Connect with us

የኢሳት ውስጣዊ ሽኩቻ በተመለከተ

የኢሳት ውስጣዊ ሽኩቻ በተመለከተ
ኢሳት

ዜና

የኢሳት ውስጣዊ ሽኩቻ በተመለከተ

የኢሳት ውስጣዊ ሽኩቻ በተመለከተ

~ የዋሽንግተን ዲሲ ኢሳት ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አጌና መታገዳቸውን ኤዲቶሪያል ቦርዱ ተቀብሎታል፣

ከኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

  የካቲት 20 ቀን 2013 ዓ.ም

 የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ ከኢሳት ምስረታ አንስቶ የተቋሙ ተልዕኮ ግቡን እንዲመታ የተሰጠውን ሃላፊነት በብዙ ፈተናዎች ተከቦ ሲወጣ ቆይቷል። ኣሁንም ይህንኑ ሃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል። ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርገውን የነጻነት፡ የፍትህና የዲሞክራሲ ትግል ለማገዝ የተመሰረተ የሚዲያ ተቋም በመሆኑ ይህንን ሀገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ እየተጫወተ ያለው ሚና የላቀ ስፍራ የሚኖረው እንደሆነ ይታመናል። 

ሃላፊነት በሚሰማቸው፡ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጽኑ አቋም ባላቸው፡ ለፍትህና ዲሞክራሲ መረጋገጥ ከፍተኛ ዋጋ በከፈሉ የተቋሙ ጋዜጠኞች የሚመራው የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ፥ ኢሳት ታማኝነቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ኣድርጎ ከትኛውም የፖለቲካ ፣የብሄር  እና መደብ እንዲሁ የእምነት አቋም እና ዝንባሌ ገለልተኛ በሆነ የኢዲቶሪያል ኣቅጣጫ እንዲመራ በፍጹም ቅንነትና ትጋት እየሰራ ይገኛል። 

በየሳምንቱ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፡ ኢኮኖሚያዊና የተለያዩ ክንውኖችን በመፈተሽና በጥልቀት በመመርመር፥ ኢሳት ከተቋቋመለት ዓላማና የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስቀድም መልኩ የዜና ክንውኖችንና  የፕሮግራም ሀሳቦችን አቅጣጫ በማስቀመጥ ሲሰራ የቆየ አካል ነው። 

የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ ባለፉት 11ዓመታት በብርቱ ፈተናዎች ውስጥ አልፏል። ፈተናዎቹ ውስጣዊና ውጪያዊ የሆኑና በየጊዜው የተቋሙን ህልውና አደጋ ውስጥ የከተቱ ነበሩ። እስከመዘጋት ሊያደርሱ የሚችሉ አደጋዎች ሲገጥሙት ከሌሎች የተቋሙ መዋቅሮችና በዓለም ዙሪያ በገንዘብና በተለያዩ ድጋፎች ከተሰለፉ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ እልህ አስጨራሽ ትግሎችን አድርጓል። 

የህወሀት አገዛዝ ከተወገደ በኋላ በነበሩት ሶስት ዓመታት ኢሳት በብርቱ የተፈተነበት፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኣደጋዎች ፈጠው የመጡበት ቢሆንም በኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች በጽናትና በአንድነት በመቆም ኢሳት ወጀቡንና ማዕበሉን እንዲሻገር አድርገውታል።ኢሳት ውጫዊውን ወጀብ ተቋቁሞ ሕልውናውን አረጋግጦ በክበር እንደገና ቀና ሲል በወላፈኑ ውስጥ አልፈው ኢሳትን እንደገና ቀና ያደረጉትን ጋዜጠኞች ገፍቶ ፣ የተቋሙን ሕዝባዊነት የመግፈፍ እርምጃዎች ቀጠሉ።

  ኢሳትን ከሰሞኑ የገጠመውና ብዙዎችን ደጋፊዎቹን ያሳዘነው ጉዳይም ኢሳት ትክክለኛና እውነተኛ ህዝባዊ ተቋም እንዲሆን በሚፈልጉና በህዝባዊነት ሽፋን የተወሰኑ ቡድኖች ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ እየሰሩ በሚገኙ ወገኖች መሀል የተፈጠረ አለመግባባት ነው። 

የአለመግባባቱ መነሻ ኢሳትን ህዝባዊ በማድረግ ረገድ ያለው ልዩነት ብቻ ሳይሆን በኢሳት የስራ አመራር ቦርድ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አባላት በውጭ የሚገኘውን የኢሳት ስቱዲዮ ለመዝጋት በተደጋጋሚ ያደረጉት ተገቢ ያልሆነ ውሳኔም ጭምር ነው። 

ባለፉት ሶስት ዓመታት የኢሳትን የውጭ ስቱዲዮ ለመዝጋት በኢሳት የስራ አመራር ቦርድ ውስጥ ባሉ አንዳንድ ግለሰቦች አማካኝነት ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶችን በማክሸፍ ረገድ የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ ከፍተኛ ትግል አድርጓል። በተጠናና በረቀቀ መልኩ የውጭውን ኢሳት የፋይናንስ አቅም በማዳከም ለመዝጋት የተደረጉት ጥረቶች፣ ዛሬም ጭምር የቀጠሉ ሙከራዎች  የኢሳት ጋዜጠኞችን በእጅጉ አሳዝኗል። በኢሳት ህዝባዊነት ላይ የማይናወጥ አቋም ያለው የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ በውጭ በሚገኙ ጋዜጠኞች የሚመራ በመሆኑ የውጭውን ስቱዲዮ የመዝጋቱ አንዱ ዓላማም በተቋሙ ህዝባዊነት ላይ የማይደራደሩትንና ላለፉት 11 ዓመታት የኤዲቶርያል ቦርድ አባላት የሆኑትን ጋዜጠኞች ከሜዳው በመግፋት ኢሳትን በፈለጉትና ባቀዱት አደረጃጀት እንደ ኣዲስ ለማዋቀር መሆኑን ተረድተናል።

   በእርግጥ የኢሳት የስራ አመራ ቦርድ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦች ኢሳትን በተሳሳተ መልኩ ለማደራጀት የያዙትን መስመርና በውጭ የሚገኘውን ስቱዲዮ ለማዳከም የጀመሩትን እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ በርካታ የውስጥ ትግሎች ተካሂደዋል። 

የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ ተከታታይ ደብዳቤዎችን በመጻፍና ውይይቶችን በማካሄድ የተሳሳተው መስመር እንዲታረም ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። ሊቀመንበሩን ጨምሮ  አንዳንድ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት  በማያውቁት ሕገወጥ አሰራርና አካሄድ የተወሰኑ ግለሰቦች ከህግና ከአሰራር ውጭ  በቦርዱ ስም ውሳኔዎችን ሲያሳልፉና ተግባራዊ ሲያደርጉ መቆየታቸው ችግሩ አንዲባባስ አድርጎታል። 

የኢሳትን ህዝባዊነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት በማሰናከል የተለየ አቅጣጫ የጀመሩት እነዚህ ግለሰቦች ኢሳትን አደጋ ውስጥ ከመክተታቸው በፊት የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት ተሰብስበው ጉዳዩን ህዝብ እንዲያውቀው ለማድረግ በመስማማት በዕለታዊ ፕሮግራም ላይ ችግሩን በመጠኑ ፈንጥቀዋል። 

የኢሳት ችግር ለአደባባይ መብቃት አብዛኛውን ህዝብ እንደሚያሳዝንና እንደሚያስከፋ ብንረዳም በውስጥ ለመፍታት ያድረግነው ጥረት ባለመሳካቱና  አማራጭ የሌለው ሆኖ በመገኘቱ አደባባይ ለመውጣት መገደዳችንን መግለጽ እንወዳለን።

  የኢሳት የስራ አመራር ቦርድ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦች አሁንም ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የማወሳሰብና ህዝብን የማደናገር እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ተገንዝበናል። በዕለታዊ ፕሮግራም ላይ ችግሩን በተመለከተ ለህዝብ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የኢሳት ቦርዱ ሊቀመንበር ዶ/ር ሰለሞን ረታ የወሰዱት እርምጃ የኢሳትን ህልወና ከአደጋ ለመጠበቅ በሚል እንደሆነ የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ ተረድቶ ቢቀበለውም፣ የኢሳት ቦርድ ሊቀመንበሩን ከአባልነትና ከሊቀመንበርነት ማገዱ ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት  አለመኖሩን አስገንዝቦናል። ጥቂት የማይባሉ  የቦርድ አባላት ኢሳት ውስጥ ስላለው ችግር የተሳሳተ እና የተዛባ መረጃ እንደሚደርሳቸውም ተረድተናል።

እኒህ ወገኖች  በቀጣይ ዕውነተኛው መንገድ ላይ እንደሚገኙም  እናምናለን።የበኢሳት ውስጥ የተፈጠረው ችግር በጥቂት የቦርድ አባላት እና በጋዜጠኞች መካከል ሆኖ ሳለ ፣ቦርዱ ጉዳዩን  በዶ/ር ሰለሞን እና በቦርዱ መካከል የተፈጠረ ልዩነት  በማስመሰለ ዕውነተኛውን ችግር ለማድበስበስ ያወጣው መግለጫም ቅንነት የጎደለው  እና ከዕውነታው የሚደረግ ሽሽት ሆኖ አግኝተነዋል። 

ቦርዱ በኢሳት ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት አቅጣጫ ተቀምጧል በሚል በኢሳት አዲስ አበባ የተሰራጨው መግለጫም  የስራ አመራር ቦርዱን ቅንነት ያጠረው አካሄድ ያጋለጠ መሆኑንም ተገንዘበናል። የችግሩ ዋና አካል ራሱን  መፍትሄ ሰጪ አድርጎ ማቅረቡ ለውይይት ያለውን እድል አበላሽቶታል  ከሚል ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ አድርጎናል።

   የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት በዶ/ር ሰሎሞን የተወሰደው እርምጃ ተገቢነት ያለው እንደሆነ እናምናለን። ርምጃው የዋሽንግተን ዲሲ ስቱዲዮ ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን ጭምር  የሚያግድ ቢሆንም፣ ለኢሳት ህልውና መረጋገጥ በሚል የተወሰደ ስለሆነ ቅሬታ ቢኖረንም ተቀብለነዋል። በአንጻሩ በስራ አመራር ቦርዱ ውስጥ የሚገኙ ተመሳሳይ እርምጃ የተወሰደባቸው ግለሰቦች ይህን የሊቀመንበሩን እርምጃ እንደወንጀል ቆጥረው እስከማገድ መድረሳቸው ከተቋሙ ሕልውና በላይ የራሳቸው ክብር የሚያጨንቃቸው መሆኑን ያስገነዝበናል።

በተጨማሪም መግለጫውን በአዲስ አበባ የኢሳት ስቱዲዮ የተላለፈበት መንገድ ዶ/ር ሰሎሞንን ነጥሎ የችግሩ ተጠያቂ በማድረግ ህዝቡን ሆን ብሎ ለማደናገር መሆኑ የስራ አመራር ቦርዱ ለእውነተኛና ቅንነት ለሚያስፈልገው ውይይት ያልተዘጋጀ መሆኑን የሚያመላክት ነው።የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት በስራ አመራ ቦርዱ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች የቦርዱን አብዛኛውን አባላት ይሁንታ ያገኙ ናቸው የሚል እምነት የለንም። 

ሰሞኑን የቦርዱን ሊቀመንበር ከማገድ አንስቶ በተወሰዱ እርምጃዎች አንጻር የብዙሃኑ የቦርዱ አባላት አቋም የተለየ እንደሆነ ተረድተናል። ኢሳት ለገጠሙት ፈተናዎች ምንጭ የሆኑና አሁንም እንዲባባስ ሚና እየተጫወጡ የሚገኙት የተወሰኑ የቦርዱ አባላት መሆናቸውንም አንገነዘባለን።

   የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ ኢሳት አሁን ከገጠመው የህልውና አደጋ እንደሚወጣ ጽኑ እምነት አለው። በብርቱ ችግሮች ሲፈተን የቆየ ተቋም አሁንም ይህንን አደጋ ተሻግሮ ህዝብን በማገልገሉ ተልዕኮው እንደሚቀጥል ለኢትዮጵያ ህዝብ ልናረጋግጥ እንወዳለን።

ኢሳት ኢትዮጵያዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ዕውቀታቸውን፣ገንዘባቸውንና ግዚያቸውን ሳይሰሰቱ ለሰጡ ፣ድጋፍ በማስተባበር እስከዛሬ ከጎናችን  ለነበሩ እና ላሉ  ምስጋና እያቀረብን፣ ኢሳትን ህዝባዊ ተቋም የማድረጉ ተልዕኮ  የማይቀለበስ መሆኑን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን።ኢሳት ነጻና ገለልተኛ  ሕዝባዊ ተቋም ሆኖ ሀገራዊ ድርሻውን የሚወጣበትን የተጠናከረና የተሻለ መስመር ለመዘርጋት ተዘጋጅተናል። ኢሳት የህዝብ ነው።

 ህዝባዊ ተቋም ሆኖ ተልዕኮውን በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል።እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም  መላው ኢትዮጵያዊ ከጎናችን እንዲቆም  ጥሪ እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top