በትግራይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ አግኝተዋል
በትግራይ ክልል ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉ ተገለጸ።
በክልሉ በሚገኙ የስደተኛ ካምፖች የነበሩ የኤርትራ ስደተኞች ጠፍተዋል የሚባለው መረጃ ሀሰት ነው ተብሏል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ስላለው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲሁም የስደተኛና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
እስከ ትናንት ባለው መረጃ በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 2 ሚሊዮን 7 ሺህ 882 ዜጎች ድጋፍ ማግኘታቸውንና 392 ሺህ 640 ኩንታል የምግብ አቅርቦት ለዜጎቹ መድረሱን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ የተገዛ 200 ሺህ ኩንታል ስንዴ ከጅቡቲ ወደብ ወደ መቀሌ ማዕከላዊ መጋዘን የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው የምግብ ነክ ሰብዓዊ ድጋፍ 70 በመቶ በመንግስት ወጪ 30 በመቶው በማህበር ረድኤት ትግራይ አማካኝነት እየቀረበ እንደሚገኝም ነው አቶ ምትኩ ያስረዱት።
ከዚህ በተጨማሪ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከአምስት ዓመት በታች እድሜ ላላቸው ህጻናት፣ነፍሰ ጡርና የወለዱ እናቶች ንጥረ ነገር ያላቸው አልሚ ምግቦችን እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች መካከል 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት ኮሚሽነሩ ይሄንንም ድጋፍ በመንግስት ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች እያገኙ እንደሆነ አመልክተዋል።
በሰብአዊ ድጋፍ የምግብ አቅርቦት ስርጭት በሚፈለገው ፍጥነት አለመሄድ፣ በመመሪያ ከተፈቀደው በላይ ድጋፍ መውሰድና ዜጎችን ድጋፍ እንዳይወስዱ ማስፈራራት በአቅርቦት ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው ብለዋል።
ችግሮቹን ለመፍታት ባለሙያዎችና ህብረተሰቡን ያሳተፈ ቡድን በየቦታው በመላክ የአቅርቦቱ ሂደት ፍትሐዊ መሆኑን የማጣራትና የሰብአዊ ድጋፍ መመሪያ በጽሁፍ በማዘጋጀት እንዲሰራጭ መደረጉን ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ላላገኙ 500 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በተያዘው ሳምንት ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እንደሚከናወንና የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ እንደሚጠናቀቅና የሁለተኛ ዙር ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሰዎች ቁጥር ለማወቅ የሚያስችል የጥናት ቡድን በክልሉ መሰማራቱን አመልክተዋል።
የጥናት ቡድኑ ቁጥራዊ መረጃዎችን ካመጣ በኋላ ሁለተኛ ዙር የሰብአዊ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
ዜጎች ከእርዳታ ተላቀው በዘላቂነት የራሳቸውን ገቢ የሚያመነጩበት ሁኔታ ላይ የሚሰራ ከመንግስት የልማት አጋሮች የተወጣጣ ቡድን መቋቋሙንና ቡድኑ በሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ አክለዋል።
የስደተኛና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው ከሕግ ማስከበር እርምጃው በፊት ባለው ቁጥራዊ መረጃ መሰረት ወደ 200 ሺህ የሚሆኑ የኤርትራ ስደተኞች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከነዚህም ውስጥ 92 ሺህ ገደማ የሚሆኑት በትግራይ ክልል እንደሚገኙና ከ40 ሺህ በላይ ዜጎች በስደተኞች ካምፕ የተቀሩት ከካምፕ ውጪ የሚኖሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በአዲ ሐሩሽና ማይ አይኒ የስደተኛ መጠሊያ ካምፖች 28 ሺህ ስደተኞች እንዲሁም 19 ሺህ 200 በህጻጽና ሽመልባ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ደግሞ 19 ሺህ ስደተኞች ይገኙ ነበር ብለዋል።
መንግስት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ ሲጀምር በአራቱ የስደተኛ መጠልያ ካምፖች የኤርትራ ስደተኞች ያገኙት የነበረው አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር አውስተዋል።
በሕግ ማስከበር እርምጃው በህጻጽና ሽመልባ የስደተኞች ካምፖች የነበሩ የኤርትራ ስደተኞች ከካምፕ መውጣታቸውን አመልክተዋል።
በአንጻሩ ከመንግስት እርምጃ በኋላ በአዲ ሐሩሽና ማይ አይኒ የስደተኞች መጠልያ ካምፖች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።
ህጻጽና ሽመልባ የስደተኛ ካምፖች የሚገኙባቸው አካባቢዎች የሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ እስከሚሆን በሁለቱ ካምፖች የሚገኙ ስደተኞች አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ኤጀንሲው እየሰራ መቆየቱን ነው አቶ ተስፋሁን ያስረዱት።
በዚሁ መሰረት ከህጻጽና ሽመልባ ካምፖች የወጡ ከ4 ሺህ 600 በላይ ስደተኞች ወደ አዲ ሐሩሽና ማይ አይኒ የስደተኛ ካምፖች እንዲመጡ መደረጉንና የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እየተደረገላቸው እንደሆነ አመልክተዋል።
በካምፖቹ ከሚገኙት 19 ሺህ ስደተኞች መካከል ኤጀንሲው 10 ሺህ የሚሆኑትን በማጣራት አግኝቷል ማለት ከ9 ሺህ በላይ ስደተኞች ያሉበት አይታወቅም ማለት እንዳልሆነና ጠፍተዋል የሚባለው መረጃ ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል።
ኤጀንሲው ቀሪዎቹ ስደተኞች በተለያዩ ቦታዎች እንዳሉ ቢያውቅም ነገር ግን የስደተኛ መታወቂያ እንዳላቸው የማጣራት ስራ ማከናወን እንዳለበት ተናግረዋል።
በማይአይኒ አዲ ሀሩሽ ካምፖች የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት የጤና፣ውሃና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ከሁለቱ ስደተኞች ካምፕ ውጪ የሚገኙና ኤጀንሲው በማጣራት የደረሰባቸውን ስደተኞች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በያሉበት ሆነው ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ሰአት ሽመልባና ህጻጽ የስደተኛ ካምፖች አገልግሎት እየሰጡ እንደማይገኝ አመልክተዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን መስፈረት የስደተኛ ካምፕ ለጥንቃቄ ሲባል ከድንበር 50 ኪሎ ሜትር መራቅ እንዳለበትና የሽመልባ ካምፕ ግን ከኤርትራ ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ በመሆኑ የካምፕ መስፈርትን አያሟላም ብለዋል።
የህጻጽ የስደተኞች ካምፕ በበረሃ የሚገኝና ለኑሮ አመቺ አለመሆኑን አመልክተዋል።
ስለዚህም በቀጣይ ኤጀንሲው የሽመልባና ህጻጽ የስደተኞች ካምፖች በመዝጋት የኤርትራ ስደተኞች በአዲ ሀሩሽ ማይ አይኒ የስደተኞች ካምፕ አገልሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
በተጨማሪም ከህጻጽና ሽመል ከወጡ ስደተኞች መካከል በከተማ መኖር ለሚፈልጉ ስደተኞች የከተማ መታወቂያ የመስጠትና ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ የማድረግ ስራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።
መንግስት ለኤርትራ ስደተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለዋል።(ኢዜአ)