ሪባን ቆራጯ – የስኬት እመቤት
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ ባለቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ይለያሉ፡፡ እምብዛም መናገር የማይወዱ ጭምት የሚባሉ አይነት ሴት ናቸው፡፡ የቀዳማዊ እመቤት ኃላፊነቱን ከተረከቡ ወዲህ በትምህርት ቤቶች ግንባታ ረገድ ጮክ ተብሎ ሊነገር የሚችል ታሪክ ሰርተዋል፡፡
በተለይ ከሁለት አሰርት ዓመታት በላይ በዚህ መንበር ላይ የነበሩት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ሲነጻጸር የወ/ሮ ዝናሽ ስኬት ተአምር ሊባል የሚችል ነው፡፡
አንድ ትምህርት ቤትን ከስምንት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ማስረከብ የእሳቸውንና የጽ/ቤታቸውን ቁርጠኝነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው ቀዳማይት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት በመላው አገሪቱ በ300 ሚሊዮን ብር 18 ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ አጠናቋል፡፡
ልብ በል!…በራስ ጥረት ሐብት አፈላልጎ፣ ኪሎሜትሮችን አቆራርጦ በመሄድ ትምህርት ቤት ለመገንባት መነሳት በራሱ ልበ ብሩህነት ነው፡፡ ለወገን ትምህርት ቤት ሰርቶ መሸለም ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ ነው፡፡ የሀገርን መጻኢ ዕጣ ፈንታ በተማሩ ወገኖች እጅ ማስቀመጥ ነው፡፡ በአጭሩ ባለራዕይ ትውልድ የማፍራት ሰፊ እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡
የቀዳማይት እመቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሉቀን ፋንታ ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው ከእነዚህ ግንባታቸው ከተጠናቀቁ ትምህርት ቤቶች መካከል 13 ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ርክክብ የተፈጸመ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ጽህፈት ቤቱ አምስት ትምህርት ቤቶችን ያስመርቃል፡፡
እነዚህ ግንባታቸው አልቆ የተመረቁም ሆነ በቅርቡ የሚመረቁ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መሆናቸውን አቶ ሙሉቀን አክለው ተናግረዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ከመደመር መፅሀፍ በተገኘ ገቢ ለሚሰሩ ትምህርት ቤቶች የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ መጀመራቸውንም አቶ ሙሉቀን አስረድተዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ያስገነቧቸው የመጀመሪያዎቹ አራት ትምህርት ቤቶች በ2011 ዓ.ም ጽህፈት ቤቱን እንደተረከቡ ግንባታ መጀመሩን ያስታወሱት አቶ ሙሉቀን፣ ቀሪዎቹ ግን 2012 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ግንባታቸው ተጀምሮ መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ ሚያዚያ 3 ቀን 2011 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታቸው የተጀመሩት ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ከመስከረም 2012 ጀምሮ ትምህርት መስጠት ጀምሯል።
ከዚህ በተጨማሪም የቀዳማይ እመቤት ጽህፈት ቤት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለ300 ማየት ለተሳናቸው በአዳሪነት የሚያገለግል ትምህርት ቤት እያስገነባ መሆኑን አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል።
ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች የግንባታ ወጪ የወጣውን ገንዘብ በአጠቃላይ ቀዳማይት እመቤት በባህር ማዶ ካሉ ወዳጆቻቸው በስጦታ ማግኘታቸውን ኃላፊው ያስረዳሉ።
ትምህርት ቤቶቹ የተገነቡት በመላ አገሪቱ ነው ያሉት አቶ ሙሉቀን፣ በአማራ እና ኦሮሚያ በእያንዳንዳቸው አራት ትምህርት ቤቶች፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ፣ ጌዲኦ፣ ሻኪሶ ሶስት ትምህርት ቤቶች፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳና መተከል ሁለት ትምህርት ቤት፣ ሶማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ ሁለት ትምህርት ቤቶች፣ አፋር አንድ፣ ጋምቤላ አንድ፣ ትግራይ በሽሬ ከተማ አንድ ትምህርት ቤት ተገንብተዋል።
በ2012 ዓ.ም ተጠናቅቀው ለአካባቢው አስተዳደር ርክክብ የተደረገባቸው አራት ትምህርት ቤቶች 26 የመመማሪያ ክፍሎች ያላቸው እና እያንዳንዳቸው ወደ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ሲሆኑ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በፊት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
እነዚህ ትምህርት ቤቶች በአንድ ፈረቃ ብቻ 1ሺህ 300 ተማሪዎችን ማስተናገድ ይችላሉ ተብሏል።
በትምህርት ቤቶቹ አስፈላጊዎቹን ቁሳቁሶች በማሟላት፣ ለተማሪዎቹም የደንብ ልብስ በማቅረብ ስራ መጀመራቸውን ያስታውሳሉ።
ከእነዚህ አራት ትምህርት ቤቶች ውጪ ያሉት ደግሞ እያንዳንዳቸው 18 የመማሪያ ክፍሎች ሲኖራቸው፣ እያንዳንዳቸው በ13 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር መገንባታቸውንና አንዱ ትምህርት ብቻ በአንድ ፈረቃ 900 ተማሪዎችን እንደሚይዝ ኃላፊው ጠቁመዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአንድ ወቅት “…የጀመርነውን ጨርሰን ሪባን እንቆርጣለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም” ያሉት ይኸን ታላቅ ስኬት ይሆን?
—