በአዲስአበባ ከከንቲባ እስከ ተራ ፈፃሚ ባለሙያ ተንሰራፍቶ የቆየው ዝርፊያ ማንን ተጠያቂ በማድረግ ይጠናቀቅ ይሆን?
(ጫሊ በላይነህ)
የአዲስአበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የቀረበውን የከተማዋን የመሬት ቅርምት፣ የኮንደምኒየም አሰጣጥና አጠቃቀም፣ የቀበሌ ቤቶች ሁኔታ የተመለከተ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሪፖርት በጥሞና ተከታተልኩት።
ጥናቱ ከዚህ ቀደም ኢዜማ የተባለው ተቀናቃኝ ፓርቲ ስለጉዳዩ ይፋ ያደረገው ጥናት ትክክለኛነት ላይ መሀተም ያሳረፈ ነው። የህዝቡን ጥርጣሬ እውነትነት ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው።
ም/ከንቲባዋ ሪፖርቱን አስመልክቶ በማህበራዊ ድረገፅ ከሰጡት አስተያየት እጠቅሳለሁ።
“1,000,050 ካ/ሜ (1050 ሄክታር) ወደ መሬት ባንክ መልሰናል።
ባደረግነው ጥናት በከተማችን በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተያዘ 1 ሺ 338 ሄክታር መሬት አግኝተናል። ይህ መሬት ዋጋው ገንዘብ ሲተመን በ14 ቢሊየን ብር ይሆናል።
በጥናቱ ከተለየው 1 ሺ 338 ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ሺ 50 ሄክታር የሚሆን መሬት እንዲፀዳ በማድረግ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ የከተማውን ልማት በሚያረጋገጥ መልኩ ለትልልቅ የልማት ስራዎች በጨረታ እና በምደባ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል።
.የከተማችን ነዋሪ ዋነኛ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ የቆየውን የጋራ መኖርያ ቤቶችን (ኮንዶሚኒየም) እና የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ በተጠናው ጥናት መሰረት 21 ሺ 695 የጋራ መኖርያ ቤቶች በተለያየ ህገ-ወጥ መንገድ ተይዘዋል።
በተጨማሪም ለጥናት እንዲለዩ ከተደረጉ የቀበሌ ቤቶች 14 ሺ 641 ያለ አግባብ ለመኖርያና ለንግድ የተከራዩ፣ ውል የሌላቸው እና በሌላ በህገ-ወጥ ይዞታነት የሚገኙ መሆኑን አረጋግጠናል።
በግኘቱ መሰረት ህጉን ተከትለን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እናረጋግጣለን። በጉዳዩም የተሳተፉ አካላት ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ግኝቱን ወደ ፌደራል ዐቃቤ ህግ እና ፌደራል ፖሊስ መርተናል።”
ወ/ሮ አዳነች ዝርፊያው ወደኋላ በመሄድ ከ1997 በፊት ጀምሮ የተንሰራፋ እንደነበር በመጥቀስ በገደምዳሜ ለውጡ ያመጣው አለመሆኑን ጠቆም አድርገዋል።
ይኸም ሆኖ ግን ወ/ሮ አዳነች ስለተጠያቂነት ማንሳታቸው ከምራቸው ይሆን የሚያስብል ነው። ተጠያቂነት ማለት ምን ማለት ነው? የከተማዋ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ይጠየቃሉ ማለት ነው። ከከንቲባዎቹ ከእነአቶ አርከበ እቁባይ ጀምሮ እስከ ታከለ ኡማ ድረስ የተዘረጉ በመንግስታዊ መዋቅር የታገዙ ዝርፊያዎች ለፍትህ አደባባይ ይቀርባሉ ማለት ነው።
ጉዳዩ ከከንቲባ እስከ ተራ ፈፃሚ ባለሙያ የሚወርድ መሆኑ፣ የፌደራል ሌሎች ባለስልጣናትን፣ በከተማዋ ትልልቅ የሚባሉ ባለሀብቶችን፣ ደላሎችን የሚያነካካ፤ በአጭሩ ሰበዙ ሲመዘዝ መዳረሻው የማይታወቅ ከመሆኑ አንፃር መንግስት ይኸን ሁሉ ሌባና የሌባ ተባባሪ አራግፎ የመጠየቅ ቁርጠኝነት አለው ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በሙስናና ብልሹ አሰራር ከአናቱ የበሰበሰ የፖለቲካ መዋቅር በቀላሉ አፅድቶ በህዝብ ዘንድ ተአማኒ መሆን ይቻላል ወይ የሚል ጥያቄንም የሚያስከትል ነው።
በዚህ ላይ በዝርፊያ ከሚጠረጠሩት አንዳንዶቹ አሁንም የለውጥ ካባ ደርበው በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ በሹመት ላይ ሹመት ደራርበው የምናያቸው ናቸው። ባለሀብቶቹም እንደሸገር ላሉ ኘሮጀክቶች ፈጠን ብለው ከሰረቁት ቆንጥረው በማካፈል “የልማት አርበኛ” የሚል ክብርን የደረቡ ናቸው።
ወ/ሮ አዳነች ፋይሉን ለፖሊስና ለአቃቤ ህግ መርተነዋል ሲሉ እነዚህ አይነኬዎች ይከሰሳሉ እያሉን ነው? ወይንስ ጉዳዩ ጥቃቅንና አነስተኛ ሌቦችና ተላላኪዎችን በማደን ይጠናቀቅ ይሆን? ያው ነገሩ “የሞተው ወንድምሽ፣ የገደለው ባልሽ፣ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ፣ ከቤትሽ አልወጣ” አይነት ነው። የጉድ ሀገር!! (የአዘጋጁ ማስታወሻ:- ይህ ፅሁፍ የፀሐፊውን እንጅ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም)