ዘጠና በመቶው ተቀጥተዋል!!
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በተከሰተዉ ሁከት የግድያ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች እንደየተሳትፏቸው ከ1 እስከ 22 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ አካባቢዎች የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በተከሰተዉ ሁከት እና ብጥብጥ ዉስጥ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በፈጸሙ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ በማድረግ በ6 ዞኖች በ3,373 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ በበመስረት በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡
በዚህም መሰረት ከላይ ከተጠቀሰው የተከሳሾች ቁጥር ውስጥ 90 በመቶ በሚሆኑት ላይ የቅጣት ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከተሰበሰቡት ማስረጃዎችም መካከል ከ90 በመቶ የማያንሱ ምስክሮች በችሎት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን መስጠት ችለዋል፡፡
በህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ የተከናወኑ ተግባርትን እና የተገኙ ውጤቶችን ክስ ስንመሰርት እንዳደርግነው ሁሉ በቅርብ ቀን ሰፊ መግለጫ የምንሰጥ ሲሆን ከወንጀል ድርጊቶቹ መካከል አንዱን በተመለከተ ፍርድ ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ ከዚህ እንደሚከተለው ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
በተከሳሾች እነ ጂሎ በዳሶ (35 ሰዎች) መዝገብ ከቀረቡት 11 ተከሳሾች መካከል፡-
2ኛ ተከሳሽ (ሀቢብ በሪሶ)፣ 5ኛ ተከሳሽ ( አማን አቤ)፣ 6ኛ ተከሳሽ (ሙስጠፋ ዋሪሶ) እና 8ኛ (ሮባ ኤዳኦ) የተባሉ ተከሳሾች በወንጀል ህግ አንቀጽ 240/3፣ 539(1ሀ) እና 690(1ለ) መሰረት በኦሮሚያ ብ/ክ/መ ምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ 01 ቀበሌ በቡድን በመሆን በቀን 23/10/2013 ዓ.ም. ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ሲሆን የሟች አቶ ገለታዉ አዉላቸዉ መኖሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ ሰብሮ በመግባት በአምስት (05) የቤተሰብ አባላት ላይ የግድያ ወንጀል በመፈጸም እና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ተሳትፈዋ በሚል እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ (ሮባ አማን)፤ 14ኛ ተከሳሽ (ከድር ራበቶ)፣ 16ኛ ተከሳሽ (አለሙ ነጋሽ) እና 17ኛ ተከሳሽ (ሚኪ ጉዬ) በወንጀል ህግ አንቀጽ 240/3 እና 690(1ለ) ስር ተከሰዉ ክርክር ሲደረግ ከቆየ በኋላ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀን 17/07/2013 ዓ.ም. በዋለዉ ችሎት የጥፋተኝነት ዉሳኔ በመስጠት የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከተቀበለ በኋላ እንደ ወንጀል ተሳትፎአቸው፡-
2ኛ ተከሳሽ (ሀቢብ በሪሶ) በ 20/ሀያ/ ዓመት ጽኑ እስራት
5ኛ ተከሳሽ (አማን አቤ) በ 22/ሀያ ሁለት/ ዓመት ጽኑ እስራት
6ኛ ተከሳሽ (ሙስጠፋ ዋሪሶ) በ 20/ሀያ/ ዓመት ጽኑ እስራት
8ኛ ተከሳሽ (ሮባ ኤዳኦ) በ 18 /አስራ ስምንት/ ዓመት ጽኑ እስራት
7ኛ ተከሳሽ (ሮባ አማን) እና 14ኛ ተከሳሽ (ከድር ራበቶ) በወንጀል ህግ አንቀጽ 488/1 እና 690/1ለ ስር እያንዳንዳቸዉ በ 1 (አንድ) ዓመት ከ ስምንት ወር ጽኑ እስራት እና 1000 ብር የገንዘብ መቀጮ፣
16ኛ ተከሳሽ (አለሙ ነጋሽ) እና 17ኛ ተከሳሽ (ሚኪ ጉዬ) በወ/ህግ አንቀጽ 488/1 / እና 690/1ለ/ ስር እያንዳንዳቸዉ በ 2 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በሙሉ ድምጽ ዉሳኔ ሠጥቷል፡፡
በዚህ እና በሌሎች መዛግብት ላይ በምስክርነት በመሳተፍ ለፍትህ ስርዓቱ ጉልህ ሚናችሁን ላበረከታችሁ ሁሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምስጋናውን ይገልጻል፡፡
በሂደቱ በተፈጠረ ከፍተኛ የስራ ቅንጅት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋዋሪ ችሎቶች ዳኞችን በማሰማራት እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ፖሊስ ኮሚሽን በምርመራ፣ ክስ እና ክርክር ሂደቱ ውስጥ ላበረከታችሁት ሚና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡(የፌ/ጠ/ዐቃቤ ሕግ)