ምርጫ 2013 ፡- ስጋትና ተስፋ በደቡብ ኢትዮጵያ
(ፍሬው አበበ)
የፌዴሬሽን ምክርቤት የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች 11ኛ የኢትዮጵያ ክልል መሆን እንዲችሉ ያቀረቡትን ጥያቄ በምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የፊታችን ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ምርጫ ቦርድ ቀጠሮ ይዟል፡፡
ደቡብ ምዕራብ የሚባለው የከፋ፣ የቤንች ሸኮ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ ዳውሮና ሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ በጋራ ያካትታል፡፡ መጪው ሕዝበ ውሳኔ (እንደብዙዎች ግምት) 11ኛውን የኢትዮጵያ ክልል ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋን ፈንጥቋል፡፡
አዲሱ የለውጥ አስተዳደር ወደስልጣን ከተሳበ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የአደረጃጀት ጥያቄዎችና እሱንም የተከተሉ አለመግባባቶችና ደም አፋሳሽ ግጭቶች ታይተዋል፡፡
ይኸንንም ተከትሎ የሲዳማን የክልል እንሁን ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ በማካሄድ 10 ኛ ክልል በመሆን የተፈታ ሲሆን የሌሎች 10 የሚጠጉ ብሔር ብሔረሰቦች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ገና ምላሽ አላገኙም፡፡ ከክልል እንሁን ጥያቄ በተጨማሪም ወደዞን እና ወደልዩ ወረዳ ደረጃ እንደግ የሚሉ ጥያቄዎች መበራከት ለግጭትና አለመረጋጋት በር ከመክፈት ባሻገር ለመንግስትም ራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይኸም ሆኖ ችግሮቹ በተሟላ ሁኔታ ባልተመለሱበት በዚህ ወቅት 6ኛ ሀገር አቀፍ ምርጫ እንደድንገተኛ ደራሽ ውሃ ደርሷል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች የሕዝበ ውሳኔ ጨምሮ የሌሎቹን የአደረጃጀት ጥያቄዎች በተሟላ መልክ መልስ ሊሰጥ የሚችለው ከምርጫ በኋላ በሚመሰረተው አዲሱ አስተዳደር እንደሚሆን ይገመታል፡፡
አሁን አንገብጋቢው ጉዳይ እነዚህ ጥያቄዎች መልስ አለማግኘታቸው በቀጣዩ ምርጫ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖር ይሆን የሚለው የብዙ ወገኖች ወቅታዊ ጥያቄና ስጋት ሆኖ መታየቱ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት እና በደቡብ ክልል አደረጃጀት ጉዳዮች የተለያዩ ኮምቴዎች ውስጥ ያገለገሉት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድሙ ችግሩ የቆየና ውስጥ ወስጡን ሲብላላ የሰነበተ ነው ካሉ በኃላ ይህንን የተጠራቀመ ችግር ደረጃ በደረጃ እንጂ በአንድ ጊዜ ለመፍታት አስቸጋሪ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ስለጉዳዩ ወደኋላ መለስ ብለን እንመልከት፡፡ ቀድሞውኑ ችግሩ ከ50 በላይ በክልሉ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድ ላይ እንዲጨፈለቁ መወሰኑና መተግበሩ ነው ይላሉ፡፡ ይህ መሆኑም አንድ ሰው ከቦንጋ ተነስቶ ሐዋሳ ድረስ ለአስተዳደራዊ ጉዳይ ረዥም ረቀት እንዲጓዝ፣ እንዲጉላላ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላትም ገንዘባቸውን በትራንስፖርትና በአበል እንዲጨርሱ ተገድደዋል ይላሉ፡፡
በግሌ በተለያዩ መድረኮች ያንጸባረኩት አቋም የደቡብ ክልል ጉዳይ እያንዳንዱን ብሔር/ ብሔረሰብ ክልል በማድረግ የሚፈታ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ይልቅስ አሁን ደቡብ ምዕራብ እንደተባለው በክላስተር ተደራጅተው የክልል ስም ቢይዙ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ የአስተዳደር ስራውንም ለማቀላጠፍ የተሻለ መንገድ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በፕሮፌሰር በየነ ጼጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ተክሉ ሸዋ ስለጉዳዩ በሰጡት አስተያየት መጪው ምርጫ እና የአስተዳደር ጥያቄዎች የተለያዩ ናቸው፤ መደበላለቅ ለባቸውም፡፡ ራሳቸውን ችለው የሚጓዙና የሚፈቱ በመሆናቸው ከምርጫው ሐደት ጋር ስለማይገናኝ እንደችግር መታየት የለባቸውም ባይ ናቸው፡፡
“የምርጫው ሐደት የሚከናወነው በቀድሞ መዋቅር ነው፡፡ ጥያቄዎቹ አሁንም ሆነ ወደፊት በተከታታይ እየተነሱ መልስ እያገኙ የሚሄዱ በመሆናቸው በተለይ የኢሶዴፓ አባላት በምርጫው በመሳተፍ የአደረጃጀት ጥያቄያቸው እንዲፈታ እንዲጥሩ ተገቢውን ሁሉ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግን ፤ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች ጥያቄያቸው መልስ ከማግኘቱ በፊት ምርጫ መካሄዱ ላያስደስታቸው ይችላል፡፡ እናም የተወሰነ ቅሬታ በገዥው ፓርቲ ላይ ሊኖራቸው ስለሚችል ይኸ ወደአልተፈለገ ግጭት እንዳያመራ ገዥው ፓርቲ አስቀድሞ ሕዝቡን የማሳመን ስራ ሊያከናውን ይገባል ይላሉ፡፡
ሰማቸውን እንዲገለጽ ያልፈለጉ የጉማይዴ ሕዝብ የሰላም ኮምቴ አባላት መጪው ምርጫ የግጭትና የብጥብጥ እንዳይሆን ምርጫ ቦርድ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ በአካል ተገኝተን አስረድተናል ብለዋል፡፡
በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን በደራሼ፣ በአማሮ፣ በቡርጂ ልዩ ወረዳዎች የሚዋሰነው የጉማይዴ ሕዝብ ወደልዩ ወረዳነት እንዲያድግ ሕዝቡ ጥያቄ በማቅረቡ ብቻ በክልል ታጣቂ ኃይሎች ማሳደድ፣ እስር፣ እንግልት እና መፈናቀል እንዳጋጠመው በመጥቀስ ይህ ተጨባጭ ሁኔታ ባለበት ምርጫ እንዴት ሊካሄድ እንደሚችል አልገባንም ብለዋል፡፡ “ሕዝቡ ከቤት፣ ንብረቱ ተፈናቅሎ ጫካ ነው ያለው፡፡ አንዳንዱም ታስሯል፣ ተሰዷል… ማንነው መራጩ? ማንነው አስመራጩስ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ጉዳዩንም አዲስአበባ ድረስ በመሄድ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአካል ተገኝተው አቤቱታ ማቅረባቸውን የኮምቴው አባላት ጠቅሰው ቦርዱ ሁኔታውን ምርምሮ ተገቢውን መልስ በመስጠት ግጭትን ያስቀራል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
በኮምቴ አባላቱ እምነት ከምርጫው በፊት የህዝቡ ችግር ሊቀረፍ እንደሚገባና የተሰደደው ሕዝብ ወደቀዬው መመለስ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ አባል እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ጀማል ከድር ለዚህ ጹሑፍ አቅራቢ በሰጡት አጭር አስተያየት መጪው ምርጫ በመካሄዱ ምክንያት የአደረጃጀት ጥያቄ ያነሱ በክልላችን የሚገኙ ወገኖቻችን ወደግጭት ይገባሉ የሚለው አስተሳሰቡ በራሱ የተሳሳተ ነው ብለው እንደሚምኑ ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ክልል ያለውን የአደረጃጀት ጥያቄ ብልጽግና ፓርቲ የወለደው ሳይሆን ላለፉት 27 አመታት ሳይመለስ የቀረና የቆየ መሆኑን አስታውሰው ፓርቲያቸው ብልጽግና ጉዳዩ በሳይንሳዊ መንገድ መፍትሔ ለመስጠት ወስኖ ብዙ ስራ እያከናወነና ተራ በተራ ምላሽ እየሰጠ መምጣቱን በማስታወስ ወደግጭት የሚያስገባ አንዳችም ምክንያት ስለሌለ ግጭት ይነሳል የሚል ምንም አይነት ስጋት የለም ነው የሚሉት፡፡
ፓርቲያችን በተደጋጋሚ የመጪው ምርጫ በተሳካ ሁኔታ መካሄድ የህዝቡን የአደረጃጀት ጥያቄ በተሟላ መልኩ ለመመለስ የሚያስቸል እንጂ እንቅፋት የሚሆን ባለመሆኑ የክልላችን ሕዝብ ለተግባራዊነቱ እንዲታገል በተቻለ መጠን እያስረዳን እንገኛለን ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሰሞኑን በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ለ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ በእጩነት ስትመዘገቡ ወይም እንደ ፓርቲ እጩዎቻችሁን ስታስመዘግቡ ከፊታችን ያለው መንገድ ከፊል ተስፋ፣ ከፊል ስጋትን አዝሎ እንደሚጠብቃችሁ፣ እንደሚጠብቀን ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡
ይሁንና ስጋትን ለመቀነስ ብሎም ወደ መልካም ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችለን አቅም እና እድል በየፈርጃችን ይዘን ይህን የጋራ ሙከራችንን በዝለት ሳይሆን በጥንካሬ ልንጀምረው ይገባል…” ማለታቸውን አንብበናል፡፡ (ማስታወሻ፡- ለዚህ መጣጥፍ ስኬታማነት ኢንተር ኒውስ ኢትዮጵያ ድጋፍ አድርጓል)