“የኦሮሚያ ክልል በማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ሊያስቆም ይገባል!”
~ የአማራ ክልል ምክር ቤት
የኦሮሚያ ክልል በማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በማስቆም በክልሉ ለሚኖረው ሕዝብ ደኅንነት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዙር ስድስተኛ ዓመት 17ኛ መደበኛ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ ነው ዋና አፈጉባኤዋ ወርቅሰሙ ማሞ ጥሪውን ያቀረቡት፡፡
ዋና አፈ ጉባኤዋ ምክር ቤቱ ትኩረት የሠጠባቸው ነጥቦችንም አብራርተዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ከሁሉም ጋር ተላምዶ፣ ተዛምዶ፣ ተጋግዞ፣ ተፋቅሮ የሚኖር መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ባህሪውን ወደፊትም ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡ ይህም ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከጥንቱ እንደ ባህል የያዘው ስለሆነ ይህንን የሚያደናቅፍ እና የሚያበላሽበትን አካል መታገል የግድ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡
የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 44 በመጥቀስ ማንም ሰው የትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በነጻነት የመኖር መብት እንዳለው አንስተዋል፡፡
ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ አማራዎችን በተመለከተም ዋና አፈጉባኤዋ “ኢትዮጵያዊ መንፈስ ነው ያላቸው፤ በሚኖሩበት አካባቢ ሲኖሩ እንደ ሠው አስበው ነው ያፈሩትን ንብረት እዛው በሚኖሩበት አካባቢ ለልማት የሚያውሉት” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና ምክር ቤት እየተደረገ ያለውን ዘር እና ማንነት ተኮር ጥቃት እንዲስያቆም ጠይቀዋል፡፡ በክልሉ ለሚኖረው ሕዝብ ደኅንነት ራሱ ክልሉ በትኩረት በመሥራት ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ በማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በማስቆምም በክልሉ ለሚኖረው ሕዝብ ደኅንነት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ዋና አፈጉባኤዋ ጥሪ አቅርበዋል።
‘ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት’ እንዲሉ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ በተለይ ደግሞ ወለጋ አካባቢ ያላችሁ አብራችሁ በልታቸሁ ጠጥታችሁ የኖራችሁ ሕዝቦች ስለሆናቹ በአማራነታቸው ብቻ የሚጎዱ ሰዎች እንዳይኖሩ ተንከባከቡልን፤ የክልሉ መንግሥትም የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር፣ መጠበቅ እንዲችል ማድረግ አለበት” ብለዋል ዋና አፈጉባኤዋ፡፡
እየደረሰ ያለውን ሞትና መፈናቀል ማስቆም ካልተቻለ ዛሬ በአማራዎች ላይ ጥቃት የፈጸመው አካል ነገ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጥቃት የማያደርስበት ምንም ምክንያት እንደሌለም አስገንዝበዋል፡፡
የምክር ቤት አባላትም ሠላም እንዲጠበቅ፣ ልማት እንዲመጣ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ወይዘሮ ወርቅሰሙ አስገንዝበዋል፡፡
በከተሞች የሚስተዋለው የኑሮ ውድነት በመገፋፋት ምክንያት ሕዝቡ መበደል እንደሌለበትም አስገንዝበዋል፡፡ መስተዳድር ምክር ቤቱም በትኩረት ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡
የቢሮ ኀላፊዎች እና መስተዳድር ምክር ቤቱ የራሳቸውን መዋቅር በመፈተሽ ለሕዝቡ ተገቢውን አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካጋጠመም ለሕዝቡ ይፋ መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ሊሠራ እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ (አብመድ)