Connect with us

ታላቁ የአስዋን ግድብና የቶሽካ ፕሮጀክት ምን ያህል የዓባይ ውኃ ይበቃቸዋል?

ታላቁ የአስዋን ግድብና የቶሽካ ፕሮጀክት ምን ያህል የዓባይ ውኃ ይበቃቸዋል?
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ታላቁ የአስዋን ግድብና የቶሽካ ፕሮጀክት ምን ያህል የዓባይ ውኃ ይበቃቸዋል?

ታላቁ የአስዋን ግድብና የቶሽካ ፕሮጀክት ምን ያህል የዓባይ ውኃ ይበቃቸዋል?

      – እስክንድር ከበደ

‹‹ሚስትሪ ኦፍ ናይል ሪቭር›› (የናይል ሚስጥር) የሚለው ዘጋቢ ፊልም በጂኦፊዚስቱ ፓስኳልና ባልደረቦቹ የዓባይን ወንዝ ከመነሻ እስከ መድረሻው ያሰሱበትን የ3,000 ማይሎች ጉዞ ያስቃኘናል። በዚህ ዘጋቢ ፊልም ኢትዮጵያዊት ሕፃን የአንገት ጌጥ አውልቃ ለቡድኑ ሴት አሳሽ አንገት ላይ ታደርግላታለች። ይህ የኢትዮጵያዊት ሕፃን ንፁህ ፍቅር እናያለን።

ይህ የአንገት ጌጥ የአሳሽ ቡድኑ ግብፅ ሲደርስ የአንገት ጌጡን ከኢትዮጵያዊ ሕፃን ላይ የወሰደቸው የቡድኑ አባል ካይሮ ስትደርስ፣ በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ ላለች ግብፃዊት ሕፃን አንገት ላይ ታጠልቅላታለች። የዓባይ ልጅ ኢትዮጵያዊት ሕፃን ለዚያች የግብፅ ሕፃን ጌጥ ብቻ ሳይሆን ፍቅርን ልካለች። ዓባይ ለዘመናት ለግብፅ ለም ውኃና ለም አፈር ስትገብር ቆይታለች። 

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በረሃብ ስትጠቃ ይህ ወንዝ የግብፅን ምድረ በዳ እያረስረሰ በግብርና ምርቶች ካይሮን አጥግቦ፣ የባህረ ሰላጤውን አገሮች በግብርና ምርቶች ብቻ ሳይሆን በኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ብዙ ገቢ እንድታገኝ አድርጓታል።

ዘመናዊው የግብፅ አስተዳደር የሚጀምረው እ.ኤ.አ. ከ1805 እስከ 1882 በቱርክ ቫይስሮይ መሐሙድ ዓሊ ዘመን መሆኑ ይነገራል:: በወቅቱ ግብፅ የኦቶማን ቱርክ ኤምፓየር አንድ ጠቅላይ ግዛት ነበረች:: እ.ኤ.አ. በ1882 ብሪታኒያ ግብፅን በመቆጣጠር ለአርባ ዓመታት በቅኝ ግዛት አገርነት አስተዳድራታለች:: አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ1922 ነፃ ወጥታ በንጉሣዊ አስተዳደር መተዳደር ብትጀምርም፣ የብሪታኒያ ወታደራዊ ኃይል ቁጥጥር ስር መሆኗ የተሟላ ነፃነት እንዳይኖራት አድርጓል::

ናይል ዴልታና ካይሮ አካባቢዎችን በመቆጣጠር የራሷን አስተዳደር መስርታ ነበር:: እ.ኤ.አ. በ1798 ዓ.ም. ፈረንሣይ ከብሪታኒያ ጋር ጦርነት ላይ ነበረች:: ናፖሊዮን ቦናፓርት መጠነ ሰፊ ጦርነትን በማካሄድ በቀጣናው የብሪታኒያን ንግድ ለማስተጓገል ጥረት አድርጎ ነበር:: 

የናፖሊዮን ጦር በላይኛው ግብፅ በመምሉኮችና በቱርኮች ከፍተኛ መከላከል ገጥሞት የነበረ ሲሆ፣ ፤በ1799 በአሌክሳንደሪያ አቅራቢያ መልህቁን የጣለውን የፈረንሣይ ባህር ኃይል በብሪታኒያ ባህር ኃይል ውድመት ደረሰበት::

 ናፖሊዮን ጦሩን ትቶ ለመሸሽ ተገደደ:: የፈረንሣይ ጦር ከሁለት ዓመት በኋላ ግብፅን ለቆ ሲወጣ የፈረንሣይ አገዛዝ አበቃ:: ፈረንሣይ ግብፅን ለቃ ስትወጣ የሥልጣን ክፍተት ተፈጠረ:: ማሙሉኮችም ሆኑ ኡለማዎች፣ እንዲሁም ነጋዴዎች ሥልጣኑን መያዝ አልቻሉም:: የኦቶማን ኤምፓየር የጦር መኮንን መሐመድ ዓሊ በግብፅ ነጋዴዎች በመደገፍ የአገሪቱ መሪነቱን ተቆጣጠረ::

መሐመድ ዓሊና አልጋ ወራሾቹ የመጀመሪያ ዕርምጃዎቻቸው የግብፅ ኢኮኖሚን ማዘመን ነበር:: አዳዲስ የውኃ ቦዮች፣ ወንዝ መገደቢያ ግንባታዎችና ፋብሪካዎች እንዲሠሩ አዘዙ:: 

በወቅቱ ግብፅ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ በብዛት ለመገንባት አልሞከረችም:: ምክንያቱም ከውጭ አምራቾች ጋር ለመወዳደር ገና ነበረች:: ሆኖም ግብርናዋን ለማዘመን ነበር ቅድሚያ የሰጠችው:: አዳዲስ የመስኖ ዘዴዎች በመጠቀም በፊት አንድ ጊዜ ብቻ የነበረውን የሰብል ምርት በዓመት ሦስቴ እንዲሆን አድርጓል:: እ.ኤ.አ. በ1952 የተወሰኑ ወታደራዊ መኮንኖች በጋማል አብደል ናስር መሪነት ንጉሣዊ አገዛዝን በመፈንቅለ መንግሥት በመጣል ግብፅ ሪፐብሊክ አገር መሆኗን አወጁ::

የግብፅ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱና የሚታረስ መሬት እጥረት በመኖሩ አገሪቱ ሕዝቧን መመገብ አልቻለችም:: አገሪቱ በዓባይ ወንዝ ጎርፍ መጥለቅለቅና ወንዙ ይዞት በሚመጣው ደለል መቸገራቸው መፍትሔ ማፈላለግ ነበረባት:: የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሮበርት ኦ ኮሊን የግብፅ ሕዝብ “ናይል ግብፅ ነው፣ ግብፅ ናይል ነው” (Nile is Egypt, Egypt is Nile) የሚለው ያለ ምክያንት አይደለም ይሉናል:: በግብፅ ሥነ ጽሑፍ፣ አፈታሪክ፣ ሥነ ቃልና ሙዚቃ ዓባይ ጭብጥ ሆኖ ቢዘልቅም ለዘመናት ግብፅን አቋርጦ ሜዲትራኒያን ባህር ይገባ ነበር::

በ1952 የግብፅ አብዮት በጋማል አብደል ናስር መሪነት ወደ ሥልጣን የመጣው የነፃ ወታደራዊ መኮንኖች ምክር ቤት መጀመሪያው ኢኮኖሚ ማሻሻያና ግዙፍ ዕርምጃው ታላቁ የአስዋን ግድብ እንዲነባ መወሰኑ ነበር:: በዓባይ ወንዝ የምግብ ሰብሎችን ጨምሮ ‹‹ካሸ ክሮፕ›› በመባል ገቢ የሚያስገኙ እንደ ትንባሆ፣ ጥራጥሬዎችና ረዥሙን ጥጥ (በዓለም ምርጥ የሚባለውን ዓይነት) ማምረት ጀመረች:: 

የግብርና ምርቶችን በ30 በመቶ የጨመረበት፣ የኤሌትሪክ ኃይሏ በስምንት እጥፍ ያደገበት፣ ከራሷ አልፋ የኤሌትሪክ ኃይል ለጎረቤቶቿ እንድትሸጥ የረዳት፣ ራሷን ከመመገብ አልፋ ወደ ውጭ የተትረፈረፈ የምግብ ምርቶችን ወደ ተለያዩ አገሮች የምትልክበት፣ በዓመት አሥር ቢሊየን ኪሎ ዋት በሰዓት ኃይል የምታመነጭበት፣ ግንባታው አሥር ዓመታት ፈጅቶ የተገነባ ግን በሦስት ዓመታት ብቻ ግድቡን ሞልታ ታላቅ ሐይቅ የፈጠረች አገር፣ በዓለማችን ምርጡን ጥጥ አምርታ ወደ ውጭ በመላክ የከበረችበት፣ ብዙ የሚባልለት ታላቁ የአስዋን ግድብ መገንባቷ ሁሉን ነገር ቀየረ።

በግብፅ አፈ ታሪክና ጥንታዊ ታሪክ ወስጥ በጎርፍ መጥለቅለቅና የድርቅ፣ እንዲሁም የሰቆቃ ተረኮች የተለመዱ ነበሩ:: በአርሶ አደሮቹ አነስተኛ ክትሮች፣ የውኃ መከላከያ የጭቃ ግንቦችና የጎርፍ መቀየሻ አጥሮች በመገንባት የመስኖ እርሻዎችን በማልማት ይታወቃሉ:: 

ለግብፅ ለዘመናት ሲፈስ የቆየው የዓባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ይዞላት የሚሄደው ውኃ ብቻ ሳይሆን ለም አፈርም ነው:: በዓለም ላይ በለምነቱ የላቀ አፈር ለእርሻ ምርቷ መጨመር ከፍተኛ ዕገዛ አደርጎላታል:: ዓባይ ይዞ በሚሄደው ደለል አፈር ግብፅ በዓመት ሦስት ጊዜ የሰብል ምርት እንድታመርት ያደርጋል::

እ.ኤ.አ. ከ1517 ጀምሮ ግብፅ በኦቶማን ቱርክ ስትተዳደር ቆይታለች:: እ.ኤ.አ. በ1805 የግብፅ መሥራች አባት ናቸው ሚባሉት ታላቁ መሐመድ ዓሊ የቱርክ አገረ ገዥ ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ፣ በግብፅ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻዎች ይዘው ብቅ አሉ:: ፈረንሣውያን አማካሪዎቻቸው የጥጥ እርሻ እንዲያስፋፉና ምርቱን ወደ አውሮፓ እንዲሸጡ አማከሯቸው:: 

አዲሱ የግብርና ምርት በቂ ውኃ ያስፈልገው ነበር:: ይህንን ለማድረግ በተለምዶ ግልገል አስዋን ግድብ (Aswan Low Dam or Old Aswan Dam) በደቡባዊ ምሥራቅ ካይሮ ጫፍ በዓባይ ወንዝ ላይ እ.ኤ.አ. በ1899 እና በ1902 እንዲገነባ አድርገዋል:: 

የግብፅ ጥጥ ምርት ተጠቃሚዋ ብሪታኒያ የመጀመሪያውን ግልገል ግድብ እ.ኤ.አ. በ1898 መገንባት ጀምራ እ.ኤ..አ. ኅዳር 10 ቀን 1902 ነበር ያጠናቀቀችው:: በወቅቱ በዓለም ትልቁ ግድብ እስከ መባል ደርሷል::ዕይህ ግልገል አስዋን ግድብ በሁለት ምእራፍ እንዲሻሻል ተደርጓል:: ግብፅ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪዎቹ በመሐመድ ዓሊ የአገዛዝ ዘመን ጥጥ ከሚያመርቱ አምስት የዓለማችን አገሮች አንዷ ለመሆን በቅታለች::

የግብፅ ጥጥ እርሻዎች የዓባይ ወንዝን ተከትለው መስፋፋት የአውሮፓውያንን ትኩረት መሳቡ አልቀረም:: የአሪቱን የጥጥ ምርቶች በበላይነት የተቆጣጠሩት መሐመድ ዓሊ፣ በናይል ሸለቆ የጥጥ እርሻዎችን አስፋፉ:: መሐመድ ዓሊ በየዓመቱ በቁርጥ ዋጋ በመሸጥ ወደ ግብፅ ካፒታል እንዲፈስ አደርገዋል:: 

በዚህ አንድ የግብርና ምርት ብቻ የአውሮፓ ገበያን መቆጣጠሯ ዛሬም ቢሆን ለብዙዎች አስገራሚ ነው:: አንድ ሸቀጥ ብቻ ተደርጎ የሚወሰድ ሳይሆን የጥጥ ምርቱን ለመቆጣጠር እንግሊዝና ፈረንሣይ፣ እንዲሁም ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ግብፅን የቅኝ ግዛታቸው ለማድረግ አንዳነሳሳቸው ይነገራል፡፡ ዓባይ ከኢትዮጵያ ውኃና ለም አፈር በረሃማዋ ግብፅ ድረስ ያጓጉዛል:: 

አርሶ አደሮቿ የዘሩት ጥጥ የአውሮፓ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪዎች ዋነኛ ግብዓት ምንጭ ሆነ፡፡ ለግብፅ የፈለገችውን እንድትበደር ያደረገ ኃይለኛ የገንዘብ ምንጭ ፈጠረላት፡፡ የጥጥ እርሻዎቿ ለካይሮ የብድር ሥርዓት አምጥተውላታል::

ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ ብቻ ሳይሆን ለም አፈርና ምርጥ የጥጥ ዝርያ ለግብፅ ሰጥታለች፡፡ የአውሮፓ ባንኮች በሚያማልል ወለድ ብድር እንድትወስድ ያግባቧትም ነበር:: ከገንዘቡ ትርፍ ይልቅ ግብፅን የሚያዘምኑ ኢንዱስትሪዎች ለመገንባት ገንዘብ እንድትበደራቸው ይገፋፏት ነበር:: በአውሮፓውኑ ባንኮች ግብፅ ዕዳ ወስጥ ገብታ የነበረ ቢሆንም፣ ከጥጥ ምርቷ ባገኘችው ገቢ መሸፈን ችላለች:: 

አሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት እ.ኤ.አ. በ1861 መቀስቀሱን ተከትሎ የግብፅ ጥጥ ምርት ለተወሰኑ ጊዜያት በአስገራሚ ሁኔታ አደገ፡፡ እ.ኤ.አ በ1862 ወደ ወጭ ከላከችው የጥጥ ምርት 16 ሚሊየን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1854 ወደ 56 ሚሊየን ዶላር ማገኘቷን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በወቅቱ ግብፅን ይመሩ የነበሩት የመሐመድ ዓሊ የልጅ ልጅ ኢስማኤል ፓሻ ፈረንሳይ የተማሩና አውሮፓን በመዘዋወር ልምድ የቀሰሙ ነበሩ፡፡ 

የፈረንሣይ ተፎካካሪ አፍሪካዊት አገር ለመገንባት የሚያልሙት ኢስማኤል ፓሻ “ፓሪስን በዓባይ” ላይ ለመገንባት ብዙ ለፍተዋል፡፡ በዓባይ ዙሪያ የተስፋፉትን የጥጥ እርሻዎች ገቢ በመጠቀም፣ በግብፃውያን ገንዘብና ደም ስዊዝ ቦይ እንዲገነባ ማድረጋቸው ይጠቀሳል::

የአስዋን አነስኛ ግድብ የሚያጠራቅመው የአንድ ዓመት ውኃ ብቻ ነበር፡፡ የሚይዘው የውኃ መጠን ብዙ አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ በ1912 ትውልደ ግሪክና ግብፅ ማሃዲሱ አድሪያና ዳንኒዮስ አዲስ የአስዋን ግድብ ግብፅ ወስጥ ለመገንባት ያቀረበው ውጥን ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1946 አነስተኛው (ግልገል) አስዋን ግድብ ዓባይ ወንዝ መሞላት ቢጀምርም የዳንኒዮስ ዕቅድ ንጉሥ ፋሩቅን ብዙም አልሳባቸውም፡፡ 

የትነት መጠኑ አነስተኛ በሚሆንባቸው ሱዳንና ግብፅ የዓባይን ወንዝ ውኃ ለማጠራቀም ሐሳቡ ይደገፍ ነበር:: የግብፅ ንጉሣዊ አገዛዝ መገርሰሱን ተከትሎ ጋማል አብደል ናስርን ጨምሮ የነፃ መኮንኖች ንቅናቄ (Free Officers Movement) መሪዎች ወደ ሥልጣን በመምጣታቸው፣ የግብፅ አቋም ሙሉ ለሙሉ ተለወጠ:: በዳንኒዮስ ዕቅድ መሠረት የነፃ ወታደራዊ መኮንኖች ንቅናቄ መሪዎች በፖለቲካ ምክንያቶች ሳቢያ የዓባይ ውኃ በግብፅ ውስጥ እንዲጠራቀም በመወሰናቸው፣ በሁለት ወራት የዳንኒዮስን ዕቅድ ተቀበሉት:: 

ይህም የታላቁ አስዋን ግድብ መገንባት ምክንያት ሆነ:: በዚህ ግዙፍ የዓባይ ወንዝ ግንባታ ላይ ሁለት ጉዳዮች ማንሳት ይጠቅማል።

  1. የሱዳን ታላቁ የመረዌ ግድብ

የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር የመጨረሻ ደማቅ ዳንስ የደነሱት እ.ኤ.አ. በ2009 ነበር፡፡ በሱዳን ሙዚቃ ከታጀበው ዳንሳቸው ጀርባ አንድ ትልቅ ግድብ ተጠናቆ እየተመረቀ ነበር፡፡ ሳይጠጡ በደስታ ያሰከራቸው በቻይናውያን ቀያሽነት፣ መሐንዲስነትና አበዳሪነት፣ እንዲሁም በዓረብ አገሮች ድጋፍ የተሠራው የመረዌ ግድብ ተጠናቆ እየተመረቀ ነበር፡፡ 

አል በሽር ዳንስና ከፊታቸው የሚታየው ፈገግታ በዚህ ግድብ አማካይነት ‹‹አዲዮስ የሱዳን ችግር እንጦሮጦስ ገባ…›› እያሉ ይመስል ነበር፡፡ ሱዳን የዳቦ ቅርጫት ሆና ከመካከለኛ የኑሮ ደረጃ በአንዴ እንደምትገባ እርግጠኛ የሆኑ ይመስል ነበር፡፡ ሱዳን ከአስዋን ግድብ ቀጥሎ በትልቅነቱ ሁለተኛ የሆነውን የመረዌ ግድብ በሰሜናዊ ካርቱም 350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2009 ሠርታ አጠናቀቀች፡፡

የመረዌ ግድብ ለኤሌክትሪክና ለአዲስ የመስኖ እርሻ ታቅዶ የተገነባ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ግብፅ በሱዳን የመረዌ ግድብ አሞላልና አስተዳደር ላይ ምንም ያነሳችው ውዝግብ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ ይኼ ግድብ እየተሠራ ቢሆንም ምን እየተደረገ እንደነበር የምታውቅም አትመስልም ነበር፡፡

 የመረዌ ግድብ ርዝመት 9.2 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ 1250 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ነበር የተሠራው፡፡ አሁንም ቢሆን ከግብፅ ታላቁ አስዋን ግድብ ቀጥሎ በግዝፈቱ ሁለተኛ ነው፡፡ ይህ ግድብ የሚይዘው ውኃ 174 ኪሎ ሜትር ድረስ የተዘረጋ ነው፡፡ 

ከቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ብድርና ከዓረብ አገሮች በተገኘ 2.4 ቢሊዮን ዶላር ወጥቶበታል፡፡ የተገነባው በቻይና፣ በጀርመንና በፈረንሣይ ኩባንያዎች ነው፡፡

ግድቡ ሲገነባ ከ50 ሺሕ በላይ ሱዳናውያን ለም ከሆነው የዓባይ ሸለቆ ተፈናቅለው በረሃ ላይ እንዲሠፍሩ ተደርገዋል የሚል ክስ ይቀርብበታል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ መብት ተቋም ሳይቀር እ.ኤ.አ. በ2007 ግንባታው እንዲቆም ሪፖርት አቅርቦበት ነበር፡፡ 

ፊት ለፊት ባይሆንም ግብፅም አቧራ አስነስታበታለች፡፡ ግን እንደ ኢትዮጵያ በግልጽ ጠንካራ ሙግት አላነሳችበትም፡፡

  1. ቶሽካ ፕሮጀክት የሰሃራ በረሃ የልማት ውጥን

የቀድሞው የግብፅ መሪ ሆስኒ ሙባረክ እ.ኤ.አ በ1997 “New Nile Valley Project” (የአዲሱ የናይል ሸለቆ ፕሮጀክት) በማለት ግዙፍ የሆነውን የሰሃራ በረሃን የማልማት ዕቅድ ነድፈው ነበር። ሙባረክ ለዕቅዱ ተግባራዊነት መንቅሳቅስ ጀምረው ነበር፡፡ 

ይህ ፕሮጀክት በዋናነት ሁለት ምዕራፎች ሲኖሩት አንደኛው በሰሜን ምሥራቅ ግብፅ የሚገኘው የአል ሰላም ቦይ (ካናል) ፕሮጀክት ነው፡፡ እሱም ውኃ ከዓባይ ግርጌ በመጥለፍ ወደ ሲና በረሃ ማሻገር ነው፡፡ ይህን በማድረግ ብዙ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት በማልማት 750 ሺሕ ግብፃውያንን ለማስፈር ያለመ ነው፡፡ ዋናውና ትልቁ ፕሮጀክት ግን የቶሽካ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ይህም የደቡብ ምዕራብ ግብፅ በረሃን ለማልማት ያቀደ ፕሮጀክት ነው፡፡ 

በግብፃውያኑ ዘንድ ይህ ፕሮጀክት አሁን ባለው ሁኔታ እ.ኤ.አ. 2020 ያልቃል ተብሎ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ በዋናነት አዲስ ግብፅ በበረሃው ለመፍጠር ያቀደ ሲሆን፣ የተለያዩ በርካታ የውኃ ቦዮችንና የውኃ መምጠጫ ፓምፖዎችን በመገንባት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ይህን በማደረግ በረሃውን በማልማት ወደ ሦስት ሚሊዮን ግብፃውያንን የማስፈር ዕቅድ አላቸው፡፡ እንደ ግብፃውያኑ ከሆነ ይህ ፕሮጀክት ውኃውን የሚያገኘው በናይል ላይ ከተሠራው የአስዋን ግድብ ጀርባ ከሚገኘው የናስር ሐይቅ ነው፡፡ 

ግብፃውያኑ ይህን ሥራ የትኞቹንም የላይኛውን የተፋሰስ አገሮች ሳያናግሩ ሲሠሩት ውኃውን ከየት እንደሚያመጡት ያውቃሉ፡፡ እነሱ እ.ኤ.አ. በ1959 ከሱዳን ጋር የተፈራረሙት በሌሎቹ አገሮች ውድቅ የተደረገው የቅኝ ግዛት ውሎች መሠረት አብዛኛውን የውኃ ድርሻ መድበው ጨርሰዋል።

እ.ኤ.አ. በ2005 መጋቢት ወር የፕሮጀክቱ ዕምብርት የሆነው የሙባረክ ውኃ ማሰራጫ ጣቢያ በይፋ ተመርቋል። የሙባረክ ውኃ መግፊያ ጣቢያ የዓባይን ውኃ ከናስር ሐይቅ ውስጥ ለውስጥ የሚገፋ ግዙፍ ማሰራቻ ነው። ከናስር ሐይቅ በስተስሜን 310 ኪሎ ሜትር የሚደርሰው ቦዩ እ.ኤ.አ. እስከ 2012 ድረስ 60 ኪሎ ሜትር ተሠርቶ ነበር።

 በዚህ ፕሮጅክት ውኃውን 2340 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሽፍን ሲሆን፣ የዓባይን ሸለቆ በረሃ ወደ ምድረ ገነት የእርሻ መሬት የመለወጥ ዓላማ አለው። የቶሽካ ፕሮጀክት በፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ አማካይነት ዳግም እንዲያንሰራራ እየተደረገ ነው። ግማሽ የሚሆነው መሬት ለኮሌጅ ተመራቂዎች

የሚሰጥ ሲሆን፣ ለእያንዳንዳቸው 4046.86 ካሬ ሜትር በመስጠት ‹‹ግብፅ ለዘለዓለም ትኑር ፈንድ›› ከሚባል ተቋም የገንዘብ ድጋፍ ምድረ በዳውን እንዲያለሙ ውጥን አለ።

የግብፅ ቶሽካ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 9 ቀን 1997 በቀድሞ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በተገኙበት መጀመሩ ተበሰረ፡፡ 

በፕሮጀክቱ ተመጋጋቢ ቦዮችን (ካናሎች) ከናስር ሐይቅ ወደ ግብፅ በረሃማ ሥፍራዎች ለመስኖ እርሻዎች የሚሆን ውኃ የሚያሻግር የመግፊያ ጣቢያ ተሠርቶለት ተጠናቋል። እ.ኤ.አ. በ2020 ወደ ሦስት ሚሊዮን ነዋሪዎችን ማሥፈር የሚያስችል ሆኖ፣ የግብፅን የሚታረስ መሬት አሥር በመቶ የሚያሳድግ ግዙፍ የዓለማችን የውኃና የመስኖ ፕሮጀክት ነው:: 

ከግብፅ ሕዝብ 20 በመቶ የሚሆኑ ሰዎችን ማሥፈር የሚያስችል ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህም ከ20 ሚሊዮን በላይ  ሰዎች በሰሃራ በረሃ በዘመናዊ ግብርና እንዲተዳደሩ፣ ብሎም ሌላ ካይሮን የምታህል ከተማ ለመገንባት ውጥን የተያዘበት ነው።

በቶሽካ ፕሮጀክት የመጀመሪ ምዕራፍ የሙባረክ የውኃ መግፊያና ማሠራጫ ጣቢያ እ.ኤ.አ. በ2005 በ436 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው ተጠናቋል:: በአንድ ጊዜ 18 የውኃ መግፊያ መስመሮች የሚሠሩ ሲሆን፣ ሦስቱ ለጥገና ፍላጎት ሌሎች ሶስት ደግሞ እንደ መጠባባቂያ የሚያገለግሉ ናቸው::

 የውኃ ማሠራጫ ጣቢያው 50 ሜትር በመሬት ጥልቅ ውኃ መግቢያ ቦይ የተፈጠረለት ነው፡፡ በሰዓት 1.2 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ይገፋል ፡፡ የካናሉ ውኃ ማስተላለፊያ ቱቦ 30 ሜትር ስፋት አለው:: የውኃ ማሠራጫና ማስተላለፊያ ካናሉ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መሪ ሼክ ዚያድ አል ናህያን ስም ተሰይሟል:: 

ቶሽካ ፕሮጀክት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራ በመሆኑ ነው በስማቸው የተሰየመው:: ከዚህ ግዙፍ የውኃ ማሠራጫ ጣቢያ የሚጀምሩና መሬት ለመሬት የተቀበሩ 24 የአግድሞሽ ውኃ መግፊያና ማሠራጫ ቱቦዎች በዋና ማከፋፈያ ጣቢያው ዳርና ዳር በሁለት ረድፍ ትይዩ ተሠርተው ተጠናቀዋል:: የውኃ ጫና መቆጣጠሪያና የፍጥነት ማስተካካያ ሥርዓትም ተበጅቶላቸዋል፡፡

የሙባረክ የውኃ መግፊያ (ማሠራጫ) ጣቢያ እ.ኤ.አ. በ2005 ሲጠናቀቅ በሲቪልና በሜካኒካል ምህንድስና ስኬቶቹ የተወደሰ ነው:: ሙሌቱ በብረት የተዋቀረ ሲሆን፣ የመሬት ርዕደትን መቋቋም እንዲችል ተደርጎ የተሠራ ነው:: 

ሆስኒ ሙባረክ እ.ኤ.አ. በ2011 በፀደይ አብዮት ከሥልጣን በመወገዳቸው የቶሽካ ፕሮጀክት ሒደትን እንደገታው ይነገራል፡፡ በአገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ ፕሮጀክቱ መቀዛቀዙ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

በቀጭን ክር ቶሽካንና ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ሼክ መሐመድ አል አሙዲን ማያያዝ ይቻላል። ‹‹ሳዑዲ ስታር አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመን›› ኩባንያ ባለቤት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሳዑዲ ዜጋ ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ናቸው፡፡ 

ኩባንያው በምዕራብ ጋምቤላ ወደ 10,000 ሔክታር መሬት የሚሸፍን እርሻ አለው። ይህ ኩባንያ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ያፈስበታል ተብሎ ነበር። ይህ ፕሮጀክት ዋና ምርቱ ሩዝ ሲሆን፣ በዋናነትም ለውጭ ገበያ የሚቀርብ እንደሆነ ይነገራል፡፡ 

ሳዑዲ ስታር የተባለው የሼክ አል አሙዲ ኩባንያም ምርቱን በዋናነት ለሳዑዲ ዓረቢያ ሊያቀርብ የታሰበ ነበር፡፡ ባለሀብቱም ከሳዑዲ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ጋር ባላቸው መቀራረብ ተነጋግረው የተጀመረ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ ይነገራል። ይህ የሚያሳየን ሳዑዲ ዓረቢያ በአንድም በሌላም ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የራሷ የሆነ የጥቅም ፍላጎት እንዳላት ነው፡፡ 

ጋምቤላ ውስጥ ያሉ ወንዞች የዓባይ ገባር መሆናቸውን ይታወቃል፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ ሚና በዚህ ፕሮጀክት ላይ ምንድነው ስንል ታላቅ ኢንቨስትመንትን እናገኛለን፡፡ የሳዑዲው ልዑል አል ዋሊድ ቢን ጣላል ቢን አብዱላዚዝ አል ሳዑድ ‹‹ዘ ኪንግደም አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት›› የተሰኘ ኩባንያ ባለቤት ሲሆኑ፣ ግብፅ ውስጥ በጥቅሉ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያንቀሳቅሳሉ፡፡

 በቶሽካ ፕሮጀክት ደግሞ ከአሥር ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ተረክበው የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለማምረት፣ ከግብፅ የውኃና የመስኖ ልማት ሚኒስቴር ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በየዓመቱም በሚሊዮኖች ለዚሁ የቶሽካ ፕሮጀክት አካል ለሆነው መሬት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈሱ ይነገራል፡፡

የቶሽካ ፕሮጀክት ሐሳብ አዲስ አይደለም፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጋማል አብደል ናስር በታላቁ የናስር ግድብ ጀምረውት፣ ግን እ.ኤ.አ. በ1964 የተቋረጠው ግዙፍ ዕቅድ አካል መሆኑ ይነገራል፡፡ የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦስቲን የዶክትሬት ተማሪዋ ኢማ በግብፅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ባካሄደችው ጥናት የቶሽካ ፕሮጀክት በጀት ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝብ የተሰወረ መሆኑን ጠቅሳለች፡፡ 

ከግብፅ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያም የተሰወረ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ደጋፊዎቻቸው የቀድሞ ፕሬዚዳንት የጋማል አብደል ናስርን ፎቶግራፍ ይዘው በመውጣት ነበር ስለመጪው መሪ አተያይ ለማንፀባረቅ የሞከሩት፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ግድያ መቃጣቱን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በተለይ አዲስ አበባ በሚካሄድ ጊዜ ለብዙ ዓመታት መምጣት በመተዋቸው፣ ኢትዮጵያ ሌሎች የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን እንድታስተባብር ዕድል አግኝታ ነበር፡፡

ይህ የገባቸው አልሲሲ ግብፅን ወደ የአፍሪካ ኅብረት መልሰው የወቅቱን ሊቀመንበርነት ከሩዋንዳ እንድትረከብ አደረጉ፡፡ እሳቸው በምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡትን መሐመድ ሙርሲን መፈንቅለ መንግሥት በሚባል ዓይነት ከሥልጣን ቢያስወግዱም፣ የአፍሪካ ኅብረት ከማጉረምረም ያለፈ ምንም አላደረጋቸውም፡፡ ቶሽካ የግብፅ ባለሥልጣናት ‹‹የፒራሚዶችን ግንባታ በ20 እጥፍ የሚያስከነዳ›› ግዙፍ የካይሮ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ይናገራሉ። አዲሱን የዓባይ ሸለቆ ሥልጣኔ እንደሚያመጣም

ተነግሮለታል። ከአየር ላይ ወደ ታች ለሚመለከት ግዝፈቱ የዘመናችንን የግንባታ ተዓምር ብቻ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ የግብፅን የዓባይ ውኃ የመቆጣጠር ታላቅ ህልም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ግብፅ በቅርቡ አዲስ ነገር ይዛ መጥታለች ብሎ የተደነቀው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የአገሩን አቋም ማስረዳቱ ብቻ በቂ አይሆንም። 

የግብፅን ታላቁ የአስዋን ግድብ መጎብኘት ወይም መፈተሽ፣ ከዚያ ግዙፍ ግድብ ጋር ተያይዞ ወደ ዓለማችን ታላቁ ሞቃታማና ምድረ በዳ በረሃ ውስጥ ለውስጥ የተሠራውን በጥርብ ድንጋይና በኮንክሪት ሲሚንቶ የተገነባውን ረዥሙንና ሽንጣሙን ቅንጡ የቶሽካ ፕሮጀክት ይመለከተኛል ብሎ መነሳት ያስፈልጋል። 

ግብፅ ከዓባይ ወንዝ ድርሻ አብዝታ መጠየቋን እንዳለ መቀበል አያስፈልግም። የኢትዮጵያን ፕሮጀክቶች ያገባኛል ብላ የምትሞግተውን ያህል፣ ሌሎችን ደብቃ ውኃውን የምታሾርባቸውን ፕሮጀክቶች መመርመር ይጠይቃል።

በሰሞኑ ቀውስ ‹‹የካይሮ እጅ እንዳለበት›› የመንግሥት ባለሥልጣናት በገደምዳሜ ሲናገሩ የሰማን መሰለኝ። መንግሥት በምርመራው ከግምት በላይ ለዚህ መረጃ ካለው፣ በግልጽ በድርድሩ ወቅት አቋሙን ማሳወቅ ይኖርበታል። ይህንን ጥርጣሬውን መንግሥት ለካይሮ ይፋ አድርጎ መሰል ሕገወጥ እንቅስቃሴ በግልጽም ሆነ በይፋ ድጋፏን የሚጠቁሙ ጉዳዮች ካሉ፣ አብሮ ተባብሮ ለመሥራት እንደማይቻል ማሳወቅ ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ። 

ከድርድር በኋላ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚሰጡዋቸው መግለጫዎች በአንድ የጋራ ጉዳይ እየተደራደሩ ሳይሆን፣ የጦር ጄኔራሎች ከጦርነት በኋላ ቀዝቃዛ ጦርነትን አስመልክተው መግለጫ የሚሰጡ ይመስላል። ይህ ደግሞ በድርድሩ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ በመሆኑ ግብፅ ልታውቀው ይገባል።

በቅርቡ የግብፅ ተደራዳሪዎች ስለሌላ ግድብ ጉዳይ የማንሳታቸው ወሬ ሲነገር ነበር። ኢትዮጵያ 90 በመቶ እየተስማማን ነው የሚል የዋህ መግለጫ አይጠቅማትም። የቀረው አሥር በመቶ ውስጥ ሰይጣኑ አለ። አብዛኛውን እንደተስማሙበት የሚነገረው እንዲህ የሚያኩራራ አይደለም። 

በየጊዜው ተለዋዋጭና አዲስ አጀንዳ እያመጣች ድርድሩ እንዲቋረጥ ከምታደረግ አገር ጋር፣ ‹‹አብዛኛው ጉዳይ ላይ ስምምነት››”ተደርሷል ብሎ ‹‹ስለድል›› መናገር ይከብዳል። አደራዳሪው የአፍሪካ ኅብረት መሆኑ አያስፈነድቅም፡፡ ምክንያቱም ተደራዳሪዋ ግብፅ ነች። ኢትዮጵያ የምትጠቀመው ከአደራዳሪዎቹ አፍሪካዊነት  ወይም አሜሪካዊ  ማንነት ሳይሆን ከእውነታው ላይ መሆን አለበት።

ከግብጽ ጋር 99 በመቶ መግባባት ወይም መስማማት እንኳን ቢኖር እንደ ዲፕሎማሲያዊ ድል መውሰድ አይገባም። አንድ በመቶ የሚሆነው አንቀጽ በጥንቃቄ ካልታየ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ቀፍድዶ ዘውትር መነታረኪያ አጀንዳ ሊፈጥር ይችላል። 

ኢትዮጵያ ሳትፈርም እንኳን ሱዳን ‹‹ውኃ ቀነሰብኝ›› ዓይነት ክስ ማንሳቷ ወደፊት የተፈራረሙበትን አንቀጽ እየመዘዙ መነታረኩ እንደሚኖር ይጠቁማል። ታላቁ የአስዋን ግድብና የቶሽካ ፕሮጀክት ምን ያህል የዓባይ ውኃ ይበቃቸዋል?  ኢትዮጵያ ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ አያያዝ ከመነጋገር ጎን ለጎን ግብፅና ሱዳን ውኃውን እንዴት እየተጠቀሙበትና እያድፋፉት እንደሆነ፣ የእነሱን ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች በአግባቡ ማወቅ ይጠቅማል። 

ያም ሆነ ይህ የሦስቱ አገሮች ድርድር ስምምነት ተደርሷል በሚል የሚደረግ የፊርማ ማሳረጊያ የዓባይ ወንዝን ንትርክ በዘላቂነት ይፈታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ግብፅ ሰነዱን መፈረም የምትፈልገው በተለሳለሰ ቋንቋ የተጀቦነ የቅኝ ግዛቱን ውል ዘመናዊዋ ኢትዮጵያ እንድትቀበል ግፊት በመፍጠር ይሆናል። 

ልክ እንደ ሱዳን ‹‹ውኃው ቀነሰ ….›› እያሉ ከግድቡ ይለቀቅ በሚል ተፅዕኖ በማሳደር የማያቋርጥ ንዝንዛቸውን  ሊፈጥር እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

     – Eskindr kebede

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top