ንጹሀንን በማሳደድና በማፈናቀል ጠብ የሚል መፍትሔ የለም!
(ሙሼ ሰሙ)
ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር የሚደርግ ትግል፣ የሌሎችን ዜጎች ሰብአዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በሕይወት የመኖር መብት በመርገጥና ንጹሃንን በመጨፍጨፍ ሊሳካ አይችልም። በመርህ ላይ ተመስርቶ ለመብት የሚታገል የነቃና የበቃ ሃይል፣ የሌሎችን መብት አክብሮ የራሱን መብት በተቀናጀ የጋራ ትግል ያስከብራል እንጂ፣ አቅመ ደካሞችን በመጨፈጭፍ ሰላም ይሰፍናል ወይም መብት ይከበራል ብሎ አያምንም።
ንጹሃንን የሚጨፈጭፍ ኋይል የፖለቲከኞች መጠቀሚያ መሳርያ እንጂ ሕዝባዊ የፖለቲካ ኋይል ሊሆን አይችልም።
ከሰሞኑ በየክልሉ እያየናቸው ያሉት እልቂቶች መገለጫው ከዚህ የሚዘል አይደለም። የየክልል አመራሮች በየድግሱና በየሰልፉ ባፈጀና ባረጀ የታሪክ ድሪቶ ላይ ተመስርተው በዘፈቀደ የሚያዘንቡት የጥላቻ፣ የማንቋሸሽና የብሽሽቅ ንግግር መሬት ላይ ሲወርድ ሕጻናት፣ አረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ከነቤተሰቦቻቸው እያሳረደና የቀቢጸ ተስፈኞች ሂሳብ ማወራረጃ ሰበብ ሊያደርግ እንደሚችል እየተረዳን ነው። የፖለቲከኞቻችን ገደብ የለሽ የጥላቻ ትፋትና ብሽሽቅ ከገደፉ አልፎ ሞልቶ በመፍሰሱም፣ የዜጎቻችን ደም በከንቱ እያፈሰሰ ነው።
ዛሬ በወንበር ላይ ስለናጠጥን፣ በታጠቀ የመንግስት ኋይል ጉያ ውስጥ ስለተከለልን፣ በቅጥር ጊቢ ስለተከበብን በኛ ተራ (Under You Watch) የተሰራ ግፍ የማያስጠይቀን መስሎን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሕግና ከሞራል በላይ የገዘፍን ስለመሰለን ብቻ ከሕግ ለጊዜው መሰወር ብንችልም፣ ከቶውንም ግን ለዘለቄታው ከዓለም ሕዝብ ፊት ማምለጥ አንችልም።
መንሰኤው ለማይታወቅና መቋጫ ለሌለው ተለዋዋጭ ጥያቄና ቅዠት፣ በሰበብ አስባቡ ለሚያገረሽ ግልፍተኝነትና ብስጭት፣ በየዕለቱ ንጹሃንን በመጨፍጨፋ፣ በማፈናቀልና በማሳደድ ጠብ የሚል መፍትሔ የለም። የነጻነት ትግል ይባል፣ ሽፍትነት ወይም ጀብደኝነት አሊያም “የፓለቲካ ማሃንዲሶች ሴሬ” ወይም የሰፈር ውስጥ ጠብ ክቡር በሆነው የሰው ሕይወት ላይ የሚቃጣ ተግባር ስለሆነ ሁሉንም በልኩ፣ በስርዓቱና በሕግ አግባብ ልናደርገው ይገባል።
መልዕክቴ ለሁሉም ክልሎች ይሄ ነው፣ ሁሉም ክልሎች በየትኛውም አካባቢ መጤ፣ ሰፋሪ፣ ነፍጠኛና ስደተኛ እየተባሉ የሚጨፈጨፉ ዜጎች ጉዳይ ሊያሳስበውና በጋራ ሊያወግዘው ይገባል። ማናችንም የዛሬ ታሪካችንን ይዘን ከሰማይ በድንገት ዱብ አላልንም።
ዛሬ ባይሆን፣ ትናንት አሊያም ከትናነት ወዲያ እንደማንኛውም ፍጡር ለወቅቱ መጤ ነበርን፣ ማናችንም አፈር ጠፍጥፈን፣ ተራራ ጠርበን፣ ወንዝ ቀይሰን፣ ጅረት አፍሰስ፣ ተረተር ገምሰን፣ ተፈጥሮን የገራንና የሰራን አይደለንም። ሁላችንም ዛሬም ወደፊትም የተፈጥሮ ስደተኞች ነን። እንጀራ ቆርሰን ለማደር፣ በሰው ሰራሽ ልዮነት በግፍ ማለቅ የለብንም።