“ህወሓቶችን የዘረፉትን ንብረት በሙሉ አስጥለን ከመኪና አስወርደን ነው ያባረርነው”
~ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ
ጁንታው ያጋጠመው ሽንፈት በጣም አሳፋሪ እንደሆነ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።
ኤታማዦር ሹሙ ሰሞኑን ለገበያ ከቀረበችው ዘመን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፣ ጁንታው ያጋጠመው ሽንፈት አሳፋሪ ነው ። እንዲህ አይነት ድምሰሳ አይቼ አላውቅም ፣ ሽንፈቱ በጣም አዋራጅ ነው።
ጁንታው የዘረፈውን ንብረት ሁሉ ጥሎ ነው የሸሸው ። የዘረፈውን ንብረት በሙሉ አስጥለን ከመኪና አስወርደን ነው ያባረርነው ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ፣ ከትላልቅ ብርጌዶች ወደ ትናንሽ ዩኒቶች ፣ከሻንበል ጋንታ ከፍ ሲል ሻለቃ ወርደው እሱም እንደገና ተደምስሶባቸው አሁን ግለሰብ ነው እየፈለግን ያለነው ብለዋል።
የህውሓት የጥፋት ጁንታ ለ27 ዓመታት በሴራ ሲመራ ቆይቶ በሕዝብ ትግል ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ዳግም ለመመለስ በሰሜን ዕዝ ላይ የተነኮሰው ጥቃት የጥፋቱ ጥግ እስከምን ድረስ እንደሆነ ያሳየ እንደነበር አመልክተዋል።
እኔ ካልመራሁ ሀገር ትፈርሳለች፣ የሚመራው መንግስት አሃዳዊ ነው በማለት ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ሰሚ ቢያጣ የሰሜን ዕዝ ላይ ሴራ በመጠንሰስ እሽ ያለውን ከጎኑ በማሰለፍ፣ እምቢ ያለውን ደግሞ በግድ በማንበርከክ እና ትጥቁን በመውረስ ዳግም ለሥልጣን መቆናጠጥ ማሰባቸው ለውድቀታቸው መነሻ መሆኑን ገልጸዋል ።
“እነሱ ያሰቡትን ሲያደርጉ ሰራዊቱ ባላሰበው እና ሀገር ሰላም ብሎ በተኛበት ነው። በትምህርት ቤት ውስጥ እስክብሪቶ እና ደብተር የያዙ ጠበንጃ ያልያዙ ወታደሮችን ይዘው ሰሜን ዕዝ ከእኛ ጋር ነው እያሉ ቢያወሩም ሠራዊቱ ግን የሀገር ሠራዊት በመሆኑ እና የበደል ጦርነት በመሆኑ ራሳቸው በለኮሱት እሳት ላይመለሱ ተቃጥለዋል” ብለዋል።
የሰሩ በሰሩት አሳፋሪ ተግባር እና ጥፋት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ‹‹ሆ›› ብሎ በመነሳት በጁንታው ቡድን ቁጣውን በመግለፅ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም የሕግ ማስከበር ዘመቻው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቅቅ እንዳደረገው አብራርተዋል።
የጁንታው ኃይል በተወሰደበት የሕግ ማስከበር እርምጃ ከመቀሌ ሲወጣ የነበረበትን ቢሮ በሙሉ ኮምፒዩተሮችን በመሰባበር፣ ዶከመንቶችን ቀደው፣ ግማሹን አቃጥለው ወንበር ሰብረው ነው የወጡት ያሉት ጄኔራሉ፣ ተግባራቸው ‹‹ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል›› በማለት ነው። አሁን ላይ የመቀሌ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደር ስራ ለመስራት መረጃ የለውም። የሰሩት ተግባር ለወጡበት ሕዝብ የማይጨነቁ የባእዳን ሀገር ወራሪ እንኳ የማይፈፅመው ድርጊት መፈፀማቸው ከልክ ያለፈ እኩይ ተግባራቸውን እንዳሳየ አስታውቀዋል።
“በ27 ዓመታት የሰሩት ግፍ በሕዝብ ብቻ ሳይሆን በእኛ በሰራዊቱ አባሎች ሁሉ ግፍ ይሰሩ ነበር፣ ምክንያት ይፈለግልን ነበር፣ ምክንያት እያሳጣን፣ ቀን እየጠበቅን ነበር እዚህ የደረስነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚው ላይ የሰሩት ዘረፋ በእጅጉ ዘግናኝ ነው። ሀገርን እና ሕዝብን ቦጥቡጦ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በአብሮነት እንዳይኖሩ በማጋጨት በሕዝብ ደም የኖሩ ናቸው”ብለዋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የህዳሴውን ግድብ ተደራጅተው ሌላ እንዳይገባ በማድረግ በአጭር ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ገንዘቡን በልተዋል። ይህ ተግባራቸው መረን የለቀቀ ጭካኔ እና ፀረ ኢትዮጵያዊነት ተግባር ነው። ይህ ሁሉ ግፋቸው አሁን ላይ ሞልቶ በመፍሰሱ ዳግም ላይመለሱ እንዲቀበሩ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
(አዲስ ዘመን ጥር 15/2013)