ʺሕይወቱን የሰጠላት ሀገር ለሐውልቱ መቆሚያ ስፍራ ነፈገችው”
መልካም ያደረገ ይከበራል፣ አንድነቱ የጠነከረ ይፈራል፣ ቆራጥ ልብ ያለው ጠላትን ያስፈራል፣ ሀገሩንም ያኮራል፡፡ ኢትዮጵያን ያስከበሯት፣ ኢትዮጵያን ያከበሯት፣ ኃያለኑ ሁሉ እንዲሰግዱላት ያደረጓት ጀግኖች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሲሻቸው በፀሎት እንዲያም ሲል በጥይት የመከራውን ቀን ያልፋሉ፡፡ በግራ እጁ የሚያርስ በቀኝ እጁ የሚተኩስ የት አለ ቢባል ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡
መከራዎች ሁሉ በፅናት ታለፉ፣ ኢትዮጵያን ለመድፈር፣ ኢትዮጵያውያንን ለማሳፈር የመጡት ሁሉ በመንገድ ተቀሰፉ፡፡ ኃያላኑ መንግሥታት አፍሪካን ተከፋፍለው እያስተዳደሩ ነበር፡፡ በአፈጣጠሯም በአኗኗሯም ለየት ያለች አንዲት ምስራቃዊት ሀገር ብቻ ከኋያላኑ እጅ አልገባችም፡፡ ያችንም ሀገር ፍጡርና ፈጣሪ በአንድነት ይጠብቋታል፤ ሕጉን የሚያከብሩ፣ ቤቱን የሚያስከብሩ ሕዝቦች አሉባትና ፈጣሪም ያችን ምድር አብዝቶ ይወዳታል፣ በኃይሉ ይጠብቃታል፣ በመከራውም ዘመን ያፀናታል፡፡ ያቺ ምሥራቃዊት ሀገር በኃያላኑ እጅ ከገባች ፍትህ እንዳዘነበለች ትቀራለች፡፡ የጥቁሮች የተስፋ ፀሐይም ትጠልቃለች፡፡ ያቺ ሀገር የኃያላኑን ክንድ ካዛለች፣ አንገታቸውንም ካስደፋች ደግሞ ፍትህ ትመለሳለች፣ የተስፋዋ ፀሐይም ከፍ ብላ ታበራለች፡፡
ዘመኑ የጭንቅ ዘመን ነው፡፡ የተስፋዋን ምድር ከሚደግፏት ይልቅ የሚነቅፏት በዝተዋል፡፡ አይዞሽ ከሚላት ይድፋሽ የሚላት ተበራክቷል፡፡ የሮም አስፈሪ ሠራዊት በአደባባዩ አገሳ፤ ወዮለት ከፊቴ ለሚቆመው አለ፡፡ አደባባዮቹ ተጨነቁ፣ የዓለም ዓይኖች ሁሉ በሮም እየሆነ ያለውን አደነቁ፣ የሮም መኳንንትና መሳፍንት ያሰቡት ይሰመር፣ ግዛታቸውም ይጨምር ዘንድ ሽተዋልና ጦሩን አበረታትተው ሸኙት፡፡ ኃያላኑ መንግሥታት ወዮላት ለዚያች ምድር አሉ፡፡ ʺእንኳን ከፎከረ ከወረወረ ያድናል” እያሉ ከሠራዊታቸው ብዛት ይልቅ የፈጣሪያቸውን ኃይል የሚያስቀድሙት፣ አብዝተውም በእርሱ የሚመኩት ኢትዮጵያውያን በአደባባይ አልፎከሩም፣ ከጦር ሜዳ በፊት አልተዘባበቱም፤ ሙያ በልብ ነው በማለት ዝምታን መረጡ፡፡
ከሮም የተሸኘው ሠራዊት የብሱንና ባሕሩን አቆራርጦ የጀግኖቹን ምድር ረገጠ፡፡ ኢትዮጵያዊያንም ʺእባካችሁን አጥራችን አትንኩ፣ ፍቅር ይሻላል” አሉ፡፡ እብሪት የወጠረው ሠራዊት ከፍቅር ይልቅ ጦር ይቅደም ብሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን በእንድነት ተሰባስበው ደረታቸውን ለጦር እግራቸውን ለጠጠር ሊሰጡ የጠላት ጦር ወደ መጣበት አቅጣጫ አቀኑ፡፡ በዚያ የጭንቅ ዘመን መንገድ እየጠረጉ፣ ጠላትን እያስበረገጉ፣ ከዋናው ጦርነት በፊት የጠላትን አንገት ካስደፉ ጀግኖች መካከል አንደኛው ራስ መኮንን ነበሩ፡፡ ራስ መኮንን የወይዘሮ ተናኘ ወርቅ ልጅ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ተናኘ ወርቅ ደግሞ የአፄ ምኒልክ አክስት ናቸው፡፡ አባታቸው ደግሞ ደጅ አዝማች ወልደ ሚካኤል ይባላሉ፡፡ ራስ መኮንን ከሕጻንነታቸው ጀምሮ በትምህርት ያደጉ ናቸው ይባላል፡፡ በተፈጥሮ ባገኙት ጠባያቸው አስታዋይና ታጋሽ ናቸውም ይባላሉ፡፡ ምኒልክ ራስ መኮንን አብዝተው ያምኗቸውና ይወዷቸው ነበር፡፡
ታላቁ የጦር መሪ ራስ መኮንን በምዕራብ ኢትዮጵያ እስከ አቢጋር ድረስ ያለውን ሀገር አቅንተዋል፡፡ ራስ መኮንን ጀግና የጦር መሪ ብቻ ሳይሆኑ ብልህ መልዕክተኛም ነበሩ፡፡ በውጭ ሀገራት እየተጓዙ ሀገራቸው ከሌሎች ሀገራት ጋር ወዳጅ እንድትሆን ሰርተዋል፡፡ ምኒልክ አብዝተው ከመውደዳቸውና ከማመናቸው የተነሳ ዙፋናቸውን ያወርሷቸው ዘንድ ይመኙ ነበር፡፡ ዳሩ ከአውራሹ ወራሹ ቀድሞ አለፈና የታሰበው ሳይሳካ ቀረ፡፡
ባሕር አቋርጦ የመጣው የኢጣሊያ ወታደር እየገሰገሰ ነው፡፡ የምኒልክ ሠራዊትም ወደስፍራው ገስግሷል፡፡ አፄ ምኒልክ የኢጣሊያ ወታደር የያዘውን ሥፍራ ለቆ ወደኋላ እንዲመለስ መልእክት ላኩ፡፡ የኢጣሊያ ወታደር ግን እየገፋ መጣ፡፡
ራስ መኮንን የጦር አበጋዝ ሆነው ራስ ወሌን፣ ራስ ሚካኤልን፣ራስ መንገሻ አቲከምን፣ ራስ አሉላን፣ ደጅ አዝማች ወልዴን፣ ፊታውራራ ገበየሁን፣ ፊታውራሪ ተክሌን፣ ሊቀ መኳስ አድነውን፣ ቀኝ አዝማች ታፈሰን፣ ይዘው ወደፊት ተጓዙ፡፡ ኢጣሊያኖች መሽገው በተቀመጡበት በአምባላጌ ተራራ አጠገብ ደረሱ፡፡ ደም ከመፋሰስ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ጠየቁ፡፡ እርሱ ግን አሻፈረኝ አለ፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በሚለው መጻሕፋቸው ʺ ራስ መኮንን አሸንጌ ሲደርሱ መጣውብህ አትችለኝምና ሽሽ ከፊቴ አትቁም ብለው ላኩበት፡፡ ማጅኦር ቶዜሊ ግን አሻፈረኝ ከዚህ ስፍራ
አልነቃነቅም እስቲ ከደፈርህ ንካኝ ብሎ ላከ፡፡ ወዲያው ራስ መኮንን ደረሱና ከበው ይዘው አንድ ሳይቀር በሰናድር እርግፍ አደረጉት፡፡ ጥቂትም ቢቀር እስከ ጠመንጃውና እስከ መድፉ በራስ መኮንን እጅ ወደቀ፡፡ ራስ መኮንን የአምባላጌን ጦር ድል ተመቱ በኋላ ወደ መቀሌ ገስግሰው ምሽጉን በታኅሣሥ ስምንት ቀን ከበው ይዘው ይዋጉ ጀመር” ብለዋል፡፡
ጳወሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጻሕፋቸው የኢጣልያኑ መድፈኛና ጋዜጠኛ የነበረው ሞልቴዶን ዋቢ አድርገው የአምባላጌውን ጦርነት ሲገልፁት ʺሙሐመድ የሚባለው የሱማሊያው ወታደር ሲያጫውተኝ፣ ጦርነቱ ተጀመረ፣ ተኩስ እሰማለሁ፣ ግን የማየው ነገር የለም፡፡ ወጥ ቤት ነኝና ቁርስ ለማዘጋጄት ተነስቼ ጉድ ጉድ ስል አምስት ሰዓት ሲሆን መቶ አለቃ እስካላ በበቅሎ ተቀምጦ መጣ፡፡ ምን ታደርጋለህ? አለኝ፡፡ ምግብ አዘጋጃለሁ አልኩት፡፡ ተወው ዛሬ ምግብ አንበላም፡፡ ሁሉን ነገር እዚያው ተወውና በቅሎ ጭነው ከሚሄዱት ሰዎች ጋር ተገናኝ አለኝ፡፡ ተደባልቄ ስንጓዝ ካንድ ሰርጥ ገባን፡፡
እዚያም አበሾች በጥይት ተቀበሉን፡፡ በየድንጋዩ ኋላ አበሾች ተደብቀው ኖረዋል፡፡ ከበላያችን ይተኩሳሉ፡፡ ከፊታችንም ይተኩሳሉ፡፡ ከጎናችንም ይተኩሳሉ፡፡ መድረሻ አሳጡን፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የሚሸሸው የእኛ ወታደር ይገፋናል፡፡ በቅሎዎቹ እየረገጡን ያልፋሉ፡፡ ይጋፋሉ፤ በግራም በቀኝም ሬሣና ቁስለኛ ብቻ ተከምሯል፡፡ የቆሰሉት ሰዎቻችን እርዱን እርዱን ይላሉ፡፡ የሚሰማቸው የለም፡፡ በየትኛውም ቦታ በየትም አበሾቹ እየተከታተሉ ይተኩሱብናል፡፡ በእነሱም ላይ ቢሆን የእኛ መድፍ ይተኮስባቸዋል፡፡ የኛ መድፍ ተኳሾች ከእኔ ጋር ሲሸሹ ሳይ ጊዜ ተስፋ ቆርጥኩ፡፡ መንገዱን ተውኩና ጫካ ውስጥ ገባሁ፡፡ አንድ ቦታም ተደብቄ ራሴን አዳንኩ፡፡ በጉዞዬ ላይ የእኛን መኮንንኖች አላየሁም፡፡ አሁን ከዚህ ከሌሉ ሁሉም ሞተዋል ማለት ነው፡፡” ማለቱን ከትበዋል፡፡
አምባለጌን በድል መትተው፡፡ በመቀሌም ተገናኙ፡፡ ራስ መኮንን እና ሠራዊታቸው ከሌሎች ጀግና ኢትዮጵያዊን ጋር ተጠምደዋል፡፡ የኢጣሊያ ሠራዊት ምሽጉን በሽቦ አጥሮ፣ በዙሪያው ጠርሙስ ከስክሶ ይከላከል ጀመር፡፡ ኢትዮጵያዊያን ጫማ ስለማይጫሙ ምሽግ ዘለው መግባት አይቻላቸውም ብሎ ነበርና፤ ኢትዮጵያዊያን ግን ብልጦች ነበሩ ለእግራቸው የሚያሰጋውን በብልጠት ያልፉት ነበር፡፡ የመቀሌው ውጊያ ቀጠለ፡፡ በእቴጌ ብልኃት ዝም ብሎ ከመዋጋት ውኃው እንዲያዝና የጠላት ጦር እንዲዳከም ተደረገ፡፡ ውኃውን ይዞ የራስ መኮንን እና የራስ አሉላ ጦር በጥይት ይቆላው ነበር፡፡ የራስ መኮንን ሠራዊትም የጣልያንን አጥር በጎራዴው እየበጣጠሰው ገባ፡፡
ራስ መኮንን የኢጣልያን ወታደር በጥይት ከመቁላት ባሻገር በስልታዊ አካሄድ ከእጃቸው ያስገቡት ነበር፡፡ አይዟችሁ ከእናንተ ጋር ነኝ እያሉ መልእክት እየላኩ የኢጣሊያ ወታደር እውነት እየመሰለው መውጫና መግቢያውን ሲናገር እየተከተሉ ድባቅ ይመቱና ያስመቱት ነበር፡፡ እኒህ አስፈሪ የጦር አበጋዝ በጥበባቸውና በጀግንነታቸው በዓድዋ ላይም ተሰልፈው የዓድዋን ድል ካመጡ ጀግኖች መካከል አንደኛው ናቸው፡፡ እኒህ የጦር መሪ ሀገር በማቅናትና በማኩራት ይታወቃሉ፡፡ የራስ ተፈሪ የኋለኛው ግርማዊ ቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ አባትም ናቸው፡፡ እኒህ ታላቅ ሰው የምኒልክ ዙፋን ይቀበላሉ ተብሎ ሲታሰብ ቀድመው አለፉ፡፡ ያለፉበት ዘመንም በዚህ ሳምንት መጋቢት 13 ቀን በ1898 ዓ.ም ነበር፡፡ ባለፉም ጊዜ ፡-
ʺሲታሰር አየነው ብረቱ ሲመታ
ምን ዋስ አገኜና ሐረርጌ ተፈታ፡፡
ጃንሆይ ምኒልክ ጠጉራቸው ሣሣና በራ ገለጣቸው
እንግዲህ ንጉሡ ምን ራስ አላቸው፡፡” ተብሎም ተገጥሞላቸዋል፡፡ በራስ መኮንን ሞት ምኒልክም መጎዳታቸውን የሚያመላክት ነበር፡፡
ታላቁ ሰው በሐረር ከተማ ሆስፒታልና ትምህርት ቤት አሰርተዋል፡፡ በበረታ ልባቸው ሀገር አቅንተዋል፤ ስለሀገር ሲሉ ዘመናቸውን በሥራ አሳልፈዋል፡፡ ራስ መኮንን ለሀገራቸው ላበረከቱት አስተዋፅዖ በልጃቸው በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን ሲያስተዳድሩት በነበረው ሀገር በሐረር ከተማ ሐውልት ተሰራላቸው፡፡ ሐውልታቸውም ታሪክን ከመዘከር ባሻገር የከተማዋ ውበት ሆነ፡፡ ዘመን ዘመንን እየተካ ሄደ፡፡ የራስ መኮንን ክብርና ጀግንነት ያልታያቸው ተነሱ፡፡ ለሀገራቸው ሕይወታቸውን ያልሰሰቱት ጀግና ለሐውልት ማቆሚያ ምድር ተነፈጋቸው፡፡
በሐረር ጎዳናዎች ወርጄ ራስ መኮንን የነበሩበትን አደባባይ ተመለከትኩ፡፡ ከእነፈረሳቸው የነበሩበት ሐውልት ተገርስሶ ድንጋዩ ብቻ ቆሟል፡፡ ከክብሩ ወርዷል፡፡ አካባቢው ሐውልቱን በማጣቱ ግርማውን ተገፏል፡፡ ሁኔታው ሳያሳዝነኝ አልቀረም፡፡ ተገረምኩም፡፡ በቆይታየ ስለ ሐውልቱ ያወጉኝ የከተማዋ ነዋሪዎች በመፍረሱ ቁጭት አድሮባቸዋል፡፡ ውበታችን ነጥቀውናል ብለውኛል፡፡ ጥላቻ ብቻ ሲሰበኩ ያደጉ ወደከተማዋ ገብተው እንዳፈረሱትም ነግረውኛል፡፡ እኔም የዓድዋውን ጀግና መታሰቢያ እያፈረሱ ለዓድዋ በዓል መታሰቢያ ድግስ ቢደግሱ እርባና ቢስ መሆኑ ተሰማኝ፡፡
አንድ እውነት ግን አለ የራስ መኮንን መታሰቢያ ሐውልት ማፍረስ እንጂ ታሪካቸውን ማኮሰስ አይቻልም፡፡ ታሪካቸውን ደም ገብረው በደማቅ ቀለም ጽፈውታልና፤ ሰው እንኳን ዝም ቢል የዓድዋ ተራራዎች መኮንን መኮንን ይላሉ፡፡ የአምባላጌና የመቀሌ ምድር መኮንን ያስታውሳሉ፡፡ ቢቻል ታሪክ መስራት ካልተቻለ ግን ታሪክ አለማፍረስ ብልኅነት ነው፡፡ መልካሙን ዘመን ያምጣልን፡፡
(ታርቆ ክንዴ ~ አብመድ)