ጃርት ያበቀለች አገር
ስለ አገራችን ወቅታዊም ሆነ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለማውራትም ሆነ ለመተንበይ እጅግ ግራ ቢገባን አይፈረድብንም፡፡ የተሠራውን ወይም የሚሠራውን አዎንታዊ ለውጥ ወይም ማለፊያ ተግባር ቢኖርም አሉታዊው ግን እጅግ ይበዛል፡፡
ብዙ ነገራችን ግራ ያጋባል፡፡ ተስፋ እንድንሰንቅ የሚያደርጉ ጥቂት እውነታዎች ብልጭ ቢሉም ብዙ አይቆዩም፤ ብልጭ ያሉት ተስፋዎቻችን ፀሐይ እንዳገኘው የማለዳ ጤዛ ለመትነን ጊዜ አይፈጁም፡፡
ሐተታውን ትቼ ለዛሬ ትኩረት ወደማደርግበት ርዕሰ ጉዳይ ልለፍ፡፡ አገልግሎት ከሚሰጡን መሥርያ ቤቶች አንዱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት ነው፡፡ ይኸ መሥሪያ ቤት አለቃ ወይም ሃይ ባይ ያለው ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ፡፡ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ እንደ ብዙዎቹ የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ተጠያቂነት የለም፡፡
መሪና ተመሪው፣ አለቃና ተራ ሠራተኛው ማን እንደሆነ የማይለይበት አምባገነንና ዳተኛ መሥርያ ቤት ነው፡፡ አሠራሩ ከቀን ወደ ቀን እየተዝረከረከ የመጣ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ደንበኞች የተጠቀሙበትን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋጋ በወቅቱ የሚቀበላቸው አጥተው ሠርክ በማንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ በየቅርንጫፍ ቢሮዎች ያለው እንግልት፣ ደንበኛን መሳደብ፣ ማንጓጠጥ፣ በደልና ትምክህት ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ርትእ ምን ያህል እንተዋረዱ ማረጋገጫ ነው፡፡
ይህ መሥርያ ቤት ደንበኞች የተጠቀሙበትን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ለመፈጸም ከስድስት ወራት በላይ ያመላልሳል፤ ያጉላላል፤ ያመናጭቃል፡፡ ከማጉላላቱ በተጨማሪ ተገቢ ያልሆነ የኪሎዋት ጭማሪ ስሌት በመሥራት ደንበኞች ፍትሃዊ ያልሆነ ክፍያ እንዲፈጽሙ ያስገድዳል፡፡ እርሱ ክፍያ በወቅቱ አልተከፈለኝም ብሎ ባመነ ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲያቋርጥ ግን “ኧረ ተው!” የሚለው የለም፡፡ ድርጅቱ ሲበዛ አምባገነን ነው፡፡
ለዚህም ማረጋገጫ ከዊንጌት አደባባይ ከፍ ብሎ ካለው የድርጅቱ ቢሮ ጀምሮ በየቦታው ዞሮ ማየት ይቻላል፡፡ እኔ የዚህ ማስታወሻ ጸሐፊና የሰፈሬ ሰዎች ያየነው ስቃይ በጽሑፍ መግለጽ አይቻለንም፡፡ መቼም ፍርድ ከላይ ነውና ደንበኞችን የሚያንገላቱ እንደ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅትና በመሳሰሉ የግልና የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ላይ ፍርዱን ይስጥ፡፡ ከምድርማ ሺህ ጊዜ ለውጥ፣ ለውጥ ቢባል ጠብ የሚል እንደሌለ አይተን አረጋግጠናል፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን ነገረ ሁኔታ አይተን “አገር ሲያረጅ ጃርት ታበቅላለች”፣ ብንል ያንሳል እንጂ አይበዛም፡፡ የአገራችን ዙሪያ ገባ ላስተዋለ በሁሉም አቅጣጫ ያስፈራል፡፡ አንድዬ ምህረቱን ይላክልን፡፡ አሜን!
ብርሃነ ዓለሙ – ተበዳይ ደንበኛ፡፡