Connect with us

አጣዬ-ችግር የማያጣው  ቀጠና!

አጣዬ-ችግር የማያጣው ቀጠና!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

አጣዬ-ችግር የማያጣው  ቀጠና!

አጣዬ-ችግር የማያጣው  ቀጠና!

(ስናፍቅሽ አዲስ ~ ድሬቲዩብ)

የከሚሴና የዙሪያው ወቅት ጠባቂ ችግር ሀገር በብዙ አቅጣጫ በተወጠረችበት ሰዓት አገርሽቷል፡፡ የህወሃት ከባድ ፈንጂ ከተጠመደባቸው የኢትዮጵያ ቀጠናዎች አንዱ የአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አንዱና ዋናው ነው፡፡

ሰሞኑን ዳግም ለብዙኛ ጊዜ በከሚሴና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች በመሳሪያ የታገዘ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ የአማራ ክልል በሰጠው መግለጫ በግለሰቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በሀገር ሽማግሌ ከተፈታ በኋላ ከሌላ አካባቢ የመጣ የታጠቀ ሃይል አካባቢውን ማተራመስ ንጹሃንን መግደልና ቤቶችን ማቃጠል ጀምሯል፡፡

በተለይም አጣዬ ከተማ የጦርነቱና የውድመቱ ሰለባ ሆናለች፡፡ ግጭቱ ለረዥም ዘመን አብረው በኖሩት የአካባቢው ተጎራባች ህዝቦች መካከል እንዳልሆነ ከደረሰው ውድመት መረዳቱ ከባድ አይደለም፡፡ ወለጋን ያሻውን እያረደ ያለው ኦነግ ፊቱን አዙሮ የፈጸመው እንደሆነ ብዙዎች ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡

ኦነግ ነው አይደለም ሌላ ጉዳይ ሆኖ የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት ምስክርነት ግን ተኩስ የከፈተው ሃይል የተሻለ ትጥቅ ያለውና በአካባቢው ካለው ህብረተሰብ አልፎ አልፎ ከሚያጋጥም ግጭት ጠባይ የተለየ እንደሆነ ነው፡፡

አሁን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት የታጣቂዎች ረብሻ ግድያና መፈንጨት እንዲህ መቀጠል አለመቀጠሉ የሚወሰነው በትግራይ ያለው ህግ የማስከበር ዘመቻ እልባት ላይ ነው፡፡ ብዙዎች መንግስት ሃይሉ ተበታትኗል በሚል በተበታተነ ቦታ ትንኮሳ ያደርጋሉ፡፡ ወለጋና መተከል ተደጋጋሚው የታጣቂዎቹ ጥፋት ከሱዳን ድንበር ጥሶ መግባት ጋር ተዳምሮ የሚነግረን አንድ ጉዳይ አለ፡፡

አቶ ጌታቸው ረዳ ከገቡበት ጉሮኖ ሆነው ጥሩ ውጤት ማስመዝገባቸውን የገለጹት አጣዬ በጦርነት ስትታመስ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ግጭቶች የጥፋት ቡድኑ የመጨረሻ እድሎች ናቸው፡፡ እድሉን ለማሳመር ከዚህ በከፋ መልኩ በሁሉም አቅጣጫ ሊረባረብ እንደሚችል ደግሞ መገመት ቀላል ነው፡፡

አማራ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻው ፊት መሪም ባለውለታም የሆነውን ያህል መንግስቱና ህዝቡ በትህነግ መደምሰስ ቂም የተያዘባቸው እንደሆኑ ከዓለም አቀፍ ሰልፎች ከሰሞኑ የዋግኽምራ ጥቃቶችና ከተደጋጋሚ ዛቻዎች መረዳት ይቻላል፡፡ የአጣዬ ጥቃት የዚያ አካል ከሆነ ላይደገም የሚቀበርበት እድልም ሰፊ ነው ማለት ነው፡፡

የአጣዬ ችግር እንዴት ይፈታ የሚለው ከችግሩ መደጋገምና ችግሩን የሚፈጥረው አካል የተደራጀ ትጥቅና ዝግጅቱ ትልቅ አላማ ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግስት ሰፊ ስራ በአካባቢው ላይ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

ዜጎች በሰላም የመኖር ዋስትናቸው እዚህ ደረጃ የደረሰው ለረዥም ዘመን በተሰራ ተንኮል ደባና የተቀበረ ፈንጂ ሳቢያ ነው፡፡ ያን ግምት ውስጥ የከተተ ራስን የመከላከል እና ህብረተሰብን የማንቃት ስራም ያስፈልጋል፡፡ እምነትና ብሔር ተገን የሆኑበት ይህ የመሬት መስፋፋትም እንደበለው የተቀበረን የትህነግ ቡድን ከመቃብር ለማውጣት የሚደረግ ጥረት የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ፣ የሀገርን ሰላም እያናጋ ሌላ ቀውስ ውስጥ ደጋግሞ ከትቶናል፡፡ እያንዳንዱን የግጭት ቀጠና ለማያዳግም ጊዜ ማጽዳት ላይ የመንግስት አመራርና ውሳኔ ሰጭነት ልምጥምጥ እንደሆነ መረዳት ግን አይከብድም፡፡

አንዱ ቦታ ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ችግር እየተፈጠረ ዜጎች ለሞትና ለስደት ሲዳረጉ መፍትሔውን በዘላቂ አስቦ ችግሩን መፍታት ግን የመንግስት ድርሻ ነው፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top