፧ግዕዝና ግብረገብነት” በሚል መሪ ቃል በጎንደር ከተማ በመካሄድ ላይ ያለው አመታዊውን የግዕዝ ጉባኤ ተጠናቀቀ
~ የግዕዝ ቋንቋ ልማት ስትራቴጂ ረቂቁ ላይም ምክክር ተደርጓል፣
(በድሬ ቲዩብ ሪፖርተር)
ጎንደር ከተማ ያስተናገደችው ስድስተኛው አመታዊ የግዕዝ ጉባኤ በትናንትናው ዕለትም ቀጥሎ ውሎ ነበር። በኢ.ፊ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋ ሥነ ቃልና ትርጉም ሥራ ልማት ዳይሮክተሬት መሪነት የተዘጋጀው ይኽ ጉባኤ በሁለተኛ ቀን ውሎው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ሊቅ በዶክተር ሥርግው ገላው “የጎንደር ዘመን የሥነ ፅሑፍና የሥነ ጥበብ ሥራዎች ለግብረ ገብነት ያለው ፋይዳ” በሚል የጎንደር ዘመን በግዕዝ ሥነ ፅሁፍ በኪነ ጥበብና በዜማ ረገድ የነበረውን ወርቃማ አበርክቶ አሳይተዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲው መምህር ሊቀ ህሩያን ተግባሩ አዳነ የግዕዝ ዜማዎች ለሥነ ምግባር ያላቸውን ሚና ባሳዩበት የጥናት ፅሁፍ ደግሞ ጥበብ። ከያኒያኑ። መስንቆና በገና ላይ አተኩረው “የግዕዝ ቋንቋ የቅኔ የመሰንቆና የመዝሙር/በገና አንድምታ ለግብረ ገብነት” በሚል ርዕስ ሰፊና ጥልቅ ጥናታቸውን አቅርበዋል።
በጠዋቱ መርሐ ግብር የጥናት ፅሁፋቸውን ያቀረቡት ሌላው ሊቅ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር የኾኑት ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን ናቸው። ደራሲውና የድጓው ሊቅ በላይ መኮንን ቅኔን የቅዱስ ያሬድን ስራዎችና ሥነ ምግባርን አስተሳስረው “ፍልስፍናና ግብረ ገብነት በግዕዝ ቅኔያት” በሚል የውይይት መነሻ ፅሁፋቸውን አቅርበዋል። ውይይቱን የመሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲው ዶክተር አገኘሁ ተስፋ ነበሩ።
በጎንደር ሊቃውንት ቅኔና ዜማ ታጅቦ የዋለው የሁለተኛው ቀን የግዕዝ ጉባኤ ማጠናቀቂያ በግዕዝ ቋንቋ እድገት ላይ የቀረበው የልማት ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ ነው። በርካታ ምሁራን በጋራ የሰሩትን ሰነድ ያቀረቡት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ጥበበ አንተነህ ሲኾኑ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋ ሥነ ቃልና ትርጉም ሥራ ልማት ዳይሮክተሬት ዳይሬክተሩ ዶክተር አውላቸው ሹምነካ ውይይቱን መርተውታል። ተሳታፊዎች ረቂቁ ላይ ቢጨመር ቢታይና ቢሟላ ያሉትን አቅርበዋል።
“ግዕዝና ግብረ ገብነት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የ2013 ዓ.ም. የግዕዝ ጉባኤ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲና በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቅንጅት የተዘጋጀው ነው።
(ለዜናው ጥንቅር የተጠቀምናቸውን ፎቶዎች ያገኘነው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የፌስ ቡክ ገፅ ነው።)