መውለድ የሞት መድኃኒቱ እንደሆነ ያስመሰከሩት የዶ/ር አምባቸው መኮንን ልጆች እና የዶ/ር አምባቸው ፋውንዴሽን ምሥረታ
(ሄኖክ ስዩም – ድሬቲዩብ)
ስራ አይሞትም፡፡ መልካም ስራ መልካም ስምን ከመቃብር በላይ ያኖራል፡፡ አበው የሞት መድኃኒቱ መውለድ ነው ይሉትን ብሂል ደርሰው አልፈጠሩትም፤ ኖረው ከህይወት ያዩት ነው፡፡ የዶክተር አምባቸው መኮንን ልጆች ይሄንን አስመስክረዋል፡፡
አባታችንን የበላች ሀገር ብለው አላኮረፉም፤ አባት የሌለን ልጆች ነን ብለው የግል ፍላጎታቸው ወላጅ ለመሆንም አልባተሉም፡፡ ራዕይን ሰንቀው የአባታቸውን ስም አስጠሩ፤ ባለቤታቸውና ልጆቻቸው በዚህ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ዶክተር አምባቸው ፋውንዴሽን ትናንት በይፋ መመስረቱን ሰማን፡፡ ደስ የሚል የምስራች ነው፡፡ ፋውንዴሽኑ የቀድሞ አማራ ክልል ፕሬዚዳንትና በተለያዩ የሥራ ሃላፊነቶች ላይ ሀገራቸውን ያገለገሉት ዶክተር አምባቸው ይመኙትና ለሀገራቸው ያስቡት የነበረው መልካም ምኞት እውን ይሆን ዘንድ የሚሰራ ነው፡፡
ሦስት አስርት ዓመታት ሀገራቸውን በማገልገል ምዕራፍ ከጽኑ አቋምና ትግል ጋር ስማቸውን ያጻፉት ዶክተር አምባቸው ለስማቸው መታሰቢያ ለእራያቸው ማሳኪያ ይሆን ዘንድ ሀገር የሚያቀራርብ መንፈስ ያለው ፋውንዴሽን ተመስርቷል፡፡
በፋውንዴሽኑ ምስረታ ላይ የዶክተር አምባቸው መኮንን የሥራ ባልደረቦች፣ የህይወት ዘመን ወዳጆች፣ ቤተሰቦችና ታማኙ ሰው ታማኝ በየነ በተገኙበት ይፋ ሆኗል፡፡ ጤና ትምህርትና አረንጓዴ ልማት የፋውንዴሽኑ ቀጣይ የእንቅስቃሴ መስኮች መሆናቸውንም ሰምተናል፡፡ የሦስቱ ችግሮቻችን ውጤት የመከራ ናዳ ላሸከመን ህዝቦች የፋውንዴሽኑ አስተዋጽኦ ቀላል አይሆንም፡፡
ዶክተር ክንዳለም ዘውዴ በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩት የዶክተር አምባቸው ፋውንዴሽን ይፋ የማድረግ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት አዳነች አበቤ በእንግድነት ተገኝተው የከተማ አስተዳደሩ ለፋውንዴሽኑ ዓላማዎች መሳካት ያለውን አጋርነት እንደገለጹና ስለ ለዶክተር አምባቸው መኮንን መልካም ምስክርነታቸው መስጠታቸውን ከመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ሰምቻለሁ፡፡
በዚህ ሀገር የቀድሞ መሪ እንኳን አልፎ ኖሮ ወደ ቀድሞ ህይወቱ ይመለሳል እንጂ ስለ ራዕዩ አስቦ ዳግም ሀገሩን ሊሰራ የሚችልበት እድል አልነበረም፡፡ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀኑትን ጎዳና ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ሄደውበት አሁን ዶክተር አምባቸው መኮንን ጋር ደርሷል፡፡
ህዝብን ለማገልገል የጓጓ መሻት በልጅና በቤተሰብ ሩቅ አሳቢነት እውን ሆኗል፡፡ እንዲህ ስለሆነ ዶክተር አምባቸውን ሞቷል ወይም አልፏል ማለት አይቻልም፡፡ ስሙ መልካም እየሰራ በመካከላችን ይኖራልና፤
ፎቶዎቹ እዚሁ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ከሰራው ዘገባ የተገኘ ነውና እጅ ነስቼ አጅቤበታለሁ፡፡