Connect with us

ይድረስ ለክቡር ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

ይድረስ ለክቡር ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ይድረስ ለክቡር ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

ይድረስ ለክቡር ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

ክቡርነትዎ ባሉበት ሰላምዎ ይብዛ።

ትላንት በቻግኒ ራንች የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ተገኝተው ከተፈናቃዮች ጋር መወያየትዎን ከመንግስት መገናኛ ብዙሀን ሰማሁ። 

በዚህም ውይይት ላይ መተከል በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል እንጂ በፖለቲካ አመራሩ እንደማይተዳደር፣ በግጭቱ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተሳትፎ የነበራቸው ወገኖች ሁሉ ለህግ እንደሚቀርቡ፤ ከዚህ በኋላ የዜጎች እሮሮና ጩኸት እንደሚቆም መናገርዎ መስማቴ በመንግስትዎ ላይ ትልቅ ተስፋን እንድሰንቅ ስላገዘኝ በቅድምያ አመሰግንዎታለሁ ።

በዚሁ ንግግርዎ በኢትዮጵያ አንድ ብሄር ብቻውን የሚኖርበት መሬት አይኖርም ማለትዎ የመገናኛ ብዙሀኑን ጉንጭ ሞልቶ መዋሉንም ታዝቤአለሁ።

በመተከል የተከሰተውን አንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ከአካባቢው ነዋሪዎች ሚልሽያዎችን መልምሎ፣ አሰልጥኖ በማስታጠቅ ራሳቸውን እንዲጠብቁ እንደሚያደርግ መወሰኑን ይፋ ማድረግዎ ሰፊ የመነጋገርያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።ይኸ አይነቱ ንግግር ካልተሳሳትኩኝ ከእርስዎ አንደበት ሲሰማ ይኸ ለሁለተኛ ጊዜ ይመስለኛል።

እርግጥ ነው፤ የአካባቢውን ነዋሪዎች የማስታጠቅ ጉዳይ   በአካባቢው ከቁጥጥር ውጪ የሚሆን ሌላ ዙር የዘር ግጭት እንዳያስነሳ ስጋታቸውን የሚገልፁ ወገኖች ቁጥር ጥቂት እንዳልሆነ እረዳለሁ። የእነዚህ ወገኖች የስጋት መነሻ ይታጠቃል የተባለው ኃይል ከአንድ ብሄር እንደሚሆን ታሳቢ በማድረጋቸው ይህ ኃይል በቀጣይ የበቀል እርምጃ መውሰድ እንዳይጀምር መስጋታቸው ነው። በግሌ ግን የሚቋቋመው ሚልሽያ ከአካባቢው ብሄር ብሄረሰቦች የተውጣጣ፣ የተቋቋመበትን ተልእኮ የሚያውቅ የመደበኛ ሀይል አጋር የሚሆን በመሆኑ የእርስበርስ ግጭት የመነሳቱ እድል እጅግ ጠባብ እንደሚሆን እገነዘባለሁ።

ከዚህ ይልቅስ የሚያሳስቡኝ አንዳንድ ጥያቄዎች አሉኝ። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በራሱ አቅም ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ ለምን ተሳነው? የተደረጉ ጥረቶች ለምን ውጤት ሳያስገኙ ቀሩ? የችግሩ አካላት እነማን ናቸው? የት ነው ያሉት? የአካባቢው የመንግስት መዋቅር ተሳትፎ ምን ይመስላል የሚለው በጥናት ተመልሷል ወይ? ምናልባትም አልተመለሰ ከሆነ እነዚህ ጥያቄዎች በጠራ ሁኔታ መልስ ባላገኙበት ሁኔታ የሚሊሽያ ሰራዊት ወደማቋቋም መግባቱ ምናልባት በጊዜያዊነት እሳቱን አጥፍቶ ፍሙን ከማዳፈን የዘለለ ፋይዳ ይኖረዋል ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ።

ከምንም በላይ ደግሞ በኮማንድ ፖስት ስር የተዋቀረ የፌደራል ሀይል ያላስቆመውን ችግር በሚልሽያ የለብለብ ስልጠና ታጣቂ ቀውሱን ለመቆጣጠር መሞከሩ ችግሩን አሳንሶ ማየት አይሆንም ወይ የሚለውም በቅጡ መልስ ማግኘት አለበት።

ክቡርነትዎ ዘር ተኮር ትርክቶችን፣ ፍጅቶችን በዘላቂነት ለማስቀረት፣ ሀገሩን የሁሉም ኢትዮጵያዊ መኖርያና መከበሪያ ለማድረግ  ብሔር ተኮር አደረጃጀቶች በህግና በስርአት ማገድ ይገባል  በሚለው የብዙዎች ሀሳብ እስማማለሁ። 

ይህን ለማድረግ ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ የግድ ይሆናል። ነፍሱን አይማረውና ህወሓት እንዲህ አይነቱን አማራጭ “አሀዳዊነት፣ ጨፍላቂነት” በሚሉ መርዘኛ ቃላት በመመረዝ የማይሞከርና የማይታሰብ አድርጎ ሲያቀርበው ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ አሁንም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባደፈጡ ርዝራዥች እና መርዛማ አስተሳቡን ተሸካሚ የውስጥና የውጭ ሀይሎች ዘንድ ተግዳሮት ሊያጋጥም እንደሚችል የሚታወቅ ነው።

ነገርግን የብሄር አደረጃጀትን ለማስቀረት የአሀዳዊ የመንግስታዊ አደረጃጀትን መከተል የግድ አይደለም። በፌደራል አደረጃጀት ውስጥ ሆኖም ዜጎችን በቋንቋና በብሄር ሸንሽኖ ራሳችሁን በራሳችሁ አስተዳድሩ ከማለት ይልቅ በጅኦግራፍ የማካለልና በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች በየክልሉ የማቀፍ አደረጃጀት አማራጭ ለማየት ራስን ማዘጋጀት፣ ተገቢውን ጥናት ማካሄድ፣ በየደረጃው ምክክር ማድረግ ይገባል።

የመንግስት የአስተዳደር ዘይቤ ወደአሀዳዊነት መቀየርም በተገቢው ጥናትና የህዝብን ተጠቃሚነት ማማከሉ እስከተረጋገጠ ድረስ መታሰቡም ሆነ መተግበሩ ስህተት አይደለም። በዓለም ላይ እንደብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ የመሳሰሉ  በዴሞክራሲ የበለጸጉ  አገራት የአሃዳዊ አስተዳደር ዘየን የሚከተሉ መሆናቸውን ማስተዋል ይገባል።

በአንፃሩ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካንን ጨምሮ አውስትሬሊያ ካናዳና ብራዚልን የመሳሰሉ አገሮች የፌደራል ስርአትን ይከተላሉ።እናም ጥያቄው ችግሮቻችን ከመሰረቱ ሊፈታ የሚችለውን አደረጃጀት ህዝብን ባስተፈ መልኩ  መምረጥና የመተግበር ጉዳይ ነው።

አሁን ወሳኙ ጥያቄ መንግስታችን ብሄር ተኮር አደረጃጀት ላይ ያለው አቋም ምንድነው? የሚለው ጥርት ብሎ አለመታወቁ ይመስለኛል። ክቡርነትዎ ከመሪ ፓርቲዎና መንግስትዎ የጠራ እና የማያሻማ ርእዮተ አለም፣ ግልፅ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንፈልጋለን። 

ብልፅግና እንደስሙ ለመሆን የፓለቲካ ተቃርኖዎችን ከዘርና ከጠባብነት አስተሳሰብ በማላቀቅ ሰፊ ሀገራዊ መሰረት ላይ ማስቀመጥ ካልቻለ ሀገሪቱ ከቀውስ አዙሪት የመውጣትዋ ነገር አሳሳቢ እንደሆነ መቀጠሉ አይቀሬ ይሆናልና ጉዳዩ በጥብቅ ቢታሰብበት?

(ጫሊ በላይነህ)

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top