አሳሳቢው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በጋምቤላ ክልል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
የእስረኞችን አያያዝ ማሻሻል እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ማረጋገጥ ይገባል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽን) በጋምቤላ ክልል ያለው የእስረኞች አያያዝና የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት በተመለከተ በቂ ማሻሻያዎች አለመደረጋቸው እንደሚያሳስበው ገለጸ።
ኮሚሽኑ ከታኅሣሥ 12 እስከ ታኅሣሥ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በጋምቤላ ከተማ እና በአኝዋህ ዞን በመገኘት፣ በአካባቢው ስላለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ክትትል አድርጎ ከሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።
ኮሚሽኑ በጎበኛቸው የክልሉ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች አያያዝና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው ነው። በተለይም በኦነግ ሸኔ አባልነት ተጠርጥረው በጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤት ከታኅሣሥ ወር መግቢያ ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሁለት የ 11 እና የ 12 ዓመት ሕፃናት ወንዶች፣ እንዲሁም አንድ የ14 ዓመት ሕፃን ሴት በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ አሳስቦ፣ በተጠርጣሪዎች ሕፃናት ወንዶች ላይ ከፍተኛ ድብደባ ያደረሱ የፀጥታ አባላት ላይ አፋጣኝ ምርመራ በማካሄድ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል። ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ሕጻናቱ በእስር ላይ ናቸው።
በተጨማሪም “ሕወሓትን በገንዘብ እና በተለያየ መንገድ ይረዳሉ፣ በክልሉ ውስጥ በሕዝብ መካከል ግጭት የመቀስቀስ ዓላማ ይዘው ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ምክንያት፣ ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በአቦቦ ከተማ፣ በአኝዋህ ዞን ማረሚያ ቤት 20 ሰዎች፤ እንዲሁም በጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤት 70 ሰዎች፣ በአጠቃላይ በአብዛኛው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ 90 ሰዎች፣ በክልሉ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።
በኢሰመኮ ጉብኝት ወቅት፣ በእነዚህ 90 ተጠርጣሪዎች ላይ በፌዴራል ፖሊስም ሆነ በክልሉ ፖሊስ በኩል የተጀመረ የወንጀል ምርመራ ሂደት አለመኖሩ በመገለጹ፣ ኮሚሽኑ ይህንኑ አሳሳቢ ጉዳይ ለሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች አሳውቆ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀመርና የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ አሳስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል፣ ኮሚሽኑ በጉብኝቱ ወቅት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን አነጋግሯል።
ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች ‘የምርጫ ሥነ ምግባር መግባቢያ ሰነድ’ የፈረሙ መሆናቸውን ገልጸው፣ ቢሮና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለማግኘት፣ በክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ለመስራትና፣ የፓርቲያቸውን ዝግጅቶችን ለማድረግ እንግልት እንደሚገጥማቸውና በአንዳንድ አባላቶቻቸው ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ መድረሱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በተለያየ ወቅት 35 አባላቱ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ለእስር መዳረጋቸውን ገልጿል። እንዲሁም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ቤተሰብ በመሆናቸው ከመንግስት ስራ የታገዱ እና ያለፈቃዳቸው ‘ለብልጽግና ፓርቲ መዋጮ’ በሚል ከደሞዛቸው ላይ የመዋጮ ክፍያ የተቆረጠባቸው ሰዎች መኖራቸውን አስረድተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በክልሉ የሚገኙ የምርጫ ወረዳ ተወካዮች ብዛት አወሳሰን ዙሪያ ያላቸውን ቅሬታ ለክልሉ ባለሥልጣናት ቢያሳውቁም፣ ምላሽ አለማግኘታቸውንም ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል።
ኢሰመኮ በእነዚህና ሌሎችም የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በተወያየበት ወቅት፣ የክልሉ ኃላፊዎች ለሰብአዊ መብቶች መሻሻል በጎ ምላሽ ሰጥተው፣ በተለይም የገዢው ፓርቲ አባል ካልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ላይ ሲሰበሰብ የነበረው የፓርቲ አባልነት ክፍያ በተመለከተ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።
በክልሉ ስላለው አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታና ኮሚሽኑ ያቀረባቸውን ምክረ ሃሳቦች አተገባበር በተመለከተ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት “የጋምቤላ ክልል መንግስት ትኩረትን የሚሹ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ የሕፃናት እስረኞችና የተጠርጣሪ ታሳሪዎችን የዋስትና መብት ማረጋገጥ እጅግ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል” ብለዋል።
ስለሆነም በሁሉም የክልሉ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ሕፃናት በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁና ጉዳያቸውን ከእስር ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ እንዲደረግ፣ በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ምርመራ እንዲጀመርና የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት በአፋጣኝ እንዲከበር፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ በክልሉ የሚገኙ እስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ያቀረባቸው ምክረ ሃሳቦች እንዲተገበሩ ዋና ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አክለውም “ሀገራዊ ምርጫው እየተቃረበ በመሆኑ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የክልሉ እና የፌዴራል መንግስት አካላት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን እንዲያረጋግጡ ያስፈልጋል” ብለዋል።