በነዳጅ ዋጋ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል፤ ለምን?
(ሙሼ ሰሙ)
ይህንን ጽሁፍ ፌስ ቡክ ላይ በትንሹ ማቅረብ በማንኛውም መለኪያ ፈታኝ ነው። ዝምታ ደግሞ ስህተት ነውና ይህንን ማለት ተገቢ ስለሆነ በቁንጽል ይህንን ብያለሁ።
አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ በነዳጅ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ የጭማሪው መንስኤ መንግስት በነዳጅ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ ማቆም አለብኝ ስላለ ነው። ይህም ሆኖ መንግስት የድግስና የአስረሽ ምችው ወጭውን በመቆጠብ ዙርያ ምን እንዳሰበና እያደረገ እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም። ለምን ?
የውጭ ምንዛሪ ያሳደረብን የዋጋ ንረትና ግሽበት መጨረሻውን እያየን አይደለም። በዚህ ወር ብቻ ግሽበት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከ19 በመቶ በላይ በማስመዝገብ ሁለተኛው የግሽበት ታሪክ ሆኗል። ካላፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ፣ ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ከመታወቂያ እደሳ ጀምሮ መብራት፣ ውኃ፣ ኪራይና መዋጮን ጨምሮ ወዘተ ከ100 % እስከ 300% ከፍተኛ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡
በተቃራኒው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመንግስት ሰራተኛና ጡረተኛና ወዘተ ገቢው ለዓመታት ትርጉም ያለው ለውጥ አላሳየም፡፡ በዚህ ላይ ነዳጅ ከምርት ግብአትነት ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ ስለሆነ፣ ሊያቀጣጠል የሚችለው የዋጋ ንረትና ግሽበት ድርብ ድርብርብ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡
ይህ ደግሞ በቋፍ ያለውን ኑሯችንን እየተፈታተነ ነው። ስጋን ትተን ዳቦና እንጀራ ከ30 በመቶ በላይ ጨምሯል።
ለውጥ ያላየው ደሞዝተኞች፣ ጡረተኞችና ዝቅተኛ ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ገቢያቸው ለተደራራቢ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ከመጋለጡም በላይ፣ ከዓመት ወደ ዓመት በሚሸጋገር ተደራራቢ ግሽበት የተነሳ የመግዛት አቅማቸው እየሟሸሸ ነው ፡፡ ዞሮ፣ ዞሮ ደግሞ ውጤቱ ከእለት ጉርሳቸው ውጭ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶችን እንኳን መግዛት የማይችሉበት አስጊ ሁኔታ መፈጠሩ እየታየ ነው።
በዚህ መንገድ ኢኮኖሚያችን እንደተቀየደ ከቀጠለ፣ የዜጎች አቅም ቀስ በቀስ ተመናምኖ፣ የእለት ፍላጎታቸውን እንኳን መሸፈን የማይችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ግልጽ ነው ፡፡ ፍላጎት አለመኖር ማለት ደግሞ አጠቃላይ ሀገራዊ የእድገትና ነኢንቨስትመንት መቀጨጭ፣ ብሎም መጥፋት ነው፡፡ ውሎ አድሮም መንግስት፣ ነጋዴውንና ዜጎችን እኩል ድሃ በመድረግ፣ ሀገርን ማክስር ነው።
በጥቅሉ፣ የአቅርቦት ፈተና ባለባቸው ሃገራት፣ አቅርቦት በሚፈለገው መጠን እስካላደገ ድረስ የደሞዝ ጭማሪ ፍላጎትን ከመለጠጥና ዋጋን ከማናር ውጭ፣ የመግዛት አቅምን ማሻሻል አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ድጎማ የአጭር ጊዜ ( Short term) መፍትሔ ከመሆን ውጭ፣ መሰረታዊ ችግሮችን አይፈታም።
ድጎማ፣ ፍላጎትን ከማናርና ከአቅም በላይ መኖርን ከማጎልበትና አቅም የሌላቸውን ዜጎች ብቻ ሳይሆን አቅም የሌላቸውንም ጭምር በጅምላ ከመደጎም ወጭ መፍትሔ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የመንግስት ወጪን ያንራል፣ ልማትን ያኮስሳል ፣ እድገትን ይጻረራል፡፡
ምን ይሻላል ? ፈታኙ ጥያቄ ይህ ነው፡፡
አብዛኛዎቹ ድሃ ሀገራት ዜጎቻቸው እንዳይጎዱ፣ ነዳጅን ይደጉማሉ፣ ድጎማ ለነሱ የተለየ ፈተና አይደለም። ሀብታም ሃገራት ግን የዜጎቻቸው የመግዛት አቅምና አቅርቦት የተሻለ ስለሆነ ነዳጅ ላይ የተለየ ታክስ በመጣል ዋጋውን አንረው ብክነትንና የአየር ብክለትን ይከላከላሉ።
በጥቅሉ የደሞዝ ጭማሪ የኑሮ ሁኔታን ማሻሻል ካልተቻለ ወይም በአጭር ጊዜ አቅርቦትን ማሳደግ ፈታኝ ከሆነ ፣ ደሞዝን ከማሳደግ ይልቅ መሰረታዊ አቅርቦቶችን በመደጎም ከሁለቱ መጥፎዎች የተሻለውን መጥፎ መምረጥ ግዴታ ነው፡፡ በተለይ፣ ሀገረ የድግስና ዳንኪራነቱን ትቶ ወጭ መቆጠብ ከጀመረ መፍትሔው ጥሩ ነው።
ድጎማንም ሆነ የደሞዝ እድገትን በአንድ ላይ መንፈግ ግን በግሽበትና በዋጋ ንረት ኑሮውና ሕይወቱ የሚታመሰውን የሰራተኛ/ ጡረተኛ/ በዝቅተኛ ኑሮ ፈተና ላይ የሚገኘውን ዜጋ ምግብ ሳትበላ ኑር ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመጀመርያ ማህበራዊ ቀውስ የሚቀሰቅስ ቀጥሎ ደግሞ አለመረጋጋትን መቀስቀሱ የማይቀር ነው፡፡