Connect with us

ማንነት ተኮሩ ጭፍጨፋ እና የዕርምት መንገዶች

የንግድ ህግ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ
በኩር ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም ዕትም

ዜና

ማንነት ተኮሩ ጭፍጨፋ እና የዕርምት መንገዶች

ማንነት ተኮሩ ጭፍጨፋ እና የዕርምት መንገዶች

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማይካድራ፣ በወለጋ እና በመተከል የደረሱ ማንነት ተኮር ጭፍጨፋዎችን መነሻ አድርጐ በተደጋጋሚ ውይይት አድርጓል:: የምክር ቤት አባላት በጥር 13 ቀን 2013  6ኛ ዘመኑ በ8ኛው መደበኛ   ጉባኤ ባደረገዉ መደበኛ ስብሰባ በተለይም የመተከሉን ጭፍጨፋ አስመልክቶ በስፋት ተወያይቶ የውሳኔ ሐሳብ  አቅርቧል::

በሽብር ስለመፈረጅ

የመተከልን ምድር የደምና የቀውስ መሬት ካደረጉ ነፈሰ-በላ ታጣቂዎች መካከል ኦነግ ሸኔ ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል:: ኦነግ ሸኔ በወለጋም ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ አድርጓል:: የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኦነግ ሸኔን ‘እርምጃ እየወሰድኩበት ነው’ እያለም ተደጋጋሚ መግለጫ ሲሰጥ ቆይቷል:: በወለጋ እና በተለያዩ ዞኖች ኦነግ ሸኔ የሚያወግዙ ሕዝባዊ ሰልፎችም በተደጋጋሚ ተደርገዋል::

ኦነግ ሸኔ በደቡብ ኢትዮጵያ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን በማውደም፤ በወለጋ መንግሥታዊ መዋቅርን በማፈራረስ እና በመተከል በንፁሀን ዜጎች ጭፍጨፋ ተደጋጋሚ ክስ ይቀርብበታል:: የምክር ቤት አባለትም ኦነግ ሸኔ እና ህወሓት በሽብር እንዲፈረጁ የውሳኔ ሐሳብ እንደኾን አንስተዋል:: በሌላ በኩል ደግሞ በሽብርተኝነት መፈረጅ ብቻ ሠላምን ስለማያመጣ፣ ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች እየተሠሩ ይቆይ የሚል ሐሳብም ተነስቷል::

በእርግጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ለ50 ዓመታት ያህል ስመ ጥር ኾኖ የቆየዉ ህወሓት በትጥቅ ትግል ሀገር ለማፍረስ በመሞከሩ  በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት ከፖለቲካ ፓርቲነት ተሰርዟል:: ህወሓት ከጥር አጋማሽ 2013 ዓ.ም ጀምሮ የፖለቲካ ሕጋዊ ሰውነቱ ተፍቆበታል:: ነገር ግን የህወሓት አመለካከት አሁንም የሀገሪቱ ገዥ መንፈስ መኾኑ መፈናቀሉን እና ጭፍጨፋውን አስቀጥሎታል:: በጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም ቻግኒ ወደሚገኙ የመተከል ተፈናቃዮች ያቀኑት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን “አናቱ ተመቷል:: ቅርንጫፉ ገና ነው” ሲሉ ተደምጠዋል::

ሀገር የማፍረስ እና የጅምላ ጭፍጨፋ አናት የነበረው ህወሓት ቢከስምም፤ የህወሓት ፖለቲካዊ እሳቤ ወራሾች (እንደ አቶ ደመቀ መኮንን አነጋገር ቅርንጫፎች) የችግር ሞገጭ ኾነዋል:: “እነዚህን ለማጥፋት መንግሥት ቀዳሚ አጀንዳው ነው” ሲሉ ተናግረዋል::

የሚሊሻ አደረጃጀት ጉዳይ

የመተከል የመንግሥት መዋቅር አግላይ መኾኑ ለጭፍጨፋዉ አንደኛዉ መንስዔ ኾኖ ይነሳል:: የመጤ እና የነባር የሚል የፖለቲካ ትርክትም ከሐሳብ አልፎ የመንግሥት መዋቅራት መመሪያ ኾኗል:: በዚህም አማራ የፖለቲካ ውክልና አንዳያገኝ ተደርጓል:: ተቋማት አግላይ መኾናቸዉ ለተጠያቂነት አሠራር ዝግ ኾኗል::

የመተከል አስቸኳይ አዋጅ ከሰሞኑ ይፋ እንዳደረገዉ በመተከል ከሁለት ዓመት በላይ ወደ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎች ብዙ ናቸው:: በአንድ ቀን ብቻ ከ600 በላይ ተጠርጣሪዎች ከሁለት ዓመት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቆይተዉ፣ በመታወቂያ ዋስ ተለቀዋል::

አማራ/አገዉ አንዳይታጠቅ፣ እንዳይወክል እና ከፖለቲካዊ ተሳትፎዉ እንዲገደብ ተደርጓል:: በምክር ቤቱም ይሄ ጉዳይ እልባት የሚያገኘዉ ፍትሀዊ እና ተገቢ በኾነ መንገድ ትጥቅ መታጠቅ ሲኖር እንደኾነ ሐሳብ ቀርቦበታል:: ስለዚህ ማስታጠቅን በመፍትሄ ሐሳብነት አንስቷል::

አቶ ደመቀ መኮንንም ለተፈናቃዮች ባስተላለፉት መልዕክት “በሚሊሻ አደረጃጀት በመታጠቅ አካባቢያችሁን እንድትጠብቁ ይደረጋል” ሲሉ ተናግረዋል:: የመተከል አስቸኳይ አዋጅ መሪዉ ብርጋዴር ጀኔራል አስራት ደኔሮሞ ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ከሕዝብ የተውጣጣ የሚኒሻ ኃይል ይደራጃል ብለዋል:: ቀሪው የተግባራዊነቱ ጉዳይ ይኾናል:: በኩር ጋዜጣ በተደጋጋሚ በዘርፉ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች በማነጋገር አግላይ መንግሥታዊ መዋቅሩ መስተካከል ለዜጐች ዋስትና መኾኑን ተደጋጋሚ ዘገባ ሲሠራ መቆየቱ ይታወሳል::

ሀሰተኛ ትርክት

በምክር ቤት አባላት ለጅምላ ጭፍጨፋዉ መንስዔ ኾኖ የተነሳዉ ሌላዉ ጉዳይ ሀሰተኛ ትርክቶች ናቸው:: በየመገናኛ ብዙኅኑ እና በየመድረኮች ሕዝብን ከሕዝብን የሚያጠራጥሩ ስብከቶች መኖራቸው አብሮነትን ሽረዋል:: ይህን የሀሰት ትርክት ለማረም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማድረግ እና ሚዲያዎችን በሕግ መምራት በተገቢነቱ ተነስቷል:: 

ምክር ቤቱ በመተከል የተፈፀመውም ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ እንደኾነም አስምሮበታል:: ይሄን እንዲፈፀም በቀጥታ የተሳተፉ እና በቸለተኝነት የተመለከቱ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ያሉ አመራሮችም እንዲጠየቁ ምክር ቤቱ ጠይቋል:: አቶ ደመቀ መኮንንም አንዳንድ ባለስልጣናት በጭፍጨፋዉ ተጠያቂ እንደሚኾኑ ይፋ አድርገዋል:: 

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ምክርቤት

የቢንሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክርቤት አፈጉባዔ አቶ ታደለ ተረፈ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የመተከል ችግር ከክልሉ ምክርቤት እና ከክልሉ መንግስት በላይ በመሆኑ ከ2011 ጀምሮ ሶስት ጊዜ የአስቸኳይ አዋጅ እንዲታወጅ ሆኗል ብለዋል:: መተከል የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ፣የማዕድን ሃብት እና ሰፊ የእርሻ ቦታ ስላለው የውስጥ እና የውጭ ሃይሎች ይፈልጉታል:: ይህን ፍላጎታቸውን በሃይል ለማሳካት ጀምላ ጭፍጨፋ ተመራጭ አድርገዋል::

አቶ ታደለ መተከል መረጋጋት ያልቻለው ከታች እስከ ላይ ያለው አመራር  የችግሩ ተሸካሚ በመሆኑ ነውም ብለዋል::

አፈ-ጉባኤው ታጣቂ ቡድኑ ከማህበረሰቡ ውሰጥ በመደበቁም ህግ ለማስከበር አስቸጋሪ ሆኖ እንደቆየ ተናግረዋል:: በጥቅሉ አቶ ታደለ በመተከል ላለው ቀውስ የመንግስት መዋቅርን በተባባሪነት እና በቸልተኝነት ወቅሰዋል::

የመተከል አስቸኳይ አዋጅ አስተባባሪው ብርጋዴር ጀኔራል አለማየሁ ወልዴ ‹‹ በሁለት ቢላ የሚበሉ የጸጥታ ሃይሎች አሉ›› ሲሉ ተናገረዋል:: የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ከታጣቂው ጎን ሆነው ለጀምላ ጭፍጨፋው ተባባሪ መሆናቸውን ኮማንድ ፓስቱ አሳውቋል::

 ተፈናቃዮችስ ምን እያሉ ነው?

ጥር 15 ቀን 2013ዓ.ም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ሉዑክ ቻግኒ ወደ ሚገኙ የመተከል ተፈናቃዮች ባመራበት ወቅት ተፈናቃዮች ሀሳባቸውን ለአመራሮች አጋርተዋል:: ከዕለት እርዳታ ይልቅ ዘላቂ መፍትሄ ይቀመጥልን የሚል ሀሳብ ያነሱ ሲሆን፤ በጊዜያዊነት የሚመጣው እርዳታ ግን በተገቢው መንገድ እየደረሳቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል::

ለተፈናቃዮች የሚደርሱ እርዳታዎች በፍትሃዊነት እና በፍጥነት እንደማይሰራጭም ገልጸዋል:: የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቃ አያሌው የተሠጠው እርዳታ በፍትሃዊነት እና በፍጥነት ደርሶ የንጽሃን ህይዎት ይታደግ ዘንድ እኛ አመራሮች ሃላፊነቱን መውሰድ አለብን ብለዋል:: 

አመራሩ ራሱን እንዲፈትሽም ያሳሰቡት አቶ ላቀ፤እርዳታው በፍትሃዊነት እና በፍጥነት እንዲደረስ ይሰራልም ብለዋል:: የገቢዎች ሚኒስትር ከ26 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የአልባስ እና የምግብ እርዳታ ታህሳስ 21 ቀን 2013 ዓም ድጋፍ አድርጎ ነበር::

በኩር ጋዜጣ በተደጋጋሚ በዘገባዋ የመተከሉ ማንነትን ተኮር ጭፍጨፋ እልባት የሚያገኘው ተገቢ የፖለቲካ ውክልና ሲኖር፣አግላይ የመንግስት መዋቅሮች ከተስተካከሉ እና ፍትሃዊ አሰራር ሲጎለብት፣ ጥላቻ የተሸከሙ አመራሮች ሲታረሙ እንደሆነ አስነብባለች:: በጊዜያዊ መፍትሄነት ደግሞ ህግ ማስከበር እና ለተፈናቀሉት ደግሞ እርዳታ ማድረስ ተገቢ እርምጃ እንደሆነ በኩር በተደጋጋሚ ጠቅሳለች::

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ወደ መተከል አምርተው ህዝብ ባወያዮበት ወቅት የጸጥታ ሃይሉ ለአንድ ወር ጊዜ አረጋግቶ  ለመንግስታዊ መዋቅር እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ቢያስተላልፉም የተፈጻሚነት ጊዜው ተራዝሟል:: መተከል በተደጋጋሚ ጥቃት በመድረሱ መንግስታዊ  መዋቅሩ ወደ ስራው አልተመለሰም:: ኮማንድ ፖስቱ ሚኒሻ እና ሌሎች የመንግስት መዋቅራትን እያደራጀ እንደሚገኝ አሳውቋል::

አደረጃጅቱ ሁሉን አቀፍ እና ህዝብን አሳታፊ ካልገሆነ ግን አሁንም አስቸጋሪ እንደሚሆን ተደጋጋሚ ምክረሃሳቦች እየቀረቡ ነው::

የኢኮኖሚ ንቅናቄ መፍጠር እና የእርቀሠላም መድረኮችን ማዘጋጀትም ከህግ ማስከበር ሥራው እኩል የሚቆሙ የመፍትሄ ሃሳቦች ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ የተሰጠባቸው ጉዳዮች ነበሩ::

(የሺሀሣብ አበራ – በኩር ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም ዕትም)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top