Connect with us

የክብር ዶ/ር  አብደላ አሊ ሸሪፍ ማንናቸው?

የክብር ዶ/ር አብደላ አሊ ሸሪፍ ማንናቸው?
የሐረሪ የመንግስት ኮምኒኬሽን ፅ/ቤት

ነፃ ሃሳብ

የክብር ዶ/ር  አብደላ አሊ ሸሪፍ ማንናቸው?

የክብር ዶ/ር  አብደላ አሊ ሸሪፍ ማንናቸው?

ክቡር ዶክተር አብዱላሂ አሊ ሸሪፍ ከአባታቸው አሊ ሸሪፍ እና ከእናታቸው አሚና የሱፍ በሀረር ከተማ በተለምዶ ሰንጋ በር ተብሎ በሚጠራው ሰፈር በ1945 ዓ.ም ተወለዱ፤ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውም እዛው ሀረር ከተማ የተከታተሉ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርታቸውም በጭላሎ ቴክኒክ ኮሌጅ በገበያ ጥናትና የትምህርት አያያዝ ዘርፍ በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

ከልጅነታቸው ጀምሮ ቅርስን የመጠበቅና የመንከባከብ ልዩ ፍላጎትና ተሰጦ የነበራቸው ክቡር ዶክተር አብደላ አሊ ሸሪፍ ህልማቸውን ለማሳካት ቀደምት የሀረሪ ሙዚቃዎችንና ጥንታዊ የእጅ ፅሁፎችን በማሰባሰብ ነበር ስራቸውን ‘ሀ’ ብለው የጀመሩት፡፡

ታዲያ ለ16 አመታት ለቅርስ ማሰባሰቢያነት፣ ለቅርስ መጠገኛነትና ጎብኚዎችም የሚስተናገዱበት የነበረው 7 የቤተሰብ አባላት በሚኖሩበት አነስተኛ መኖሪያ ቤታቸው ነበር፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰበስቧቸው ቅርሶች በአይነትም በመጠንም እየጨመሩ፣ የጎብኚዎችም ቁጥር እያደገ መጥቶ ክቡር ዶክተር አብደላ ሸሪፍ ጊዜያቸውን፣ ቤታቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ገንዘባቸውንም መስዋዕት ያደረጉለት ይህ ተግባር ፍሬ አፍርቶም  በ1991 ዓ.ም ‘’ሸሪፍ ሙዚየም’’ በመባል  በኢትዮጵያ ብቸኛውን “የግል ሙዝየም” ለመመስረት ቻሉ፡፡

ይህ ታላቅ ስራቸው ከበርካታ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላም ከሀገር አልፎ የበርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎችንም ጭምር ትኩረት መሳብ ጀመረ፡፡

በ1999 ዓ.ም የሀረሪ ክልል መንግስት ለቅርስ ጥበቃ በሰጠው ትኩረት እና የክቡር ዶክተር አብደላ ሸሪፍ እያከናወኑት ላለው የቅረስ  ማሰባሰብና ጥበቃ ተግባር ውጠታማ እንዲሆን ቀድሞ የተፈሪ መኮንን ጫጉላ ቤት የነበረውና 21 አባወራ(ቤተሰብ) ይኖርበት የነበረውን ታሪካዊ ቤት ለዚሁ የቅርስና ታሪክ ጥበቃ ተግባር እንዲውል በመወሰንና ለነዋሪዎቹም ተለዋጭ ቤት በመስጠት ሙሉ ህንፃውን ለሙዚየምነት እንዲገለገሉበት የክልሉ መንግስት ለክቡር ዶክተር አብደላ አሊ ሸሪፍ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎላቸዋል።

የክቡር ዶክተር አብደላ አሊ ሸሪፍ ዘርና ሃይማኖት ሳይገድባቸው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን እንዲሁም የሁሉንም እምነቶች ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ቅርሶችን ሰብስቦ በያዘው የግል ሙዝየም ከ13 ሺህ በላይ ውድና እድሜ ጠገብ የሀገር ሀብት የሆኑ ቅርሶችን በማሰባሰብና በመጠበቅ ለትውልድ ለማቆየት ችለዋል፡፡

ክቡር ዶክተር አብደላ አሊ ሸሪፍ በግል ሙዚየማቸው ካሰባሰቧቸው ከ13 ሺህ በላይ ቅርሶች መካከልም የሀረሪ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ የአርጎባ እና የሌሎችም ብሔረሰቦች የማንነት መገለጫ ቅርሶች ይገኙበታል።

በክቡር ዶክተር አብደላ አሊ ሸሪፍ በግል ሙዚየም ቅርሶችን ከመሰብሰብ ባለፈም ቅርሶችን የመመዝገብና የመንከባከብ እንዲሁም የተጎዱ ቅርሶች የመጠገንና የማደስ ስራዎችንም መስራት ሌላው በሙዝየሙ የሚከወን ልዩ ተግባር ነው፡፡

ለዚህም የቅርስ ጥበቃና እክብካቤ ስራቸው በተቋማቸው ደረጃ ሰባት(7) የቅርስ ጥበቃና ጥገና ቴክኒክ ማኑዋሎችን በማዘጋጀት ከመላው የሀገራችን ክልሎች ለሚመጡ ሞያ ፈላጊዎችም ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።

በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት 107 ቦታ ተጎድቶ የነበረውን የሀረር ጀጎል ግንብ የእድሳት ስራ 80 በመቶ የሚሆነውን ጥገና አድርገዋል።

እንዲሁም 67 መስጊዶች ቅርስነታቸዉን ሳይለቁ እንዲቆዩ የማደስ ስራ እንደሰሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የክቡር ዶክተር አብደላ ሸሪፍ በበርካታ የሐገር ውስጥና የውጪ ሚዲያዎችም በመቅረብ እንዲሁም ቅርሶን በመያዝ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የአለም ሐገራት በመዘዋወር የሀገራችንን ታሪክና ቅርሶች በማስተዋወቅ በርካታ አስተዋፅኦ ለማበርከት ችለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከተለያዩ አለማት ለሚመጡ የውጭ ሐገር ጎብኚዎች እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ለሚገኝ ኢትዮጵያዊያንም ሙዚየማቸውን በማስጎብኘት ታሪክን እና ማንነትን እንዲያውቅ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡

የክቡር ዶክተር አብደላ ሸሪፍ የተለያዩ አለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘት የቻሉ ሲሆን በሀገር ወስጥም የአመቱ የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ በርካታ እውቅናዎችን ያገኙ ሲሆን እነሆ ትላንት መጋቢት 04/2013 ዓ,ም የሐረማያ ዩኒቨርሲቲም “የሀገራችንን ጥንታዊና ዘመናዊ ስልጣኔዎችን በአለም ህዝቦች እንዲታወቁ የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል!” በማለት የዘንድሮ አመት (የ2013 ዓ.ም) የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሀገራችን ባልተለመደው በግል የቅርስ ማሰባሰብና ጥበቃ ዘርፍ የተሰማሩ “የትውልድ አብሪ ኮኮብ፣ የቅርስ ጥበቃ ጀግና አድርጎ ይመለከታቸዋል” ሲል ዩኒቨርሲቲው አድናቆቱን ችሯቸዋል፡፡

ለክብር ዶ/ር አብደላ አሊ ሸሪፍ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ በማግኘታቸው እንዲሁም እሰከ አሁን ድረስ እያደረጉት ለሚገኘው ቅርስን የማሰባሰብ፣ የመንከባከብና ለትውልድ የማቆየት አኩሪ ተግባራቸው በሀረሪ ክልል መንግስት እና ህዝብ ስም ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን።(የሐረሪ የመንግስት ኮምኒኬሽን ፅ/ቤት)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top