በባለሃብቱ ፍልስፍና ቀናኹ!
(እሱባለው ካሳ)
የባለሃብቱ የአቶ በላይነህ ክንዴ ፍልስፍና አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሳነብ ተደምሜአለሁ፡፡ “ኢትዮጵያ ቢዝነስ ከመስራትም በላይ ለወገን፣ ለሀገር አስበው የሚሰሩ ባለሃብቶችም አሏት ወይ?” የሚያሰኝ የመደነቅ ስሜት ተስምቶኛል፡፡
ያስደነቀኝ ንግግራቸው የትኛው ነው?
ልብ በል፤ የብዙ ባለሃብቶች ምኞትና ፍላጎት ምንድነው? እንደምንም ተጋግጦ አዲስበባ ውስጥ ኪስ ቦታ ማግኘትም አይደል? በተገኘ ኪስ ቦታ ሳጥን መሰል ሕንጻ ገትሮ ቁጭ ብሎ ገንዘብ መሰብሰብም አይደል?
እሳቸው እቴ!..እንዲህ አይነቱ ስራ ያጥወለወላቸው ናቸው፡፡ ጥሮ ግሮ፣ ፋብሪካ አቁሞ፣ አዲስ እሴት ፈጥሮ፣ ስራ የሌላቸው ብዙዎችን ቀጥሮ ሀብት ማግኘትን የሚሹ ናቸው፡፡ እናም እስከዛሬ አዲስአበባ ውስጥ የእኔ የሚሉት ሕንጻ አልገነቡም፡፡ ኢትዮጵያ ሆቴልንም እጃቸው የገባው ያው በገጠመኝ ነው፤ የመግዛት እድሉን ስላገኙ ገዝተውት እንጂ፡፡
በአንደበታቸው “አንድ ፎቅ ብሰራ የሥራ ዕድል የምፈጥረው ለሁለት ሰው ነው፤ ለዚህ መሰል ነገር ዕድል አልሰጥም” ይላሉ፡፡
ምን ማለታቸው ነው? የሚል ጥያቄን ሳታስከትል ወደቡሬ ይዥህ ልብረር፡፡
ሰውየው አንቱ የተባለለት የምግብ ዘይት ፋብሪካ ቡሬ ላይ መገንባታቸውን መቼም ሰምተሃል፡፡ በአማራ ክልል በቡሬ ከተማ በኢትዮጵያዊ ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ የተገነባውና ሰሞኑን በይፋ እንደሚመረቅ የተነገረለት የምግብ ዘይት ፋብሪካ፤ የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን እስከ 60 በመቶ ይሸፍናል ተብሎ ቅድመ ትንበያ ተነግሮለታል።
በዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም እንዳለውና አገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት እንደሚፈታም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የፊቤላ ኢንዳስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስር የሚገኘው ይኸው ፋብሪካ ማንኛውንም አይነት የቅባት እህሎችን እንደሚያጣራና በአሁኑ ወቅት ለአምስት መቶ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ወደ ምርት ሲገባ ቁጥሩ እስከ ሶስት ሺ ከፍ እንደሚል ታውቋል፡፡
ፋብሪካው በየዓመቱ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቅባት እህሎችን በግብዓትነት ስለሚጠቀም ለአርሶ አደሩ የገበያ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
አንዳንድ የሰበሰብኳቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አቶ በላይነህ ክንዴ በአንድ ወቅት በአመታዊ ገቢያቸው የፎርብስ አፍሪካ የደረጃ ሰንጠረዥ ተቆናጠዋል፡፡
ለተከታታይ 10 ዓመታት ባሳዩት የላቀ የስራ ውጤት የሰሊጡ ንጉስ የሚል ስያሜ ተጎናጽፈዋል፡፡
የ ቢኬ አስመጭና ላኪ (BKIEA) ባለቤትና CEO የሆኑት አቶ በላይነህ ክንዴ ከኢትዮጵያ አመታዊ ገቢ ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት ቀዳሚ መሆናቸውን ፎርብስ አፍሪካ በአንድ ወቅት አስነብቧል፡፡.
እንደ ፎርብስ መፅሔት፡ Belayneh Kindie Import And Export (BKIEA), ታላቅና ግዙፍ የሆነ በኢትዮጵያ ታላቁ የግብርና ምርት ውጤቶች ንግድ ድርጅት ነው።
ዋና ዋና ኢንቨስትመንቶቻቸው በ 5 የተለያዩ ክልሎች ይገኛሉ፡፡
– በትግራይ – ሁመራ ሰሊጥ አዘጋጅቶ መላኪያ፣
– ኦሮሚያ -ታጠቅ ላይ ቡና አዘጋጅቶ መላኪያ፣
– ገላን ላይ ሰሊጥ አዘጋጅቶ መላኪያ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ፣
– አዳማ- ሆቴል፣
– አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ ሆቴል (የቢኬ ካምፓኒ ዋና መስሪያ ቤት መገኛ)
– ደቡብ ቤንች ማጅ፣
– አማራ -ቡሬና ባህር ዳር፣
በተጨማሪም ቤንች ማጅ ዞን በ 2 ሺ 750 ሄክታር መሬት ላይ የእርሻ ልማት…(ቡና፣የኤክስፖርት እህሎችና ምርጥ ዘር) ይገኛል፡፡
ቢኬ ትራንስፖርቴሽን ከ 175 በላይ ተሳቢ መኪናዎችን በማሰማራት ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ የጭነት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ብዙ ግዙፍ ማሽነሪዎችን በማስመጣል አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በሆቴል ዘርፍ፡- በባህርዳር ከተማ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ ባለ 5 ኮከብ የሂልተን ሆቴልን እያስገነቡ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ከመንግስ በገዙት ሆቴል ፤አንደኛው አገልግሎት እየሰጠ ያለ ሲሆን ሁለተኛው ማስፋፊያ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ሆቴል የተለያዩ እድሳት በማድረግ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ሲሆን እዚሁ ቦታ ለወደፊቱ በ 2 ቢሊዮን ብር በአፍሪካ አንደኛ የሚሆን ሆቴል ለመገንባት አጠቃላይ ፕላኑ ተሰርቶ ተጠናቋል፡፡
ወዳጄ፤ ባለሃብቱ በላይነህ ክንዴ ፍልስፍና ገባኸም አይደል? በቃ ነግዶ ማትረፍ ለእሳቸው በቂ አይደለም፡፡ ለዜጎች ስራ መፍጠር፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠንካራ ድጋፍ ማድረግ የፍልስፍናቸው የስበት ማእከል ነው፡፡ ለብዙ ዜጎች ስራ መፍጠራቸው ትልቁ እርካታቸው ነው፡፡
ለጋስነትስ ብትል?!…ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 33 ሚሊዮን ብር አውጥተው ቦንድ የገዙ ሲሆን ለገበታ ለሀገር 35 ሚሊየን ብር በማውጣት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡
ታላቁን ባለሃብት እና የልማት አርበኛ ፈጣሪ ዕድሜና ጤና እንዲሰጥልኝ በመለመን ልሰናበት፡፡ (ማጣቀሻዎች፡- ኢፕድ፣ አብመድ…)