ብጹዕ አቡነ እንጦንስ በአሰቦት ገዳም አካባቢ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ተመለከቱ
– በእሳት ማጥፋቱ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን አመሰገኑ፣አበረታቱ፣
ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው እና በአሰቦት ገዳም አካበቢ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት ሌት ተቀን በመረባረብ ላይ የሚገኙት የአሰበ ተፈሪና የአካባቢው ወጣቶችን ለማበረታታትና የእሳት ቃጠሎው ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት ዛሬ ጠዋት አሰቦት ገዳም የተገኙት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ እንጦንስ ገዳማውያን አባቶችንና የአካባቢውን ወጣቶች አሳቱን ለማጥፋት ለሚያደርጉትን ጥረት አመስግነዋል።
ከብጹዕነታቸው ጋር የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀኅሩያን ደረጄ ብርሀኑና የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን እሳቱን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት አድንቀዋል።ከቃጠሎው ጋር በተያያዘ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠርም ከዞኑ አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት አእየተሠራ እንደሆነ እና አስተዳደሩ በእሳት ማጥፋቱና በጸጥታ ማስከበሩ ሥራ ላይ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ብጹዕነታቸው ገልጸዋል ።
በተያያዘም በእሳት ማጥፋት ሥራው ላይ የአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ነዋሪ ህዝቦች ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ መሆኑን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል።ይሁንና በእሳወት ማጥፋት ሥራው ላይ ለተሰማሩ ወገኖች የሚሆን ከፍተኛ የመጠጥ ውኃ ችግር የገጠመ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ ሀገረ ስብከቱ የመጠጥ ውኃ ችግሩን ለማቃለል ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ቃጠሎው በአንድ አቅጣጫ ለጊዜው የጠፋ ቢሆንም በሙቀትና በንፋስ አማካኝነት ዳግም እንዳይቀሰቀስ ከፍተኛ ሥጋት እንዳለ ጨምረው ገልጸውልናል።
የእሳት ቃጠሎውን በሰው ጉልበት ብቻ ለመቆጣጠር አዳጋች እእየሆነ መምጣቱን የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ ጠቅላይ ቤተክህነተት ቃጠሎውን በአውሮኘላን ማጥፋት በሚቻልበት ሁኔታ ከሚመለከተው አካል ጋር መስራት ይቻል ዘንድ ሀገረ ስብከቱ በደብዳቤ መጠየቁን ገልጸዋል ።
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤትም የሁኔታውን አስሳቢነት በመግለፅ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዛሬ ደብዳቤ መጻፉንና ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።(የኢኦተቤ-ሕዝብ-ግንኙነት-መምሪያ)