Connect with us

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የፈጠረው ቀውስ

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የፈጠረው ቀውስ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የፈጠረው ቀውስ

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የፈጠረው ቀውስ

(ሙሼ ሰሙ)

መንግስት በነዳጅ ላይ (ከውጭ ምንዛሪ በተጨማሪ) ያደረገው የዋጋ ጭማሪ የፈጠረው ንረት፣ የአቅርቦት መዛባትና የንግድ ስርዓት ምስቅልቅ ማብረጃ እንዳጣ ቀጥሏል። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ግልጽነት የጎደለውና ብዙ አጠራጣሪ አካሄዶችን የተከተለና በቂ አመክንዮ ያልቀረበበት በመሆኑ፣ በኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ መያዠያና መጨበጫ ማጣቱ የሚታይ ነው። በዚህ ወር፣ በታሪክ ታይቶ በማይታውቅ ሁኔታ አጠቃላይ ግሽበቱ 21 % ደርሷል። የምግብ ምርት የተናጠል ዋጋ ንረት እጥፍ ነው።

ኮሮና፣ ጦርነት፣ አንበጣና አመረጋጋት በበረታበትና ኑሮ ውድነቱ ጥላውን ባጠላበት በዚህ ፈታኝ ጊዜ ወገብን ጠበቅ አድርጎ ፈተናውን ተጋግዞ ማለፍ ሲገባ፣በተከታታይ መብራት፣ ነዳጅ፣ ስንዴ፣ የምግብ ዘይት፣ ዶላር በተለይ ደግሞ ነዳጅ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ለምን አስፈለገ። ኢኮኖሚያዊ አመክንዮው ምንድን ነው?! ሊያስረዳን የቻለ ተሿሚ ማግኘት አልቻልንም።

ሰሞኑን ባገኘሁት መረጃ መሰረት፣ መንግስት የስኳር ተረፈ ምርት የሆነውን ኢታኖል ላይ ከ29 ብር ወደ 80 ብር ጭማሪ ተደርጓል። ኢታኖል የነዳጅ ዋጋን ያረጋጋል የተባለለት የስኳር ተረፈ ምርት ነው። ዋነኛ ምርት የሆነው ስኳር በ28 ብር እየተሸጠ ነው። ተረፈ ምርቱ ከቤንዚንም ሆነ ከስኳር ዋጋ ከሁለት እጥፍ በላይ በ80 ብር እንዴት ሊመረትና ሊሸጥ ቻለ። ሀገር ውስጥ በሚመረት ተረፈ ምርት ላይ፣ በዚህ ደረጃ የናረ ጭማሪ ማድረጉስ ምን አመክንዮ ይቀርብለታል?!

እንደሚታወሰው በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር የነዳጅ ዋጋ  ከ2 ዓመት ጀምሮ ያሳየውን ጭማሪ ተከትሎ፣ መንግስት ጭማሪውን ለመሸፈን 24.05 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን አስታውቀው ነበር። በመቀጠልም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ሸገር ላይ ቀርበው ላለፉት 2 ዓመት መንግስት ለነዳጅ የሸፈነው ወጭ ከ25 ቢሊየን ብር እንደሚበልጥ ገልጸዋል። በሁለቱ ኃላፊዎች መካከል እንደዋዛ የታለፈ የአንድ ቢሊየን ብር ልዩነት አለ። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?!

ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው በነዳጅ ዋጋ ላይ በጭማሪነት የቀረበው መነሻ ዋጋ ስምንት ብር እንደነበረ ገልጸው በሁለት ተከታታይ ዙር የተፈቀደው ጭማሪ ግን 25 ብር መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ስሌት መሰረት 75 በመቶውን መንግስት 25 በመቶ ደግሞ በሕዝቡ እንደሚሸፈን አክለዋል ነበር። 

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በሕዝብ እንዲሸፈን የተጠየቀው ስምንት ብር ከነበረና አምስቱ ብር በሕዝብ እንዲሸፈን ከተደረገ በሕዝብ የሚሸፈነው ጭማሪ 63 በመቶ እንጂ 25 በመቶ አይደለም። በዚህ መልክ የተዛባ መረጃ ለሕዝብ መስጠት ለምን አስፈለገ?!

በመቀጠል፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት መንግስት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋን እያጣራና እየመዘነ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር እየጨመረ እንደመጣ በየወሩ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በይፋ መግለጫ ሲሰጥ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ይህ መረጃ እውነት ከነበረ፣ ዛሬ ላይ በመንግስት ተሸፈነ የሚባለው 24 ቢሊየን ብር ወጭ ከየት የመጣና ለምን የተከፈለ ይሆን። መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው?!

የነዳጅ ዋጋን ለመቋቋም ሁለት መሰረታዊ ስራዎችም ቀደም ባሉት ዓመታት እንደተተገበሩ ይታወሳል። አንደኛው እስከ 10% የሚደርስ የኢታኖል ምርትን ከነዳጅ ጋር በመቀላቀል የነዳጅን ዋጋው ማርከስ ሲሆን ሌላው የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ማቋቋም ናቸው። 

በነዚህ እርምጃዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሸጠው የነዳጅ ዋጋ ዓለም ላይ ካለው ያልተደባለቀ የነዳጅ ዋጋ ጋር ሲወዳደር ቢያንስ የሀገር ውስጥ ምርት በሆነውና በተደባለቀበት ኢታኖል ልክ መቀነስ ነበረበት።

የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድም የነዳጅ ዋጋ ንረትን ለመቋቋም ታስቦ ከሕዝብ ኪስ በተለያየ መንገድ የሚሰበሰብ ሀብት ነው። ዛሬ ላይ ትርጉም ቢያጣም፣ ለልማት የሚውል ገንዘብ ከመንግስት ካዝና በድጎማም ሆነ በሽፈን ስም ወጭ እንዳያደርግ የታቀደ ነበር። በዚህ መንገድ  በሚሰበሰበው ገንዘብ አማካኝነት ምን ያህል የዋጋ ንረት ማረጋጋት ተችሏል።

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ነዳጅ ድርጅት ዙርያ ከነዳጅ አቅርቦት፣ ግዢና ስርጭት ጋር በተያያዘ እዚህ ማቅረብ ባይቻልም በርካታ አሳሳቢ ሀሜቶች ይነሳሉ። እንደዚህ ዓይነት የተምታቱና የተቀሸቡ መረጃዎች መቅረባቸው ደግሞ ሃሜቱን ይበልጥ እንድንጠራጠር ያደርገናል። የተወካዮች ምክር ቤትና መንግስት እውነታው ማን ጋር ነው ያለው? ሕዝብን ከሰው ሰራሽ የኑሮ ምስቅልቅል ለመታደግ እራሳችሁን ፈትሹ?!

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top