያወግዘው እንደ ሀረሪ እንደ ጋምቤላ እንደ ሱማሌና እንደ አፋር ክልል ነው፡፡ ታዲያ ማን ነው የሚያስቆመው? ባለመቻሉስ ስልጣኑን የሚለቀው ማን ነው? ያሳዝናል፡፡